“የሱዳን መንግስት ጠ/ሚር አብይ ከሰጠው መሬት ለቆ አይወጣም!”
የሱዳን መሪዎች ከኢትዮጵያ የወሰዷቸው ቦታዎችን ትናንት ጎበኙ። የሱዳን ጠቅላይ ምክር ቤት መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ ቡርሃን እንዲሁም ጠቅላይ ሚንሥትር አብዳላ ሐምዶክ አል ፋሻጋ በተባለው ለም አካባቢ ተገኝተው የልማት መርሃ ግብሮችን ማስመረቃቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።
አል ፋሽጋ የሱዳን ጦር በቅርቡ ከኢትዮጵያ በኃይል ያስመለሳቸው ይዞታዎች መሆናቸውን የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤቱ ገልጧል።
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ባለው ጦርነት አጋጣሚውን በመጠቀም ሱዳን ወረራ መፈጸሟን ጉዳዩ ከጦርነት ይልቅ በድርድር መፈታት እንዳለበት በተደጋጋሚ ስትገልጥ ቆይታለች።
የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ በወሰደው መሬት ዋድ ኩሊ በተባለው መንደር የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር አብዳላ ሐምዶክ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር «መልካም ትስስር» ለማድረግ ጥረት ማድረጓን ገልጠው ግዛቶቼ ያሏቸው ቦታዎችን የማስጠበቅ እና የመከላከል አቅም እንዳላት ተናግረዋል።
የሱዳን ከፍተኛ መሪዎች የአል ፋሻጋ ጉብኝት ኢትዮጵያ የሱዳን ጦር በኃይል ከያዛቸው ቦታዎቿ ለቅቆ እንዲወጣ ላቀረበችው ተደጋጋሚ ጥሪ ቀጥተኛ የእምቢታ ምላሽ መኾኑን የዜና ምንጩ አክሎ ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕወሓት ጋር የጀመረውን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሱዳን በክፍተቱ ገብታ ወረራ መፈጸሟን ከድርጊቷም እንድትቆጠብ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።