>

“የወልቃይት ጥያቄ” በምን ይመለሳል? (በፍቃዱ ኃይሉ)

“የወልቃይት ጥያቄ” በምን ይመለሳል?

በፍቃዱ ኃይሉ

በ1983 የቆመው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጦርነት እንደገና ከ30 ዓመታት በኋላ በ2013 ከቆመበት ቀጥሏል ማለት የምንችልበት ጊዜ ላይ ነን። የወልቃይት ጥያቄ የአሮጌው ጦርነት መቋጫ ሰሞን ከተጫረ ወዲህ በአዲሱ ጦርነት ማዕከላዊ አጀንዳ ሆኗል።
በ1983 የቆመው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ጦርነት እንደገና ከ30 ዓመታት በኋላ በ2013 ከቆመበት ቀጥሏል ማለት የምንችልበት ጊዜ ላይ ነን። የወልቃይት ጥያቄ የአሮጌው ጦርነት መቋጫ ሰሞን ከተጫረ ወዲህ በአዲሱ ጦርነት ማዕከላዊ አጀንዳ ሆኗል። ለመሆኑ የወልቃይት ጉዳይ ምንድን ነው? መልሱስ በአስተዳደር መካለል ብቻ የሚፈታ ወይስ መዋቅራዊ ድርድር የሚፈልግ?
ልክ የዛሬ ሦስት ዓመት፣ ነሐሴ 2008፣ የወልቃይት ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ የተቀጣጠለበት ወቅት ነበር። የፀጥታ ኃይሎች “የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ” አቅራቢ ኮሚቴ አመራር የሆኑትን ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን በቁጥጥር ሥር ሊያውሉ በእኩለ ሌሊት ሙከራ ካደረጉ በኋላ፣ ኮሎኔሉ እና ወዳጆቻቸው የተኩስ ልውውጥ በማድረግ የእስር ሙከራውን አጨናግፈውት ነበር። ከሁለት ቀን በኋላ፣ ኮሎኔሉ የክልሉ መንግሥት ለሕወሓት አሳልፎ እንዳይሰጣቸው በመደራደር እጃቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል። የዚህ ኮሚቴ ሌሎች አባላትም በተለያዩ መንገዶች ታስረው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሽብር ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር። ሁሉም የተፈቱት የ2010ሩን የኢሕአዴግን ሹም ሽር ተከትሎ በመጣው የፖለቲካ ለውጥ ክሳቸው በዐቃቤ ሕግ ተቋርጦ ነው። ዛሬ ላይ ታሪክ ተቀልብሶ የወልቃይት የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ የያኔው እስረኛ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው።
“የወልቃይት ጥያቄ
የወልቃይትን ጉዳይ በተለይም “የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ” ካነሳቸው ጥያቄዎች አንፃር በኦስትሪያ፣ የክላግንፈርት ዩኒቨርሲቲ ምሁር የሆኑት ሶንያ ጆን “የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የመሆን አቅም፦ የወልቃይት ጥያቄ እንደመፈተኛ” በሚል የሠሩት ጥናት ውስጥ በሚገባ ተዘርዝሯል። ተመራማሪዋ የኮሚቴውን አባላት ከሁለት ሺሕ ዐሥሩ ለውጥ በፊት እና በኋላ አነጋግረዋቸውም ነበር። ጥናታቸው ጉዳዩ እንዴት እንደተቀጣጠለ በጥቅሉ ከማስመልከቱም ባሻገር “የሽግግሩ” ስኬት መወሰኛ እንደሆነ ያሳያሉ።
አባላቱ መሰብሰብ የጀመሩት በነሐሴ 2007 ቢሆንም፣ መስከረም 9፣ 2008 ጎንደር ላንድማርክ ሆቴል በተደረገ እና 540 “የወልቃይት አማሮች” በተገኙበት በተደረገ ጉባዔ ላይ ባለ 20 አባላት ኮሚቴ እና መሪዎቹን መርጧል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የበላይ ተጠሪ የተደረጉት ያን ጊዜ ነው።
ኮሚቴው የክልሉ ባለሥልጣናት አልተቀበሉትም እንጂ ከትግራይ ክልል እስከ ፌዴራል መንግሥቱ (የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ) የደረሱ ዝርዝር ጥያቄዎችን አቅርቧል። ጥያቄዎቹ ከማንነት መረገጥ (በአማርኛ መማር እና መሥራት አለመቻል) ጀምሮ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መነፈግ (የእርሻ መሬት እደላ መጠኑ ለአማራ እና ትግራይ ቤተሰቦች የተለያየ መሆኑ) በአቤቱታው ተጠቅሷል።
ሕወሓት/ኢሕአዴግ በርካታ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በኃይል በማፈን በሚፈታበት መልኩ የወልቃይትንም ጉዳይ በኃይል ለማፈን መሞከሩ እና አጀንዳው መድረክ ላይ እንዳይሰማ ማድረጉ በራሱ ጥያቄውን የበለጠ እንዲወሳሰብና የሕልውናም፣ የክብርም ጥያቄ እንዲሆን አድርጎታል።
የትርክቶች ግጭት
