ሰሜን ኢትዮጵያ በስድስት ግንባሮች ያለው ወቅታዊ ሁኔታ
ግርማ ካሳ
1) የራያ ግንባር
የመከላከያን ከትግራይ መውጣት ድንገት እንደመሆኑ፣ አንዳንድ መንግስታዊ አሻጥሮች በመደረጋቸው ወያኔ ያለ ምንም ዉጊያ ኮረም፣ አላማጣ፣ ዋጃ፣ በአጠቃላይ ራያን፣እንዲሁም ቆቦን ሮቢት የመሳሰሉት ይዛ ወልዲያ ደጃፍ ደረሰች፡፡
በአሁኑ ወቅት በራያ ግንባር ወልዲያና መርሳ አካባቢ ጦርነቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከሌሎች ግንባሮች ሁሉ ይህ የራያ ግንባር ላይ ወያኔ ጠንከር ያለችበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በወልዲያ ከወልዲያ ዙሪያ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ መድፍ እየተኮሰች ወልዲያን ለመያዝ ብዙ ሙከራ እያደረገች ነው፡፡ ይሄ ጽሁፍ እስከተሳፈበት ጊዜ ድረስ የወልዲያ ሕዝብ ከተማዋን ከወያኔ ጠብቆ እንዳለ ነው የሚነገረው፡፡ ከወልዲያ ወረድ ብሎ መርሳ ላይ ግን ትንሽ የተወሳሰበ ነገር ነው ያለው፡፡
2) ዋገምራ ግንባር
በዋገመራ ዞን በቀላሉ የአበርገሌ ወረዳን እንዲሁም ላሊበላ ከተማ ወያኔ በአሻጥር፣ ያለውጊያ ስትቆጣጠር፣ ሰቆጣ ለመያዝ ያደረገችው ሙከራ እስከ አሁን አልተሳካም፡፡
3) የወልቃይት ግንባር
በወልቃይት ግንባር ወያኔ ብዙ ጊዜ እንደ አዲ ጎሹ ባሉ አካባቢዎች ዘልቃ ለመግባት ሞክራ፣ ሁሉንም ጊዜ በሽንፈት ነው የተመለሰችው፡፡ ብዙ ታጣቂዎችን አጥታለች፡፡ በዚያ መስመር እነ ኮሎኔል ደመቀ አይቀጡ ቅጣት ነው የቀጧት፡፡
ያ ብቻ አይደለም ሱዳን ያሉ ሳምሪ የሚባሉ አሸባሪ የሰለጠኑ ታጣቂዎቿንም ከሱዳን ወደ ወልቃይት ለማስገባት አንድ ሁለቴ ሞከራም አልተሳካላትም፡፡
እስከ አሁን ባለው እንደገና ጥቃት ካልተከፈተ የወልቃይት ግንባር በወያኔ ተሸናፊነት ተጠናቂል ማለት ይቻላል፡፡
4) የጠለምት ግንባር
በጠለምት ግንባር ወያኔ አሁንም በአሻጥር ማይጠምሪ፣ ዘሪማ ። አዲ አርቃይ የመሳሰሉትን ይዛለች፡፡ ሆኖም ባለፉት 4 ቀናት የአማራ ሕዝባዊ ሰራዊት በከፈተው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በጠለምት ግንባር ብዙ ሽንፈቶችን እያስተናገደች ነው፡፡ በዚያ ያሉ በርካታ ስትራቲጂክ ምሽጎቿ ተይዘውባታል፡፡ ብዙ ታጣቂዎቿንም እያጣች ነው፡፡
ይህ ግንባር ከሁሉም ግንባሮች በጣም አስቸጋሪ ግንባር ነው፡፡ ቦታው እጅግ ተራራማ በመሆኑ፡፡ ሆኖም ግን ከሞላ ጎደል በዚያ የሚሰማው ጥሩ ነገር ነው፡፡
5) የአፋር ግንባር
በአፋር ግንባር ወያኔ ጭፍራን በመያዝ ወደ ሚሌ ለመገስገስና የጅቡቲ አዲስ አበባን መስመር ለመዝጋት ብዙ ተንቀሳቅሳ ነበር፡፡ ብዙ ሰራዊትም አሰልፋ ነበር፡፡ የአፋር ክልል ዞን 4 ካሉ አምስት ወረዳዎች አራቱን ተቆጣጥራም ነበር፡፡
