ተስፋለም ወልደየስ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አድርገው የሾሟቸው ጄፍሪ ፌልትማን በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። ልዩ መልዕክተኛው ከነገ በስቲያ እሁድ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደሚጓዙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቃባይ ቢሮ ሐሙስ ለሊት በወጣው መግለጫ መሰረት፤ ፌልትማን በሶስቱ ሀገራት ለ10 ቀናት ያህል ቆይታ ያደርጋሉ። ልዩ መልዕክተኛው በቆይታቸው፤ ከሶስቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ በመግለጫው ተጠቅሷል። ውይይቱ፤ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ “ሰላምን የምታበረታታባቸው” እና የቀጠናውን “መረጋጋት እና ብልጽግና የምትደግፈባቸውን” ዕድሎች የተመለከተ እንደሚሆን ተገልጿል።
የፕሬዝዳንት ባይደን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ከዚህ መግለጫ መውጣት ሰዓታት አስቀድሞ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ልዩ ልዑኩ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ጥቆማ ሰጥተው ነበር። የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው በዚሁ መልዕክታቸው፤ “በዚህ ወሳኝ ወቅት፤ ፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል” ብለዋል።
ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/ 2021/4205/