>

ለአሸባሪው ህወሓት የቀረበ ምስጋና...!!! ( ኢ.ፕ.ድ)

ለአሸባሪው ህወሓት የቀረበ ምስጋና…!!!

ኢ.ፕ.ድ

በአንዳንዶቻችን ዘንድ ምስጋና ለሚገባው ምስጋናን መቸር ልምዳችን ሆኖ አያውቅም፡፡ ነገር ግን እነሆ! ዛሬ አንድ ባለውለታን ልናመሰግን ነው፡፡ ይህ ባለውለታችን በበጎ ሰው ሽልማት ላይ ታጭቶ አያውቅም፡፡ ሌሎች መሰል አካላት በጎ አድራጊውን ለሰናይ ድርጊትህ ሁሉ ተገቢ ምስጋናና አክብሮት ያሻሃል አላሉትም፡፡

እኛ ግን ባለውለታችንን ፈጽሞ አንረሳም፡፡ ይህ ባለውለታችን በልባችን ስፍራ አግኝቶ በደማቅ ቀለማት መመዝገቡ ያለምክንያት አይደለም፡፡ አዎ! ስለሀገርና ወገን፣ በታሪካችን ላይ አውቆም ባይሆን ሳያውቅ ደማቅ አሻራውን አኑሯል፡፡ ያልታሰበ ሲሳይ፣ ያልተገመተ በረከት አውርዶ የታሪክ መዝገብ ቀይሯል፡፡ አዎ! ምስጋናና አክብሮት ለድንገቴው ወዳጃችን ይሁን ፡፡

ምስጋናችንን ከአክብሮት ጋር ስንጀምር የወዳጃችንን ማንነት መዘንጋት የለብንም፡፡ በእርግጥ ይህ እኛ ወዳጅ የምንለው አካል ለሀገራችን ኢትዮጵያ ግንባር ቀደሙ ጠላት ነው፡፡ ይህ መርዛም፤ እሾሃማ ጠላት ለአገራችን በህዝቦቿ ህልውና በማንነቷ ክብር እንቅፋት ሆኖ ከፊቷ ሲጋረጥ ቆይቷል፡፡ አገር ለማፍረስና ህዝብ ለመበተን እንቅልፍና ሰላም ኖሮት አያውቅም፡፡

ይህ ወዳጅ መሳይ ጠላት እስከ ዛሬ በነበረው ታሪኩ አስነዋሪ ታሪኮችን ሲፈጽም ኖሯል፡፡ ለሃያ ሰባት ዓመታት ተቆናጦ በያዘው ስልጣን ክቡር የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ በእጅጉ አዋርዷል። የአብሮነት ታሪኩን ቀይሮ ፣ ከፋፍሎ ለጥላቻና ለዘር ልዩነት ዳርጓናል፡፡

የህወሓት ሴረኛ ቡድን ስልጣን በያዘ ማግስት የዘረጋው የክፋት ወጥመድ ብዘዎችን ጠልፎ ጥሏል፡፡ ለእድሜው መራዘም ያሰጉኛል ያላቸውን አገር ወዳዶች በሰላ ሰይፉ ቆርጦ አስወግዷል፡፡

ሴረኛው የህወሓት ቡድን የስልጣን ቁንጮውን ላለማስነካት በፈጸማቸው ኢ – ሰብአዊ ተግባራት ንጹሃን እንደቅጠል ረግፈዋል፡፡ በርካቶች ቤተሰብ በትነው ለአስከፊ ስደት ተዳርገዋል፡፡ ለምን? ያሉና ድርጊቱን ሊቃወሙ ያሰቡ ዜጎች በአደባባይ በግፍ ተገድለዋል፡፡

ይህ አገር አጥፊ ቡድን በብሄር ብሄረሰብ ከፋፍለህ ግዛ ስልት ህዝብ፣ ከህዝብ እንዳይተማመን፣ መልካም አብሮነቱ እንዳይቀጥል ሌት ተቀን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ባይሳካለትም ታሪክ እንዲጠፋ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲደበዝዝ፣ ትውልድ እንዳይተማመን የማድረግ ሩጫው እረፍት የለሽ ነበር፡፡

