>

‹‹መቀሌን የለቀቅነው የቡድኑ ስትራቴጂው ስልት ስለሆነ ነው›› -ጌታቸው ረዳ

‹‹መቀሌን የለቀቅነው የቡድኑ ስትራቴጂው ስልት ስለሆነ ነው››

ጌታቸው ረዳ

 

እየሩስ አበራ


 የሰሞኑን የአማጺው ቡድን አፈቀላጤ የጌታቸው ረዳ ንግግር ላጤነው አፍ ሲያመልጥ – አይነት ነው። እርግጥ ነው! ይህ ሰው ከአንደበቱ የሚወጣውን ንግግር በውል ያውቀዋል ለማለት ባያስደፈርም ፤ ከመናገር ግን ቦዝኖ አያውቅም፡፡ አሸባሪው ህወሓት በመንበረ ስልጣን ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ አፈቀላጤ የሆነው ይህ ሰው በሚያደርገው የሀሰት ዲስኩርና ዋሾነት የሚታወቅ ነው፡፡ ዘላባጅ የሚሉት አይነት ሰው ነው፡፡

የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ከአዲስ አበባ ሸሸቶ መቀሌ በከተመበት ጊዜ በትግራይ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ እያለ የተለመደውን የሀሰት ዲስኮሩ መደስኮር ልማዱ ሆኖ ነበር ፡፡ የሰውዬው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ‹‹ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ›› እንዲሉት አይነት ነው፡፡ በፍጹም ያልሆነና ያልተፈጠረን ነገር በእውን የተደረገ በማስመሰል ፤ እውነት የሆነን ደግሞ ፍጹም ውሸት የሆነ አድርጎ በማቅረብ የተካነ መሆኑን በተደጋጋሚ በሚያደርጋቸው ንግግሮቹ ማየት ችለናል፡፡

የአሸባሪው የጥፋት ኃይሎች ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባ በመውጋት የፈጸመውን ክህደት ከምንም ሳይቆጥር እንደውም በድል የተገኘ የጀግና ገድል ይመስል እያወደሰ የፈጸሙትን ወንጀል እንደ ጀብዱ በመቁጠር አበጀን እያለ ሲያወራ መታዘባችን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ሰውዬው እኮ ማንም ሳይጠይቀው በራሱ አንደበት በትግራይ ቴሌቪዥን ብቅ ብሎ የሰሜን እዝ ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውና የወሰዱት እርምጃ ትክክል እንደሆነ በልበ ሙሉነት አረጋግጦልናል። የኢትዮጵያን ዓይን እያወጡ፤ ወንጀል እየሰሩ በአደባባይ እንደ ጀብዱ ማውራት ይሉሃል ይህ ነው!፡፡ ‹‹ጦርነት ባህላዊ ጫወታችን ነው፡፡ ጦርነት አዋቂ ከኛ በስተቀር ላሳር ! ማን ወንድ ፊታችን ቆሞ ሊመክተን አይችልም…›› እያለ ቱሪ ናፋውን እየነፋ በዲስኮሮቹ የጆሮአችን ታምቡር ሲበጥስ ቆይቷል፡፡ ሰሚ የለሽ ሆነ እንጂ!

በተመሳሳይ የተናገረውን ወዲያውኑ የሚረሳው አፈቀላጤ፤ የጥፋት ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ሸፍጥ ወደ ጎን በመተው ለሁሉም ጉዳይ ተጠያቂ መንግሥት መሆኑን ይናገራል፡፡ ሰውዬው በተደጋጋሚ ከአፉ የማይጠፋውን የአብይ መንግሥት እየዋሸ ነው ፤ እውነቱ እኛ ጋ ነው የሚል ማስረጃ የለሽ አሰልቺ ንግግሩን በቅርቡ በቢቢሲ ሀርድ ቶክ ላይም ደግሞታል፡፡ አፈቀላጤው የለመደውን ነጭ በነጭ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ሲግተን የኖረ መሆኑ እንዴት በአንዴ መርሳት ቻለ ብለን በትዝብት መዝገብ ላይ ማስፈራችን አልቀረም፡፡ ወይስ ተመልካች የማገናዘብ ችሎታ የለውም ከሚል አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጭፍን አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡ በተለይ በሀርድ ቶኩ ላይ ከጋዜጠኛ ለሚቀርበለት ጥያቄ አብይ የሚለውን ስም ከመደጋገም በዘለለ ከመንተባተብ እና ነገሮችን ከመደጋገም በስተቀር ምንም እርባና ያለው ነገር ማንሳት አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ንግግሮቹ እውነት እየተናነቀው እውነቱ ድንገት እንዳያመልጠው ያደረበትን ስጋት ያሳብቃሉና፡፡