ሆኖም አሁን ከሁለቱ ወረዳ ትልቅ ሽንፈት ስላጋጠማት ለቃ የወጣች ሲሆን፣ ከተቀሩት ሁለቱ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ትለቃለች ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡
በአጭሩ የአፋር ግንባር ጦርነት በወያኔ ተሸናፊነት በቀናት ውስጥ ሊጠናቀቅ ይችላል ማለት ነው፡፡
6) የመቄት/ጋይንት ግንባር
ወያኔ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያዎች ከጎጃምና ጎንደር ወደ ወሎ እንዳይመጡ ለማጨናገፍ ያደረግችው ነገር ቢኖር የወልዲያን ደብረ ታቦርን መንገድ መዝጋት ነበር፡፡ እንደ ጋሸና፣ ደብረ ዘቢጥ ፣ ኮኪት፣ ፍላቂት ያሉ ከተሞችን ይዛ ነበር፡፡ ከደብረ ዘቢጥ ጨጨሆ ፣ ንፋስ መውጫ ብለው ደብረ ታቦርን ለማያዝ ነበር እቅዳቸው፡፡ ከአስር ሺህ በላይ በጣም በከባባድ መሳሪያ የታጠቀ ሰራዊት ነበር ወያኔ ያሰማራቸው፡፡
ሆኖም የጋየንት ሚሊሺያዎች፣ የአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም መከላከያ በቅንጅት፣ በጥንቃቄ፣ ከበስተኋላ በሙሉ ስንቅና ትጥቅ በታጀበ መልኩ ባደረጉት ጥቃት ከጨጨሆ ተነስተው ደብረ ዛቢጥ የነበረው የወያኔ ጦር በመደምሰስ ፣ ኮኪት፣ ፍላቂት እያሉ ወደ ጋሼና እያመሩ ነው ከጋየንት የመጣው ጦር ከደብረ ታቦር ወልዲያ ያለውን መንገድ ሙሉ ለሙሉ ከወያኔ በማጻዳት የራያ ግንባር የመቀላቀል እድሉ የሰፋ ነው፡፡
እስከ አሁን በተደረጉ ጦርነቶች ከባድ መሳሪያ ከመያዛቸው የተነሳ ወይንም በአሻጥር ካልተለቀቀላቸው በቀር፣ ወያኔዎች በእኩል ደረጃ ዉግያ ገጥመው የያዙት ቦታ የለም፡፡ ያ ብቻ አይደለም በብዙ ቦታዎች ከባድ መሳሪያዎችንም ይዘው የአማራ ሚሊሺያዎች ድባቅ ያደረጓቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው፡፡
በመከላከያና በአማራ ልዩ ኃይል ዘንድ ችግሮች ነበሩ፡፡ አሁንም አሉ፡፡ የአመራር ችግር፡፡ ነገር ግን እነ ጀነራል ተፈራ ማሞ ብዙ ነገሮች እያስተካከሉ በጥንቃቄ እየተጓዙ በመሆናቸው ስራዎችን በትክልል እንዲሰሩ ፋታና ጊዜም እንደሚያስፈልጋቸው መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ውጣ ዉረዶች አሉ፡፡ ነገሮች መስመር ሲይዙ አንዳንድ ቦታ ሕወሃትን አይለው ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በርግጠኝነት ሕወሃት ሕዝብን ማሸነፍ አትችልም፡፡ ትደመሰሳለች ወይንም ተገዳ ለድርድር ትቀርባለች፡፡