ለእሱና ለመሰሎቹ ምቾት፣ ኢትዮጵያንና መላ ዜጎቿን በቁም እስከመዝረፍ ፣ የደረሰው ይህ ራስ ወዳድ ቡድን ለኢትዮጵያ ህዝብ ድህነትን በማውረስ የሀሰት ካባውን ተከናንቦ አገርን ሲዋሽና ሲቀጥፍ ኖሯል፡፡ ዛሬ ላይ እውነት የማይመስለው አስከፊ ታሪክ በለውጥ ናፋቂዎች እውን ሆኗል፡፡ አሁን የክፋት ለበቁ ይብቃን ያሉ፣ ድንቅ ጀግኖች በድንገቴው ለውጥ የስልጣን መንበሩን ከእጁ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ተረክበዋል፡፡ የትናንቱ የጨለማ ዘመን የመቋጨቱን እውነት እስከዛሬ ያላመነው ሰው በላው ህወሓት ግን፤ አፈሩን አራግፎ በሙት መንፈስ አገር ማመሱን ቀጥሏል፡፡

ነገሩ ሁሉ ‹‹ላታመልጭኝ አታሩጭኝ ›› ቢሆንም ሴረኛው የህወሓት ቡድን ግን ላይሰበሩ በቀጨጩ እግሮቹ፣ እየተንከላወሰ ዳዴ ማለቱን ይዟል፡፡ ትናንት ደም መጠጣት የለመደ ማንነቱ ዛሬ ከዋሻና ጉድጓድ አውጥቶ የድሃ ልጆችን ህይወት እያሳጨደ ነው። የፈሪ ዱላ ስልቱም በትግራይ ህጻናት ሞት የመኖር ተስፋውን ለመቋጠር፤ የመቃብር እስትንፋሱን ለመቀጠል ይንፈራገጥ ጀምሯል፡፡ ይህ ህፃናትን ለጦርነት የማሰማራት ተግባሩ ታሪክ ሆኖ በዓለም አደባባይ በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ታትሞ ተነቧል፡፡

እኛ ግን ዛሬ ‹‹ጁንታው›› እያልን ለምንጠራው ቡድን ከመሞቱና እስከወዲያኛው በመጥፎ ታሪክነት መቃብር ከመውረዱ በፊት ታላቅ ምስጋና ልንቸረው ወደናል፡፡ አሁን ለሴረኛው፣ ለከፋፋዩ፣ ለጨካኙ የህወሓት ቡድን ምስጋና የማቅረቢያ ጊዜው ደርሷል፡፡ በእርግጥ ሞት የቀረበው ቁስለኛ አካሉ፣ በጣር ላይ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ለንስሀ የሚተርፍ ጊዜ፣ ለጸጸት የሚበቃ አፍታ እንደሌለውም እንረዳለን፡፡ ተስፋ የለሽ ሩጫው ከጠዋቷ ጸሀይ፣ ከነገዋ ጀንበር ፣ እንደማያገናኘውም እርግጠኞች ነን፡፡ ያም ሆኖ ግን ከእኛ ዘንድ የሚቸረውን ታላቅ ምስጋና እንዲቀበለን ‹‹እነሆ!›› ብለነዋል፡፡

ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን በህወሓት የመቃብር አድራሻ በተጻፈ መልዕክት ምስጋናችንን ስናቀርብ ታላቅ ኩራት ይሰማናል። ‹‹ዕድሜ ለእሱ›› ይሉት አባባል ጁንታው ለሚገኝበት አቋም የሚመጥን ባይሆንም እኛ ግን ደግመን ደጋግመን እድሜ ለጁንታው ማለታችንን ቀጥለናል፡፡

አዎ! ‹‹እድሜ ለጁንታው›› ይሁንና ዛሬ እሱ ለተንኮል ሲል የጫረው እሳት አንድነታችንን አቀጣጥሏል፡፡ ይህ በቀላሉ የማይቀዘቅዝ ትኩሳት እንደ ፍም ተጋግሞ፣ ጠላቶቹን የአመድ ክምር ማድረጉን አላቋረጠም፡፡ አሁን የጁንታው የተንኮል ሰደድ አቅጣጫው ተቀይሯል፡፡ አይጠፌው ወላፈን ሲንቀለቀል ቀድሞ ያቀጣጠለውን ሴረኛ እያጋየ፣ በጫረው እሳት እያነደደ ጭምር ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያዊነት በጁንታው የተንኮል እሳት ብርሃኑ ደምቋል፡፡ አሁንም ምስጋና ለጁንታው ይሁንና የኢትዮጵያዊነት ህብር ፣ የአገር ሰንደቅ ክብር፣ የዜግነት ሞገስ፣ ከፍ ባለ ማማ መታየት ጀምሯል፡፡

ትናንት ጁንታው አገር ለማፍረስ፣ ወገን ለመበተን፣ በፈጣን የሩጫ ትራክ ላይ ነበር፡፡ አጋር ጀግኖችን ገድሎ፣ በክብራቸው ተደራድሮ ክህደቱን በተግባር አሳይቷል፡፡ ይህ አሳፋሪ ድርጊቱ ያበገናቸው፣ የንጹሃን ደም የጠራቸው፣ ብዙሃን ግን ዛሬን ዝም አላሉም፡፡