ሰውዬው እኮ ! መከላከያ ሠራዊት የማያዳግም እርምጃ እየወሰደባቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው፤ ከመቀሌ እግሬ አወጪኝ ብለው እየፈረጠጡ ባሉበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት እንኳን ውሸት ከአፉ አልጠፋም። ለሮይተር እንዲህ ሲል ተደምጧል ‹‹መቀሌን የለቀቅነው የቡድኑ ስትራቴጂው ስልት ስለሆነ ነው›› በማለት ነጭ ውሸት ዋሽቷል፡፡ ጌታቸው እንዳለው ለስትራቴጂያዊ ስልት መቀሌን ለቀው ከሆነ ዝንጀሮ ከማይገባበት ገደል እና እልም ካለ በረሃ ውስጥ መንከራተታቸው ለምን ይሆን? ጉድ እኮ ነው! ከሞት አፋፍ መትረፋቸውን ረስተውት ይሆን፡፡ ጌታቸው አይነኬዎቹን የጃጁ ሸማግሌዎቻቸው አጥተው፤ የሞትን በር አንኳኩቶ እሱን ጨምሮ ጥቂት ርዝራዥ በተአምር መትረፋቸውን ለምን አልነገረንም፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጥፋት ኃይሉን አፈር ከድቤ እየደባለቀ ባለበት ወቅት ከሞት አፋፍ ላይ ቆሞ ከነበረበት የቀበሮ ጉዱጓድ ውስጥ ሆኖ ባልሞተችው ምላሱ የደረሱልን ጥሪ በከፍተኛ ጽምፅ እንደ ገደል ማሚቱ ሲያስተጋባ ነበር፡፡ አልሞት ባይ ተጋዳዩ በደጋፊዎቹ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በኩል እራሱ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመውን በደል ለመንግሥት በመስጠት ‹‹የትግራይ ህዝብ ተርቧል ፤ የሰብዓዊ እርዳታ እየደረሰለት አይደለም›› እያለ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የደረሱልኝ ጥሪ ሲያሰማና ሲወተውት ቆይቷል፡፡

ሆኖም ግን ሰውዬው አንዳንዴም ሳያስበው ቢሆን የሚናገራቸው አስገራሚ ንግግሮችም እንዳሉ መመልከት እንችላለን፡፡ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ መንግሥት የተኩስ አቁም በማድረግ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ከትግራይ ክልል መከላከያ ሠራዊት እንዲወጣ ማድረጉን የገለጸበት ወቅት ነበር። አማጺው ቡድን ግን በነጻነት ሜዳ እንደፈለገ እንዲሆን የተፈቀደለት ያህል መቀሌ ለመግባት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡

አሸባሪው ሕወሓት መቀሌ በረገጠ ማግስት ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያሰማ ከርሟል፡፡ ክፋት የባህሪው መገለጫ ነውና መንግሥት ተኩስ አቁም ቢያደርግ እነሱ ተኩስ አቁም ብሎ ነገር እንደማይመቻቸው አረጋግጧል፡፡ የህዝብ መከራና ሰቆቃ ከመጤፍ ሳይቆጠር ወደሚመኘው ጦርነት ደግሞ ለመግባት ያለውን የጦርነት ጥማት በፍጥነት ለማሳካት እንደሚፈልግ ተናግሮ ነበር፡፡ አፈቀላጤው በትግራይ ሚዲያ ሀውስ በኩል ‹‹ጦርነት አልቋል የሚባለው ምኞት እንደሆነ ፣ጦርነት ያልተካሄደበት ቀን እስካሁን እንደሌለ ፣ ጦርነት አልቋል የሚባለው ተረት ነው›› በማለት ለጦርነነት ያለውን ጥማት አሳይቷል፡፡ እንደ ሰውዬው ከሆነ የጀመሩት ጦርነቱ እነሱ የሚፈልጉት እስኪፈጸም ድረስ ያለቀው ሰው አልቆ ፤ የጠፋው ንብረት ጠፍቶ እስከመጨረሻ ምዕራፍ የሚቀጥል ነው፡፡ አክሎም ኢትዮጵያ ለማፍረስ ሲኦል መውረድ ካለብን እንወርዳለን ሲልም ተደምጧል፡፡

