>

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአማራ ብልፅግና ፓርቲ ፣ ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ፣ ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴሃን) በጋራ የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአማራ ብልፅግና ፓርቲ ፣ ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ፣ ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴሃን) በጋራ የተሰጠ መግለጫ
ለውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ! 
ለተከበርከው የአማራ ህዝብ !

አሸባሪውና ከሃዲው ትህነግ – ህወሓት ለሶስት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያን እንደ ልቡ ሲዘርፍና ሲያደማ መኖሩ ሳይበቃው ፣ የክህደት መጨረሻውን ያሳየበትና  በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ የመላው ኢትዮጵያውያንን ልብ መስበሩን እናስታውሳለን፡፡
ይህ በእብሪት የተወጠረው  አሸባሪ ቡድን ያለፈ በደሉ ሳያንሰው በድጋሚ ሀገራችንን ወደ ብጥብጥ ፣ ደም መፋሰስና መበታተን ለመውሰድ ግልፅ የአጥፍቶ መጥፋት ጦርነት ከፍቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም ከመጤፍ ሳይቆጥር የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር ንፁሃንን እየገደለ ፣ ሴቶችን እየደፈረ ፣ ንብረት እየዘረፈና እያቃጠለ ይገኛል፡፡ ቁጥራቸው ከ300 ሺህ በላይ ዜጎችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡
አረመኔው ትህነግ ከሰሞኑ በአፋር ክልል በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ በንፁሃን አርብቶ አደሮች ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ270 በላይ ህፃናት ፣ ሴቶችና አረጋውያንን መጨፍጨፉ የጭካኔውንና የጠላትነቱን ልክ ያሳየ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአፋር ክልል መንግሥት የጥቃቱን ሰለባዎች ለማሰብ ያወጣው የሀዘን አዋጅ ተገቢና የእኛም ሀዘን መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን አፈራርሳለሁ ፣ በአማራ ህዝብ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ የተነሳውን የትህነግ እኩይ ኃይል የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ህዝባዊ ሚሊሻዎች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እዳር እየተፋለመውና በተባበረ ክንዱ እየደቆሰው ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህን ከታሪክም ከነባራዊ ሁኔታም በፍፁም ሊማርና ሊፀፀት የማይችል አረመኔ አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስና በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለመመለስ  ሲል ነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ማንሳቱ እጅግ ወቅታዊና ተገቢ እርምጃ መሆኑን እናምናለን፡፡
መንግሥት ‹‹ኢትዮጵን ለማዳን እዘምታለሁ ! የትም ፣ መቼም ፣ በማንም›› በሚል መሪ ቃል ያቀረበውን ሀገራዊ ጥሪና የአማራ ክልልን የክተት አዋጅ በመደገፍ ለተነሳችሁና የትህነግን የክህደት ጦርነት ለመመከት አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ፈጣን ምላሽ ለሰጣችሁ መላው ኢትዮጵያውያን ፣ መላው የአማራ ወጣቶች ፣ ሴቶች ፣ ምሁራን ፣ ባለሀብቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ልባዊ አድናቆታችንንና ምስጋናችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
አሁንም እኛ ለአማራ ህዝብ ፍትህና ነፃነት የምንታገል የፖለቲካ ፓርቲዎች ትህነግ እንደ ህዝብ  ያወጀብንን ሂሣብ የማወራረድ ዘመቻ የፖለቲካ ፣ የእምነት ፣ የእድሜ ፣ የጾታና ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበን እንደ ህዝብ በአንድነት ቆመን እንድንመክት ለመላው አማራ ህዝብ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በዚህ ረገድ የድርጅቶቻችን አባላትና ደጋፊዎች በህዝባችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በሚደረገው ፍትሃዊ ጦርነት የተጠየቀውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል በፍጹም አንድነትና ቁርጠኝነት በግንባር ቀደምትነት እንድትሰለፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
አሸባሪነት ይቀበራል ! ኢትዮጵያዊነት ይለመልማል !
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ! ድል ለአማራ ህዝብ !
የአማራ ብልፅግና ፓርቲ
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ፤
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን)
ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዓ.ም
Filed in: Amharic