በአንድ ወገን ወልቃይትና ዙሪያው “ምዕራብ ትግራይ ነው” የሚሉ፣ በሌላው ወገን “የአማራ [ክልል] ርስት ነው” በሚሉና በማይታረቁ የወልቃይት ጉዳይ የትርክት ጫፎች ላይ ቆመዋል። ወልቃይት የአማራ ክልል ርስት ነው የሚሉት ወገኖች ታሪክን ይጠቅሳሉ፤ አካባቢው ከ1983 በኋላ በሕወሓት ኃይል የተወሰደ ነው የሚል ትርክት አላቸው። ከዚያ በፊት አካባቢው በጎንደር ወይም ቤጌምድር ክፍለ አገር ሥር ይተዳደር ነበር። ይህንኛው ትርክት የትግራይ ድንበር ከተከዜ ወዲያ ነው የሚል መከራከሪያ ይዟል። ወልቃይት ምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ነው የሚለው ትርክት አራማጆች ደግሞ ያንን ታሪካዊ ማስረጃ ያረጀ ያፈጀ ነው ይላሉ፤ ፌዴራሊዝሙ ከመፈጠሩ በፊት አማራ የሚባል ክልል አለመኖሩን ነው የሚጠቅሱት። አማራ ክልል የአራት ክፍለ አገሮች (ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ እና ሸዋ) ከፊል ግዛቶች ተገጣጥመው የፈጠሩት ክልል ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።  ከዚህም አልፈው ወልቃይት የሕዝቡ ብዛትም (በ1999ኙ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ተመስርተው)፣ የመሬቱ ሥያሜም የየወረዳዎቹን ሥያሜ ዘርዝረው የትግራይ ነው የሚሉ ማስረጃዎችም ሲቀርቡ ይደመጣል። ለዚህ መልስ የሚሰጡት ወልቃይት የአማራ ነው የሚል ትርክት የሚያራምዱ ሰዎችም በበኩላቸው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራው ውጤት የአሰፋፈር ለውጥ ተደርጎ የመጣ ሲሆን፣ ሥያሜውም ከጊዜ በኋላ የተለወጠ ነው ባይ ናቸው፤ ጠገዴ/ፀገዴ፣ ጠለምት/ፀለምት እየተባሉ በአማርኛ/ትግርኛ እንደሚጠሩ ይታወቃል።
ጥያቄው ላይ ላዩን ብቻ ከተመለከትነው የአንድ አካባቢ እና አስተዳደር ጥያቄ ብቻ ይመስላል። ወደ ውስጥ ዘልቀን ስንመረምረው ግን የስርዓቶች ግጭት ነው። የአማራ ተወላጆች ለበርካታ ዓመታት የብሔር ፌዴራሊዝም ስርዓቱን በሙሉ ወይም በከፊል እንደማይቀበሉት ሲገልጹ ኖረዋል። የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ግን ፌዴራሊዝሙ ላይ ይሄ ነው የሚባል ቅራኔ የለም። የትርክቶቹ አስኳልም እዚህ ልዩነት ዘንድ ይገኛል።
ሕጋዊ መፍትሔ?
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ክልሎችን ሲፈጥር ሥማቸውን ይዘርዝር እንጂ የየትኛው ክልል የአስተዳደር ወሰን የት እንደሚደርስ የሚያመላክት ግልጽ መሥመር የለም። በዚህም ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በገላጋይነት ሥራ ተጠምዶ ኖሯል። በሁሉም ክልሎች መካከል እስካሁን አጥጋቢ መልስ ያላገኙ በርካታ የወሰን ጥያቄዎች አሉ።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 48/1 “የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ሥምምነት ይፈፀማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መሥማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወስናል” ይላል። ይሁን እንጂ ያኔም ይሁን አሁን በወልቃይት የሚሥማሙ ወገኖች የሉም። ወልቃይት የአማራ ነው የሚሉት ወገኖች ከአካባቢው የአማራ ተወላጆች እንዲወጡ እና የትግራይ ተወላጆች እንዲመጡ በማድረግ የአሰፋፈር ሁኔታው በሦስት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ለውጥ ተደርጎበታል ይሉ ነበር። አሁን ደግሞ በተመሳሳይ፣ አካባቢው የትግራይ አስተዳደር ክልል ነው የሚሉ ሰዎች የጦርነቱ መቀስቀስ እና አካባቢው በአማራ ክልል አስተዳደር ሥር መግባቱን ተከትሎ የተፈናቀሉ እና የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች ከመኖራቸውም ባሻገር እንዳዲስ የሰፈሩ የአማራ ተወላጆች ስላሉ ሪፈረንደም ማድረግ የማይታሰብ ነው ይላሉ።
የ2010ሩ ለውጥ እንደጀማመረ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰያሚነት የተቋቋመ “የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን” አለ። ኮሚሽኑ በሕወሓት እና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል ቅሬታ ከፈጠሩ የመጀመሪያዎቹ ጉዳይ ውስጥ ይቀመጣል። ሕወሓት መራሹ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ኮሚሽኑን “ኢ-ሕገ መንግሥታዊ” ያለው ሲሆን፣ በአስተዳደር ወሰኖችና ማንነት ጉዳይ የሚደረግ ማናቸውም ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ብቻ ነው ብሏል። በዚህም አካሔድ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማግኘት የሚቸግር ይመስላል።
በጦርነት መነጣጠቅ?