ይህንን ምኞታቸውን ለማሳካት መከላከያ ትግራይን ለቆ ሲወጣ መከላከያን አሸንፈው መቀሌን መቆጣጣራቸው እና ቀጣይ ተግባራቸው ምን እንደሆነ ሳይቀር ተናገሯል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የአየር መቃወሚያ እንደሌላቸው እየታወቀ የጦር አውሮፕላን መትተን ጥለናል የሚል ዲስኩርም ከአቶ ጌታቸው ረዳ አንደበትም አዳምጠናል፡፡

በአንደበቱ ዓለምን ማካለል የማይሰለቸው ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገረው ‹‹ወደ አማራ ክልል መሄድ ካለብን እንሄዳለን፤ ወደ ኤርትራ መዝመት ካለብን እናደርገዋለን›› ብሎ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የተሰጣቸው የጥሞና ጊዜ ትናንትና በፈጸሙት ተግባር ተጸጽተው ልብ የሚገዙበት እንደሚሆን ታስቢ ተደርጎ ነበር፡፡ የሞትን ደጅ ረግጦ የተመለሰ ቀሪ ህይወቱን በንሰሐ በመመለስ ለመኖር ይጓጓል ተብሎ ተማኖ ነው፡፡ ነገሩ ተገላቢጦሽ ሆነ እርፍ አለ እንጂ! ‹‹ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ›› እንዲሉት ሆኖ ሰውዬው የኢትዮጵያን ሠራዊት በሙሉ በመደምሰስ መቀሌ መያዙን ሲለፍፍ ተደምጧል፡፡ኧረ ምን ይሄ ብቻ! እንዲያውም ከፈለጉ የናፈቀቻቸው አዲስአበባ ድረስ ያለምንም ከልካይ ሰተት ብሎ እንደሚገቡ ሁሉ ይደሰኩራል፡፡ የአፈቀላጤው ንግግር እጅን በመዳፍ ላይ አስደፍቶ የሚያስቅ፤ ሰዎቹ የቁም ቅዠት ውስጥ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

የተንኮልና የሴራ ልክፍት ያለበት የጥፋት ቡድኑ ውሎ ሳያደር ትንኮሳ በአማራና በአፋር ክልል ጀምሮ እውን አደረገ፡፡ የንጹኃን ደም በማፍሰስ፤ ሀብት ንብረት በመዝረፍ በርካታ ሰዎች ከቦታቸው እንዲፈናቀሉ ጦስ ሆነ ፡፡ ሲያቀብጠውም ‹‹ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን›› በሚል አፉን አዳልጦት ዛሬ አማራ ህወሓት ላይ ሂሳቡን እንዲያወራርድ መንገዱን ከፍቶለታል፡፡

መቼም ጆሮ አይሰማው የለም እንዲሉት ሆኖ በጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ ንጹሃን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ አልበቃ ብሎት በድጋሚ ነሐሴ 5 ቀን 2013ዓ.ም በአፋር ክልል በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸመ፡፡ በጋሊኮማ በንፁሃን ላይ ያደረሰው እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ 100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ዜጎች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ በታሪክ የማይሽረው ጥቁር ጠባሳ መዝገብ ላይ ሰፍሯል፡፡

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮ እንደገለጹት፤ በጋሊኮማ 107 ህፃናትን፣ 89 ሴቶችን እና 44 አዛውንቶችን ህይወት የቀጠፈውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የፈጸመው አሸባሪው ህወሓት ነው፡፡ የህወሓት ጁንታ ድንገት በከፈተው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ንፁሃን አርብቶ አደሮች መገደላቸውና መቁሰላቸው እንዲሁም በመጋዝን የነበረ ለ31ሺ ለችግረኞች የዕለት የአስቸኳይ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ማውደውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አርፎ የማይቀመጠው አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልል በንፁሃን ላይ ባስከተለው ቀውስ ከ300ሺ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፡፡

