>

የኦነግ ከህወሀት መጣመር አዲስ ቁማር ከሌለው በቀር "ሰበር" አይሆንም...!!! አሳዬ ደርቤ

የኦነግ ከህወሀት መጣመር አዲስ ቁማር ከሌለው በቀር “ሰበር” አይሆንም…!!!
አሳዬ ደርቤ

ትልቅ ሰበር ዜና ሊሆን የሚችለው ኦነግ ሸኔ እና ትሕነግ ፍቺ ቢፈጸሙ እንጂ ‹‹ሕብረት ለመመስረት ተስማሙ›› የሚለው  ጉዳይ አይደለም፡፡
ምክንያቱም ኦነግ ሼኔ ከህውሓት ጋር አጋር መሆኑን ያረጋገጠው የኦሮሞ ቄሮዎች እና ፋኖዎች ባደረጉት ትግል ትሕነግ ተባርሮ ወደ መቀሌ በገባ ማግሥት ነው፡፡
በዶክተር ዐቢይና በቲም ለማ የሚመራው ለውጥ ሳይፈተን በፊት ነው አምሳ ዓመት ሙሉ ጫካ ለጫካ ሲያንከራትቱት ከኖሩት የትሕነግ አመራሮች ጋር መቀሌ ላይ ሕብረት ፈጥሮ ከእነ ትጥቁ ከበረሃ ወደ አገር ቤት ያስገባውን ሃይል መታገል የጀመረው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ በትግል ሱስ የተለከፈው ኦነግ ሼኔ የሚያቀነቅናቸው ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ቢያገኙ እንኳን ‹‹የእኔን ጥያቄ መመለስ ያለብኝ እኔው ነኝ›› ብሎ ትግሉን ይቀጥላል እንጂ እፎይ ብሎ አይቀመጥም፡፡
ሌላው ቀርቶ የሥልጣን ጥያቄው መልስ ቢያገኝ እንኳን ሁሉም አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አራት ኪሎ መግባት ካልቻሉ ዝቅ ያለ ሥልጣን ያገኙት አመራሮች ጫካ ገብተው ቤተ-መንግሥት የገባውን ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ይታገሉታል እንጂ ድል አድርገናል ብለው አያስቡም፡፡ እንደውም ከጃል መሮ ይልቅ ጌታቸው ረዳ አራት ኪሎ ቢገባ ይመርጣሉ፡፡
ከዚያ ውጭ የሕዝብን ጥያቄ ማስመለስ ቀርቶ የድርጅታቸውን አንድነት ማስቀጠል ተስኗቸው ‹‹በእንትና የሚመራው›› በሚል መጠሪያ አራት ኦነግ እንደመሠረቱት ሁሉ ኦነግ ሼኔ ድል ሲያደርግ ሌለኛው ኦነግ ተነስቶ ወደ ትግል መግባቱ አይቀሬ ነው፡፡
በተረፈ በኦነግና በኦፊኮ መሃከል ካለው ስምምነት ይልቅ በኦነግና በትሕነግ መሃከል ያለው የጌታና የአሽከር ግንኙነት በፍቅር ላይ የተመሠረተና ረዥም ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ‹‹ሕብረት ፈጥረው አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል›› የሚለው የዛሬው ዜናም ሌላ ድብቅ ዓላማ ከሌለው በቀር “ፍቅር እስከ መቃብር” በሚል ርዕስ ‹‹በሕብረት ለመሞት ተስማምተዋል›› ተብሎ ነው መዘገብ ያለበት፡፡
ምክንያቱም የፌደራሉ እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አሸባሪው ሃይል ጠንክሮ እንዲወጣ ካልፈቀዱለት በቀር በመግለጫ ሲደመስሱትና ሲያስነሱት የኖሩትን ይሄን ሽፍታ በጦር መደምሰስ ይሳናቸዋል ብዬ አላስብም፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት የትሕነግ አሸባሪን ሙሉ ለሙሉ ለማክሰም የሚያስችል ቁርጠኝነት ካለው
ህውሓት ሲደመሰስ የኦነግና የጉምዝ ታጣቂዎችም በእራሳቸው ጊዜ አፈር የሚለብሱ ይሆናሉ፡፡ ለአሸባሪዎች ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ የተጠመዱት የሱዳን እና ግብጽ መንግሥታትም በልዩ ጥቃት ፈንታ የልዩ ጥቅም ምንጫችን መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡
ድል ለኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic