>
5:33 pm - Thursday December 5, 2785

ወለጋ ለአማራው ማህበረሰብ የደም መሬት ሆናለች....!!! (ጌትነት ዮሴፍ)

ወለጋ ለአማራው ማህበረሰብ የደም መሬት ሆናለች….!!!

ጌትነት ዮሴፍ


ምስራቅ ወለጋ አማራው ላይ ዛሬም የዘር ፍጅት እየተፈፀመ ነው!! 
ከወንበዴዋ ትህነግ ጋር የሚደረገው ጦርነት አማራ ተኮር ሆኖ የተወጠነ ጥቃት ሲሆን  ፥ የትህነግ መንትያ ኦነግ ሼኔ በአማራ ላይ ላይ የሚፈፅመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ በዝምታ ማለፍ ለጭፍጨፋው ይሁንታ መስጠት ስለሚሆን ማጋለጥ ተገቢ ንው!️
አሸባሪው ኦነግ በምሥራቅ  ወለጋ  ነቀምት  ዞን  ኪረሙ    ወረዳ ከነሀሴ 12-13 / 2013 ዓ.ም ባሉት ሁለት ቀናቶች ውስጥ  ፥   ቂልጡ አቦ ፣ አሹ ኩሣየና    ሢረ ዶሮ/ መርጋ    ጂረኛ   በተሰኙ ሦስት ቀበሌዎች ብቻ  እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል፡፡ ይህ የዘር ፍጅት የተፈፀመው ደግሞ በቀን 11/12/13 በስፍራው የነበረው የክልሉ ልዩ ሀይል ፖሊስ “ከላይ የመጣ ትእዛዝ ነው!” በሚል ሙሉ በሙሉ አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኃላ መሆኑ ደግሞ ጭፍጨፋውን ይበልጥ አስከፊ አድርጎታል!️
ባለፉት ሁለት ቀናት ከላይ በተጠቀሱት ቀበሌዎች ብቻ የደረሰውን የዘር ፍጅት ፣ የሀብትና ንብረት ውድመት በተመለከተ መረጃዎችን ለማጠናቀርና የሟቾችን ቁጥር ለመለየት ብሎም አስከሬን ለማንሳት ጭምር የፀጥታው ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም እስካሁን ባለው መረጃ :-
1ኛ. በ12/12/2013 ዓ.ም ፥ አሸባሪዎቹ የኦነግ ታጣቂዎች በሲረዶሮ  ቀበሌ  የሚኖሩትን አማራዎች ” መንግሥት የለም! መንግስታችሁ እኛ ነን! ስለዚህ ስብሰባ ውጡ!” ብለው አስገድደው ከየቤቱ በማስወጣት ፥ በስለት አርደውና በጥይት ጨፍጭፈው ከ60 በላይ የሚሆኑ ንፁሀንን ፈጅተዋቸዋል፡፡
2ኛ. በተመሳሳይ በዚያው በሲረዶሮ  ቀበሌ እለቱ የሚካኤል በአል የሚከበርበት ቀን በመሆኑ ፥ በቤተክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው በፀሎት ላይ የነበሩ 27  (ካህናትን ጨምሮ) ንፁሀንን ረሽነዋቸዋል፡፡
3ኛ. በዚያው በሲረዶሮ  ቀበሌ 01 ከተማ አስተዳደር በመፈፀም ላይ ያለውን እልቂት ሸሽተው  ወደገጠራማው ክፍል በመሸሽ ላይ የነበሩ ህፃናት ፣ ሴቶችና አረጋውያንን ጨምሮ ቁጥራቸው ከ100 የሚበልጥ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ልዩ  ቦታው  ቃንቄው  ጎራ  እየተባለ ከሚጠራው   ጎጥ  ላይ ሲደርሱ የኦነግ አሸባሪዎች ደርሰውባቸው በጅምላ ገለዋቸዋል፡፡
4ኛ. አሁንም   እዛው    ቀበሌ   በገጠሩ   ክፍል   ልዩ  ቦታው  “ወይናዱ” ከሚባል ቦታ አንድ ማየት የተሳነውን ግለሠብ ቤት ዘግተው በእሳት አቃጥለውታል፡፡ ሰውየውን ለማትረፍ የሞከሩ 3 የአካባቢው ነዋሪዎች በጥይት ተገለዋል፡፡
5ኛ.  በአሹ   ኩሣየ    ቀበሌ  ” ኩቲ  ጎጥ”    አንድ    የ80 አመት  መለኩሴ  ከሁለት  ህፃናት  ጋር  በአሰቃቂ ሁኔታ ሲታረዱ ፥ ሌሎች ቁጥራቸው 30 የሚሆኑ ደግሞ በጥይት ተረሽነዋል፡፡
6ኛ. በቂልጡ  አቦ  ቀበሌ  “ጨፌ  አርባ  ሚካኤል” ከሚባል ጎጥ   ላይ  ደግሞ ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ተለይቶ ያልደረሰኝ ንፁሀን ተጨፍጭፈዋል፡፡
7ኛ. በሁሉም ቀበሌዎች ያሉ አብያተክርስቲያናት ተቃጥለዋል ካህናቱም ተገድለዋል፡፡
መረጃውን ከስፍራው ያደረሱን በሽሽት ላይ የሚገኙ የአካባቢው  ነዋሪዎች ፤
“ የፌደራልና የክልሉ መንግሥት በአስቸኳይ የፀጥታ አካላትን ወደ አካባቢው ልኮ ቀሪ በጭንቅ ላይ ያሉ ዜጎችን እንዲታደግ ፥ የደረሰውን ጭፍጨፋና ግፍ አጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግና  ፥ ተጎጂዎችንና የተጎጂ ቤተሰቦችን በሙሉ ደህንነታቸውን በማስጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ “
 ሲሉ የድረሱልን ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል!
Filed in: Amharic