የአማራና የአፋርን ክልል በኩል ያደረገው ትንኮሳ በተወሰደበት እርምጃ መደምሰሱ ግራ ቢገባው ምን ያለ ይመስላችኋል፡፡ ‹‹የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም›› እንዲሉት አይነት የዓመቱን ምርጥ ቀልድ ቀልደዋል። ‹‹አፋር ላይ ኦፕሬሽን ልንሰራ ሄደን የአፋር ህዝብ አላሳልፍ ሲለን እኛ ፀባችን ከእናንተ ጋር አይደለም ከአብይ ሰራዊት ጋር ነው ብለን ስናስረዳቸው ሊሰሙን ባለመቻላቸው ከአፋር ወንድም ጋር ላለመቀያየም ብለን ዘመቻውን ሰርዘን ተመልሰናል›› ብሎ አስገራሚ ንግግር ተናግሯል፡፡ ከዚህ በላይ አፋር ህዝብን ምን ሊያደርጉት እንደሚችሉ ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ነው፡፡

ለትግራይ ህዝብ ሰቆቃና መከራ የተፈጠሩት እነጌታቸው ህጻናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች ወደ ጦርነት እንዲሰለፉ ሲያስገድዱ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ እንደሰው ተፈጥረው ሰብዓዊነት ብሎ ነገር የማያውቁ የትግራይ እናቶችን ሰቃይና መከራ ወደ ጎን በመተው ከጉያቸው ልጆቻቸውን ነጥቀው ለጦርነት መማገዳቸውን እንደ ትልቅ ገድል አድርገው የሚያወሩ ናቸው። የራሳቸውን ልጆች በውጭ ሀገራት እያንደላቀቁ፣ ደሃው የትግራይ ህዝብ ልጅ ወደ ጦርነት በመማገድ የራሳቸውን ዕድሜ ለማራዘም እየጣሩ ነው፡፡

እነ አፈቀላጤው ጌታቸው እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናትና ወጣቶች በአደንዛዥ እጽ አስክረው ወደ ጦርነት በመማገድ በትግራይ እናቶች እንባ ይሳለቃሉ፡፡ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ለአፈቀላጤው እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናትን በጦርነት ለምን ታሰልፋላችሁ ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ የቡድኑን ደንታ ቢስ መሆን የሚያሳይ ነው። ‹‹እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናት ቡድኑን ለመቀላቀል ሲመጡ በቂ የሆነና፣ በርካታ ቁጥር ያለው ተዋጊ አለን ብለን ወደ ቤታቸውም እንመልሳቸዋለን። በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንዶቹ በግድ ይቀላቀላሉ፤ ድጋፋቸውን ለማሳየት የጦር መሳሪያም ሆነ ማንኛውንም ነገር ይዘው ከታዩም አንድ ሰው ፎቶ ያነሳቸውና ህፃናት ወታደሮች አሰለፉ እንባላለን›› እያለ ይቀልዳል፡፡ ይህንን እንግዲህ ምን ያህል ሰብዓዊነት ብሎ ነገር እንደማያውቁ ማሳያ ነው፡፡ ሀገር ያወቀውን ፀሀይ የሞቀውን እውነት ህዝቡ ለማደናገር የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡ የትግራይ እናቶች እንባ እሳት ሆኖ ይፍጀው እንጂ ሌላማ ምን ይባላል፡፡

በዓለም አቀፉ የወንጀል ህግ ላይ የተደነገገው እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረስ ህጻናት እያሰለፉ በዓለም አቀፉ ማህበረስብ ዘንድ በዝምታ መታለፉ እኛ እጅግ ቢገርመንም ሰውዬ ግን ገና ከጅምሩ የዓለም አቀፉ ማህረሰብ ከአሸባሪው ጋር መቆሙን ሲናገር ሰምተናል፡፡ አፈቀላጤው እንዲህ ብሎ ነበር ‹‹ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በምንፈልገው ደረጃ እየተገናኘን ነው ማለት አንችልም ፤ መገናኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ ውሱን የኮሙኒኬሽን አቅም ግን ከደጋፊዎቻችን ጋር ፤ በርካታ መንግስታት በርካታ የዓለም ተቋማት ድጋፍ እንዳለን እናውቃለን›› በማለት ያለውን እውነታ ፍንትው አድርጎ ለቢቢሲ ተናግሯል። ለዚህም ነው ምዕራባውያኑ ህወሓት የፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት እያዩ በዝምታ ለማለፍ የሚሞክሩት፤ በተቃራኒው ደግሞ እነሱ የተነኩ ሲመስላቸው ከያሉበት ይንጫጫሉ፡፡

