>

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ ግንባታ እና ለእመቤታችን፣ ለቅድስት ድንግል ማርያም የቀረበ ተማሕጽኖ!! (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ) ተማሕጽኖ!!

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ ግንባታ እና ለእመቤታችን፣ ለቅድስት ድንግል ማርያም የቀረበ ተማሕጽኖ!!

 (በወቅቱ የሥራና መገናኛ ሚ/ር የነበሩት፣ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም እንዳጫወቱኝ)

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


(Senior Researcher, Historian, Heritage Practitioner, Ambassador of Peace)

ክቡር፣ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ይህን ታሪክ ያጫወቱን በወቅታዊው የሀገራችን ሰላም ጉዳይ ላይ ለመወያየት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከዓለም ዕርቅ ሰላም ድ/ት አባላት ጋር በመሆን በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን በነበርንበት ወቅት ነው፡፡ ታዲያ ልዑልነታቸው በውይይታችን መካከል እንዲህ አሉን፡፡

‘‘… ዛሬ እንዲህ ሰላም የሰማይ ያህል ርቆን ብንጨነቅም በቀደመ ታሪካችን እኛ ኢትዮጵያውያን- ለአፍሪካ ሰላምና አንድነት፣ ፍቅርና ወንድማማችነት በብዙ የደከመን ታላቅ ሕዝብ ነን፡፡’’ በማለት ከቀደመው አኩሪ ታሪካችን በመነሳት ‘የአፍሪካ አዳራሽ ግንባታን ከፍልሰታ ጾም’ ጋር አያይዘው ትዝታቸውን እንዲህ አወጉን፡፡ 

በቅድሚያ ግን ምናልባት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ማን ናቸው ለምትሉ፤

የተዋሕዶ ሃይማኖት ስታለቅስ ቆማ፣

[እናት ኢትዮጵያ ስታለቅስ ቆማ]፣

አንገቱን ሰጠላት ዮሐንስ መተማ፡፡

ተብሎ የተገጠመላቸው ለተዋሕዶ ሃይማኖት፣ ለኢትዮጵያ ነጻነት እጅጉን ቀናኢ፣ ‘‘ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ወጽዮን’’ ተብለው ይጠሩ የነበሩት እና የግብፅን ወራሪ ኃይል በጉራዕና በጉንደንት የጦር አውድማ ለወሬ ነጋሪ እንዳይቀር አድርገው የደመሰሱት፣ የታላቁ ኢትዮጵያዊ፣ የዐፄ ዮሐንስ (ሦስተኛ) የልጅ፣ ልጅ ናቸው፡፡

ልዑልነታቸው፣ ራስ መንገሻ ሥዩም ከትግራይ ጠቅላይ ግዛት ገዥነት እስከ ሚኒስትርነት ማዕረግ የደረሱና፣ ሀገራቸውን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተዘዋውረው በቅንነት ያገለገሉ ትልቅ ባለታሪክ፣ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ (ለበለጠ መረጃ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመውን፣ የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩምን፣ ‘‘የትውልድ አደራ’’ መጽሐፍን ይመለከቷል)፡፡

አሁን፤ ወደ ልዑልነታቸው ‘የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሕንፃ ግንባታ ሂደትና የፍልሰታ ጾም ትዝታ’ ወጋቸው ልመልሳችሁ፡፡

አፍሪካውያን በአንድ ድምፅ- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሺሕ ዘመናት ታሪካችንና ሥልጣኔያችን መሠረት፣ የነጻነታችን ትእምርት፣ ሰው የመኾን ከፈጣሪ የተቸረ ፍቅር፣ ክብርና የመንፈስ ልእልናችን ማሕተም፣ የአፍሪካዊነት ብሔራዊ ኩራታችን ቀንዲል፣ የሃይማኖታችን የተስፋ ምድር… በሚል ክብር ከፍ በሚያደርጓት በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሲያቋቋሙ ዋና ጽ/ቤቱ በመዲናችን፣ በአዲስ አበባ እንዲሆን ነበር የወሰኑት፡፡