አሁንም ምስጋና ለእሱ ይሁንና ይህ ማንነቱ የገባቸው፣ ድርጊቱን የተጸየፉ እልፎች፣ ታሪክ ሊቀይሩ፣ የጋራ ጠላታቸውን ሊያዳባዩ ሃይላቸው ተጣምሯል፡፡ ዛሬ ጁንታው የቀደደው የተንኮል አጥር ሁሉን በአንድ አሰባስቦ፤ ልዩነትን አስወግዷል። አማራው፣ ኦሮሞው፣ ደቡቡ፣ ቤንሻንጉል፣ ሶማሌ እና አፋር ሁሉም መቃቃርን አርቆ በጋራ ስሜትና አብሮነት ኢትዮጵያን ከታላቅ ከፍታ ለመስቀል በአንድነት ዘምቷል፡፡

ጁንታው ትናንት በሴራው የሸረበው የዘር፣ ሃይማኖት፣ የብሄርና ቋንቋ ልዩነት ትርጉሙ ለበጎ ሆኖ ዓላማውን ለይቷል። አሁን በልዩነት የሚፈረጅ፣ በእኔ እበልጥ በሽታ የሚታመም የለም፡፡ የአንድነት ህክምናው ሁሉን ፈውሶ ለሰላማዊ ትግል ፣ ዘብ አቁሟል፡፡ ዳግም ምስጋናውን ጁንታው ይውሰድና ይህ ሁሉ አውነት ፍንትው ለማለቱ ምክንያት እሱው ሆኗል፡፡

እነሆ! ለጁንታው የምናቀርበው ምስጋና ይቀጥላል፡፡ እሱም በማምሻ እድሜው፣ በመሰናበቻ ጊዜው በሰመመን ይሰማናል፡፡ ሌላውን ታላቅ ምስጋና ለመቸር ደግሞ የቀደመ ሴራውን ማስታወስ ግድ እያለን ነው፡፡ የኦነግና የህውሓትን ያልፈረሰ ጋብቻ፡፡

ከሰሞኑ ሁለቱ ተጣማሪዎች በግልጽ እንዳወጁት በእጮኝነት የከረመ ወዳጅነታቸውን አድሰዋል፡፡ ይህ ታሪክ መለስ ብሎ ሲመረመርም አስቀድሞ በድብቅ የተመሰረተ ጋብቻ እንደነበራቸው የሚያጋልጥ ሆኗል፡፡ እኛም እስከዛሬ በሀገር ማፍረስ ድብቅ ሴራ አብሮነታቸውን ላሳየን ጁንታው ከወገባችን ዝቅ ብለን ምስጋናውን ችረናል፡፡

ይህ ጁንታ ይሉት ሴረኛ የእባብ ገላውን ቀይሮ ማንነቱን ባያሳየን ዛሬ ሚስጥር ተግባሩን ባላወቅን ነበር፡፡ እሱ እስከዛሬ የዋጠው ቁንጣን ሆኖት አላስቆም፣ አላስቀምጥ ባይለው ኖሮ እኛ በርሃብ አለንጋ መገረፋችን በቀጠለ ፣ መዘረፋችን ባላቆመ ነበር፡፡ ጁንታው ስልጣኑን በይሁንታ ለቆ በእስስት ባህረይው ቢቀጥል ኖሮ አሁን በድብቅ ሴራው፣ በተንኮል መረቡ በተጠለፍን ነበር፡፡

ጁንታው ሆይ! እንኳንም ወጋኸን፣ እንኳንም ገደልከን፣ እንኳንም አገር ለመሸጥ ሞከርክ፡፡ ይህ ባይሆን እድሜ ጠገብ ሴራህን፣ ህዝብ ማጥፊያ መርዝህን መቼም አናውቅም ነበር፡፡

አሁን የጁንታ ህወሓት ማንነትን አውቀን ከስሩ ልንነቅል ነፍጥ አንስተናል፡፡ የአንድነት ክንዳችን በርትቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን አብቧል፡፡ የጋራ ጠላታችንን አፈር ምሰን ልንቀብረው ከመቃብሩ ጫፍ ቆመናል፡፡ በህይወት ታሪኩ መቋጫ ደግመን ደጋግመን ምስጋናን ችረናል፡፡ ‹‹ጁንታ ሆይ! ስላደረከው እኩይ ተግባራት ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ‹‹ነፍስ ይማር ››

 ከአትጠገብ

Filed in: Amharic