ሰውዬው ለእነዚሁ ደጋፊዎቻቸው ባለፈው ሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም በቲውተር ገጽ በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመደራደር ያወጣቸው ሰባት ነጥቦች ነበሩ፡፡ በዚህም ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቅል አይነት ጠብ አጫሪነት የተሞላባቸውን ጥያቄዎች ማቅረቡ የሚታወስ ነው። አፈቀላጤው በአንድ በኩል አሁን በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ቅቡልነት የሌለው ነው እያለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግራይ ክልል ተቋርጠው የቆዩ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና እና የንግድ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት መጀመር እንዳለባቸው ይወተውታል። እንደገናም የ2013 ዓ.ም. እና የ2014 ዓ.ም በጀት በፍጥነት መለቀቅ እንዳለበትና የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ለሁሉም አይነት የትራንስፖርት አማራጮች በርካታ መተላለፊያ ኮሪደሮች ክፍት መደረግ አለባቸው ሲል ይጠይቃል፡፡ በአንድ በኩል ኮሪደር ይከፈትልን የሚል ተማጽኖ እያቀረበ በሌላ በኩል ደግሞ ያለማንም ከልካይ አዲስ አበባ መሰስ ብሎ እንደሚገባ ሲደሰኩር ተሰምቷል፡፡ አዲስ አበባ መሰስ ብሎ መግባት ከቻለ ኮሪደር ክፈቱልን ብሎ መለማመጡን ምን አመጣው ፡፡

አሁን ላይ መላው የጠፋው ቡድን አሁን ደግሞ አይን ፍጥጥ፣ ጥርስ ግጥጥ የሚያደርግ ውርጅብኝ እየወረደበት መሆኑን አምኗል፡፡ የኢትዮጵያውያን አንድነት ያስፈራው የአሸባሪው አፈቀላጤ አብይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ደንታ የለሽ ነው፡፡ የአማራ ፣ የኦሮሚያ እና የተለያዩ የልዩ ሃይሎች በሙሉ በሚባል ደረጃ ገበሬዎች የነበሩ እና በጣም ኋላ ቀር መሳሪያ የታጠቁ ስብስቦች ናቸው ብሎ ለመዝለፍ ቃጥቶታል፡፡ እነሱ ኢትዮጵያን ለማፈራስ የያዙት ስትራቴጂ በአንድ ጀንበር መምከኑ ተስፋ ያስቆረጣቸው ይመስላል፡፡ የህዝቡን በነቂስ ወጥቶ ለዘመቻው መትመም ክፉኛ ስላስደነገጣቸውም አፈቀላጤ እግዚኦ ተከበናል እያለ የድረሱልኝ ጩኸቱን በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡

ሰውዬው እነሱ ሲሸረሽሩትና ሲከፋፈሉት የኖሩት ኢትዮጵያዊነት መኖሩን ይጠራጠር ነበር፡፡ ሆኖም ግን አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነት ማዕበል እንዲህ ሲገነፍል መመልከቱ ደግሞ መሬት ተከፍታ አትውጠው ሆኖበት ግር ቢለው የሚናገረው ጠፍቶታል፡፡ እናም እርስ በእርሱ የተሳከረ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እየነዛ እድሜ ለማራዘም እየሞከረ ይገኛል፡፡ በተለይም እዚህ ደርስናል፤ ይህንን ከተማ ተቆጣጥረነናል፤ አዲስ አበባ ልንገባ ጥቂት ቀርቶናል የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመልቀቅ ደጋፊዎቻቸው በማይጨጥ ተስፋ ውስጥ እንዲኖሩ እያደረገ ነው፡፡

የተበታተነች የመሰለቻቸው ኢትዮጵያ ዛሬ በልጆቿ አንድነት የተባባረ ክንድ አሸበባሪ ቡድኑን ለመቅበር ጫፍ ደርሳለች፡፡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለመው አሸባሪ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ማይቀርለት መቀመቅ መውረጃው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ዛሬ ትናንት አይደለምና በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሁል ጊዜ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ አሁን እውነት ፍንትው ብላ ወጥታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከመፍረሷ በፊት አሸባሪው ይፈርሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት ‹‹እኛ እንፈርሳለን እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም ›› ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፡፡

 

Filed in: Amharic