የትግራይ መንግሥት ኃያል በነበረበት ወቅት ወልቃይት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን አፍኖ አቆይቷል። አሁን ደግሞ በማዕከላዊ መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል በተነሳው ውጥረት የተቀሰቀሰውን ጦርነት አጋጣሚ ተጠቅሞ የአማራ መንግሥት ወልቃይትና ዙሪያውን በኃይል ተቆጣጥሯል። ሕወሓት እና ተዋጊ ኃይሎቹ ወደ ሰላማዊ ድርድር ለመግባት ካስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የአማራ ኃይሎች “ከምዕራብ ትግራይ መውጣት አለባቸው” የሚለውን ነው። ካልሆነ ግን በኃይል ለማስመለስ እንደሚሞክሩ ግልጽ አድርገዋል። የአማራ ክልል መንግሥትም አከባቢውን ላለመልቀቅ የሚችለውን ሁሉ የጦር ኃይል እንደሚያሰልፍ አሳውቋል። ሁኔታው ግልጽ ነው በጦርነት ያሸነፈ እየነጠቀ አካባቢውን ለተወሰነ ጊዜ ሊያስተዳድር ይችላል። ነገር ግን ዘላቂ መፍትሔ እስካልመጣ ድረስ፣ ተሸናፊው አካል አቅሙን አጠናክሮ ድጋሚ ይመጣና ይዋጋል እንጂ ሽንፈቱን አምኖና ተቀብሎ አይኖርም። ስለሆነም፣ በጦርነት መነጣጠቅም ሕዝብ ይፈጃል እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም።
መዋቅራዊ መፍትሔ?
የትግራይ እና አማራ ሕዝቦች በመሠረቱ ታሪክ፣ ባሕል፣ እንዲሁም እምነት የሚያመሳስላቸው ሕዝቦች ናቸው። አሁን የገቡበት ፖለቲካዊ ቅራኔ የአስተዳድር መዋቅር የፈጠረው ችግር ነው። አሁን ባለው የፌዴራል ስርዓት ውስጥ ወልቃይት የትግራይ ወይም የአማራ መሆኑ የራሱ የሆነ ኪሳራ እና ትርፍ ለእያንዳንዳቸው ይተዋል። ይኸውም “የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ” ውስጥ የተነሱትን ጉዳዮች በመመልከት መረዳት ይቻላል። የትምህርት እና ሥራ ቋንቋው በአስተዳዳሪው ክልል የሥራ ቋንቋ ስለሚሆን ሌላኛውን ቋንቋ ብሎም ባሕል ማሳደግ ይቸግራል። የመሬት (የሀብት) እደላውም በብሔር አድሎ ይወሰናል። ይህንን የአስተዳደር አከላሉን በመቀየር መመለስ አይቻልም፤ ችግሩ ያለውም አንድ ክልል ውስጥ ብቻ አይደለም።
የወልቃይት ጥያቄ በሕግም፣ በፖለቲካም፣ በጦርነትም የማይፈታ ጥያቄ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አስተዳደር መዋቅራዊ መገለጫ ስለሆነ ነው። የኢትዮጵያ የብሔር ፌዴራሊዝም የፈጠረው መዋቅር ዜጎች የሚተዳደሩበት አካባቢ አስተዳደር ከብሔራቸው ጋር ካልሠመረ ፍትሓዊ አስተዳደር የማያገኙበት መዋቅር ነው። የፌዴራሊዝሙ ፍልስፍና በአንድ አካባቢ ወጥ የሆነ ማንነት ያላቸው ዜጎች ሲሰፍሩ ለማስተዳደር እንጂ፣ እንደወልቃይት ያሉ ሁለት እና ከዚያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉበት ብዝኃ ብሔሮች የሰፈሩበትን አካባቢ (diverse settlement) ለማስተናገድ የሚሆን ብልሐት የለውም። በዚህ ምክንያት ዘላቂ መፍትሔ በዚህ መዋቅር ውስጥ ማግኘት ይቸግራል።
ስለሆነም ቀላል ባይመስልም፣ ብዙ ሕይወት የተከፈለበት ቢሆንም፣ ተጨማሪ ሕይወት ላለመክፈል ሲባል፣ ሁሉም ወገኖች ነፍጣቸውን አስቀምጠው መዋቅራዊ እንከኑን በድርድር ለመፍታት መወሰን አለባቸው።
Filed in: Amharic