>
5:13 pm - Thursday April 18, 7354

የሳውዲ ጉዳይ * የውጭ ጉዳይ ሚር ይውረዱ ወይ ይፍረዱ ‼ (ነቢዩ ሲራክ)

የሳውዲ ጉዳይ

— የውጭ ጉዳይ ሚር ይውረዱ ወይ ይፍረዱ ‼
ነቢዩ ሲራክ

* አምባሳደር ሌንጮና ዲፕሎማቶቻችን…
  አልተሰሙም ወይም አልቻሉበትም  ‼
 
ይድረስ ለክቡር አቶ ደመቀ መኮንን …
 ከሁሉ በማስቀደም በየዶር አቢይ አህመድ እና በእርስዎ የመከመራው መንግስት ዛሬ ላይ በህግ የማስከበር ወሳኝ ሀገርና ወገንን በመታደግ ብርቱ ተግዳሮቶች ላይ መሆኑን አሳምሬ አውቃለሁ ። በአንጻሩ የውጭ ጉዳይ ሚር መ/ቤት በዲፕሎማሲው መስክ ለአለም ማህበረሰብ በመረጃ ቅበላው ስራ ላይ እንደሆነ እረዳለሁ። ያም ሆኖ በሳውዲ አረቢያ በከፋ አደጋ ላይ ያለው ዜጋ ቁጥር በአማራና በአፋር ከተፈናቀለው በመቶ ሽዎች የሚቆጠር ዜጋ የማይተናነስ ነውና አሳስቦኝ በእርስዎ በውጭ ጉዳይ ሚሩ  በኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብየ አምናለሁ ።
    ክቡርነትዎ ጥቂት በውል ይረዱት ዘንድ ሰሞነኛውን የዜጎች ይዞታና ይህን መልዕክት እንድልክልዎ ገፋኤ ስለሆነኝ ጉዳይ በአጭሩ ላስረዳዎ።  ዛሬም  በሳውዲ አረቢያ መንግስት ህጋዊ እና ህገ ወጥ በተባሉ  ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽመው የከፋ በደል ተኩሶ እስከ መግደል ደረጃው ከፍ ብሏል 🙁  ምግብ ፣ ውሃ  ለታመሙ መድሐኒትና ለህጻናትና ሴቶች መጸዳጃ ቁሳ ቁስ በማይቀርብበት ሁኔታ አስሮና በጭንቅ  አፍኖ ማሰቃየቱ ከፍቷል። የሰብአዊ መብት ረገጣው በዝግ እየተፈጸመ እንደሚገኝ በሰውነታቸው ብቻ አዝነው በወህኒ ውስጥ እየተሰራ ያለው  ግፍ እና በደል ገልጸው “መንግስታችሁ አንድ ነገር ያድርግ ” ያሉኝ አንድ የሳውዲ አረቢያ የጸጥታ አስከባሪ  ሰራተኛ ብርቱ መልዕክት አድርሰውኛል። ሌላው ከወር በፊት ወደ ሳውዲ አረቢያ ተጉዘው ከነበሩት ልዑካን መካከል አንድ የኢሚግሬሽን ተወካይ በቦታው ተገኝተው በተመለከቱት ልባቸው ከመሰበሩ በላይ ስራ ለመስራት እንኳ እያወካቸው መሆኑን ሰምቻለሁ።  እናም ለእርስዎ ለሀገሬ የውጭ ጉዳይ ሚር አቶ ደመቀ መኮንን ለጉዳዩ መፍትሔ ያበጁለት ዘንድ በድጋሜ መልዕክት ላደርስዎ ተገድጃለሁ…
ክቡር አቶ ደመቀ …
  ስለ እውነት ለመናገር አሁን አሁን ” ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራዎች እየተሰሩ ነው ” ከሚባለው ዲስኩር ወረድ ብለን በሳውዲ ያለውን እውነት ሌላ ነው። መቸም በግል እንደማምነው ደግሮ ስራ አይሰራም ማለት ባይቻልም ስራ ተሰርቶ ፍሬ ከሌለው ዋጋ ቢስ ሆኖ አገኘውና እቸገራለሁ።  ለወራት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ስቃይና መከራ በቅርብ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሪያድ – ሳዑዲ ዓረቢያ ስራ አልሰራም ባልልም ውጤት ግን አላየንም።  ሌላው ቀርቶ በሳውዲ አረቢያ የሚገኘው ኢንባሲያችን በሳውዲው ንጉሰ በኩል ምህረት የተሰጠውን ምህረቱን ወደ ተግባር ገዶታል።
 በክቡር አምባሳደር ሌንጮ ባቲ የሚመራው የዲፕሎማት ቡድን የቤት ሰበራ ፣ ዝርፊያ አሰሳና ማሳደዱን አላስቆመም። የሀገሬ ዲፕሎማቶች ምህረት ተሰጠ ከተባለ መባቻ ጀምሮ  ከተለያዩ የሳውዲ ኃላፊዎች ጋር መምከሩን እና የመወያየታቸው ጉዳይ በዜና ተደጋግሞ ቢነገረንም የሚጨበጥ መፍትሔ አላመጣም። ከዚህ አንጻር የተረዳነው ጭብጥ ሀቅ ቢኖር በክቡር አምባሳደር ሌንጮ ባቲ የሚመራው ዲፕሎማት ቡድን ያገኘነው መፍትሔ የለም ‼
   በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ መልዕክተኛና የኢንባሲው የበላይ አምባሳደር ሌንጮ ባቲና ጓዶቻቸው  ለኢትዮጵያውያን ተሰጠ ብለው በአደባባይ የነገሩን ምህረት እንዲፈጸም አለመቻላቸው አሳስቦኛል ፣ አሳዝኖኛልም። የዲፕሎኘማቱ ውጤት የሌለው ድካም ስመለከተው አንድም በሳውዲ መንግስት ተከብረው የሚያቀርቡት ጥያቄ አልተሰማም አልያም  ወይም ችግሩን መፍታት አልቻሉበትም ከሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ  ‼
   ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከትዎ እርስዎን የውጭ ጉዳይ ሚር አቶ ደመቀ መኮንን
ነውና ወይ አንድም ዝቅ ብለው ይወረዱና ይመልከቱ ፣ ሲቀጥል በሳውዲ እየተገፋ ያለው እልፍ አእላፍ ዜጋዎን ችግር ይረዱና ይፍረዱ … ‼
   ክቡር አቶ ደመቀ ዛሬ ነገ ሳይሉ በአደጋ ተከቦ ለሚንገላታውን ዜጋ አዋጭ  ሁነኛ መፍትሔ ለጠፋበት እና ተስፋ ለጨለመበት ዜጋዎ ይደርሱለት  ስል በአክብሮት ተማጽኖየን አቀርባለሁ‼
  እኛም ሁላችን ስለ ተገፊው የሳውዲ መንግስት እየተገፋ  በስቃይ ፣  መከራና እንግልግት ላይ ስላለው ወገናችን ዝም አልልም ፣ ዝም አትበሉ  ‼
Filed in: Amharic