>

"ትህነግ ዛሬ "ጠቤ ከብልጽግና ነው" ስትል አትስማት፤ ትናንት "ከደርግ ነው" ብላ ገብታ ሃያ ሰባት አመት አስለቅሳሃለችና...!!!" (ስናፍቅሽ አዲስ)

“ትህነግ ዛሬ “ጠቤ ከብልጽግና ነው” ስትል አትስማት፤ ትናንት “ከደርግ ነው” ብላ ገብታ ሃያ ሰባት አመት አስለቅሳሃለችና…!!!”
ስናፍቅሽ አዲስ

እዚሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንዱ ሰው ትህነግን እና መለኛ የማጭበርበሪያ ዘዴዋን አስመልክቶ የጻፈውን አነበብኩ፡፡ እውነት መሆኑና ታሪክ ራሱን መድገሙ በጣም ገረመኝ፡፡ ከደደቢት ደደብ ሀሳብ ይዛ ጭቁን ታጋዮችን መጠቀሚያ በማድረግ አዲስ አበባ የገባችው ትህነግ በወቅቱ በየመንገዷ ችግሬ ከንጹህ ህዝብ ሳይሆን ከደርግ ነው ብላ ነበር፡፡
ችግርሽ ከደርግ ከሆነና ከእኛ ጠብ ከሌለሽ ያላት ገበሬ ያለውን እያበላ አሳለፋት፡፡ አራት ኪሎ ገብታ ነጋዴ ሆነች፡፡ ያበላትን ገበሬ በማዳበሪያ እዳ በላችው፡፡ ደርግ ወድቆ የምትጥለው ስታጣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ጣለች፡፡
ለትግራይ ገበሬ ጽዮናዊ ነኝ ጽዮንህ ስር መስጂድ አይሰራም እያለች ለደቡብ ገበሬ ኦርቶዶክስ ነፍጠኛ ናት ብላ ሀገር በእምነት እንዲባላ፣ በዘር እንዲለያይ አደረገች፡፡ ችግሯ ከደርግ እንዳልነበረ ገብታ አረፍ ሳትል ላግዘው ያለችው ጀነሬተር ምስክር ነበር፡፡
ደርግ ላይ እንጂ ንጹህ ላይ ችግር የለብኝም ያለችው ትህነግ አፋኝ ሆነች፤ ጠላቷ ንጹህ ሰው ሆነ፡፡ ዘራፊነቷ ለየለት፤ መርከብ እስከ መስረቅ የደረሱ ወንበዴዎችን በአፍሪካ ታሪክ አበረከተች፡፡ ያ ሁሉ የጫካ ቃል ኪዳን ተረሳና አማራን ጠላት ነው ብላ ዳግም አወጀች፡፡
ዛሬ ሁሉን ረስታ ዳግም እንደ ድሮው ያንኑ ድራማ ልትደግም ትፈልጋለች፡፡ ከደርግ ነው ችግሬ ያለችውና መንግስቱ ሃይለማርያም ነው ጠላቴ ብላ የማርያም መንገድ ያገኘችው ትህነግ ሊቀ መንበሩን አላገኘቻቸውም፤ እሳቸው ዙምባቤ ገቡ፡፡ እሷም አዲስ አበባ ገብታ አዲስ ታሪክ ፈጠረች፡፡
የሺህ አመት ባለታሪኳን ኢትዮጵያ ከአክሱም ሐውልት ስር ብረት አንግባ ትግል የጀመረችው ትህነግ የመቶ አመት ታሪክ ያላት ሀገር ናት ብላ ታሪክ ካደች፡፡ የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው ብላ የጋራ ታሪካችን ምንም እንዲመስለን ሰራች፡፡
በዚህ አላበቃችም ባንዲራ ጨርቅ ነው በሚል መፈክር የሀገርን ክብር አፈር አስገባችው፡፡ ነውር ክብር የሆነበት ሥርዓት ሰፈነ፤ አናሳዎቹ ታጋዮች ኢትዮጵያን በዝብዘው በብዙሃኑ ላይ ቀንበር ሆኑ፡፡
ዛሬም ደግማ ትህነግ ችግሬ ከብልጽግና ጋር ነው እና አብይ አህመድ ነው ጠላቴ ብላ እንደለመደችው ልትቀጥፍ ትሞክራለች፡፡ ዶክተር አብይን አሳይታ እሱን ብቻ ፈላጊ ነኝ ብላ ህዝብ ለመብላት ያሰፈሰፈው መንፈሷ የትም ላይደርስ እምነት አጥቶ ሜዳ እየቀረች ነው፡፡
የቢቢሲው ጋዜጠኛ እናንተ በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ እንወስን ባይ ናችሁ ሲል ለጄነራል ጻድቃን ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ የፖለቲካ እስረኞችን በማጎር በዓለም ዘንድ ሳይቀር ስመ ገናናዋ ትህነግ አሁን የፖለቲካ እስረኛ ይፈታልኝ የሚል ዜማ የማጭበርበሪያዋ ማጀቢያ አድርጋዋለች፡፡
ኢትዮጵያ ምኔም ናት አፈርሳታለሁ ያለ ሃይል ጠቤ ከዶክተር አብይ ነው ሲል እንደ ቀድሞው ታሪክ ከደርግ ነው ብሎ ኢትዮጵያን አንድ ዘመን ወደ ኋላ እንደጎተተው ዛሬም ያንን ሊደግም ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያን የማይፈልግ አማጺ ከኢትዮጵያ መሪ ነው ጠቤ ካለ ጠቡ ከኢትዮጵያውያን መሆኑን ሊያውቅ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፡፡
Filed in: Amharic