>

ኢትዮጵያን አናውቃትም....!!! (ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ)

ኢትዮጵያን አናውቃትም….!!!

  ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ

ኢትዮጵያን አውቃታለሁ የሚል አላዋቂነቱን የማያውቅ ነው !
ከምናስባት ሁሉ በላይ የማትገመት ሀገር ናት!
.
እኛኮ ያልሞከርነው ክፋት የለም። እንደ ሂትለር ዘር ተኮር ስብከትን አስፋፍተናል። እንደ አይሁድ ሰውን እርቃኑን ሰቅለናል፤ በድንጋይ ወግረን ገድለናል። እንደ ስታሊን ቁልቁል ሰቅለን ገርፈናል፤ አሰቃይተናል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ሩዋንዳን ከበተነው የዘር ተኮር ጥላቻ ስብከት በላይ ተሰብከናል፤ ሶማሊያን መንግሥት አልባ ካደረገው በላይ ችግር ተፈጽሞብናል፤ ሶሪያን ካፈራረሰው በላይ ሴራና ግጭት ተከናውኖብናል። ተከፋፍለንና ተበታትነን እንድንጠፋ እስከመገንጠል መብት ተሰጥቶናል። ይህ ሁሉ ተሞክሮም ግን አለን። ይህችን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ልዩ ምሥጢር ካልሆነ በቀር ማነው የሚያኖራት?
.
ሳስበው ክፋትን ሁሉ ሞክረን ስለጨረስን አሁን መልካም ነገር የሚሞከርበት ጊዜ ላይ ነው። ካሁን በኋላ በዚህች ሀገር ላይ ያልተሞከረ አዲስ ክፋት ፈልጎ ሊያገኝ የሚችል ስለማይኖር ሁሉም በጎ በጎውን ማሰብና መሥራት መጀመሩ አይቀርም። ለኢትዮጵያ የተሻለ ጊዜ እየመጣ ነው።
“ኢትዮጵያን አውቃታለሁ” የሚል ሰው ድፍረቱ ይገርመኛል። እኔ እንደማላውቃት ነው ማውቀው። ኢትዮጵያን አናውቃትም። ፈጽሞ አላስተዋልናትም።
ኢትዮጵያ የራሷ ማንነት ያላት ሀገር ስለሆነች ከሌላ ሀገር በተቀዳ ሐሳብ ልትመራ አትችልም። ማንም ሀገር የሌለው የራሷ የሆነ ጥበብና እውቀት አላት። በድህነት መነፅር ስለምናያት ነው እንጅ… ልዩና ማንም የሚመኛት ሀገር ናት።
.
አንዳንዱ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀኛል፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የምታገለው፣ ሕዝቡ ከእኔ ጋር ነው…” ሲል ይሰማል። ምን ማለቱ ነው? የትኛው ሕዝብ? ፌስቡክ ላይ ያለው? ሚዲያ ያለው? ፖለቲከኛው? ሃይማኖተኛው? ወይስ የቱ? መለየት አለበት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀውም የሚሰማውም ሰው ያለ አይመስለኝም።
Filed in: Amharic