ታዲያ ከመስቀል አደባባይ ከፍ ብሎ የሚገኘውን የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን/የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሰብሰቢያ አዳራሽን በ10 ወራት ውስጥ ገንብታ እንድታስረክብ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከአፍሪካ ነጻ ሀገራት መሪዎች ለኢትዮጵያ ይህ ትልቅ አደራና ሓላፊነት ተሰጥቷት ነበር፡፡

ታዲያ ይህን ታላቅ የኾነ የአፍሪካውያንን አደራና ሓላፊነት የተቀበለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመገንባት ወገቧን በአጭር ታጠቀች። ‘‘የአፍሪካ አባት’’ ተብለው የሚጠሩት ንጉሠ ነገሥት፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃ/ሥላሴ ሥራውን በበላይነት ሲቆጣጠሩ፣ ሥራውን ይመሩ የነበሩት ደግሞ በወቅቱ የሥራና የመገናኛ ሚ/ር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ነበሩ፡፡

ልዑልነታቸው እንዳጫወቱንም፤ የአዳራሹን ግንባታ በ10 ወራት ለማጠናቀቅ ሲባል የግንባታው ለ24 ሰዓታት ያለምንም እረፍት በሦስት ፈረቃ ነበር ሲሠራ የነበረው፡፡

ታዲያ በወርኻ ነሐሴ በፍልሰታ ጾም ወቅት ልዑል ራስ መንገሻ አዘወትረው እንደሚያደርጉት አንድ እኩለ ሌሊት ላይ የሕንጻ ግንባታውን ሂደት ለመከታተልና ሠራተኛውን ለማነቃቃት በስፍራው ላይ ይገኛሉ፡፡ ልዑልነታቸው ሠራተኛውን እያበረታቱ፣ በዜማ ጭምር ‘‘ማርያም ሆይ እርጂን፣ ድንግል ሆይ እርጂን’’ እያሉ በማዜም ሥራውን ሲያስተባብሩና ሲያሠሩ ሳሉ በዛው ውድቅት ሌሊት ግርማዊ ጃንሆይ በድንገት የሥራውን ሂደት ለመከታተል አጃቢዎቻቸውን አስከትለው በቦታው ይደርሳሉ፡፡ ጃንሆይ ቀድሞውንም በትጋታቸውና በሥራ ወዳድነታቸውን የሚያደንቋቸውን ራስ መንገሻን በይበልጥ በትጋታቸው እየተደነቁ ከኋላቸው በመምጣት ትከሻቸውን መታ መታ በማድረግ፤

‘‘ራስ መንገሻ ትጋትህን እናደንቃለን፣ ሠራተኞችህም የዋዛ አይደሉም፣ እንደ ንቢቱ ታታሪ ናቸው፡፡ አፍሪካውያንና ዓለም የሰጠንን ብርቱ አደራ በጊዜው አጠናቀን እንደምናሳያቸው ተስፋዬ ጽኑ ነው፡፡ በዚህ ሌሊት ብርዱ ሳይበግራችሁ የአንተም የሠራተኞችህም ብርታትና ጥንካሬ በእውነቱ ይገርማል፣ ይደንቃል፡፡’’ አሏቸው፡፡

ራስ ልዑል መንገሻም ጃንሆይን ለጥ ብለው እጅ እየነሱ፣ ‘‘ጃንሆይ በእጅጉ የሚደንቀውስ የእርስዎ በዚህ ሌሊት በመካከላችን መገኘትዎ እንጂ… እኛማ ሥራችንም አይደል?! የእርስዎ የነጉሠ ነገሥታችን መንግሥት፣ አፍሪካውያንና ዓለም አምኖ የሰጠን አደራ ነውና ኢትዮጵያችን በዓለም ፊት እንዳታፍር ነው እንዲህ ጠዋት ማታ ሳንል መትጋታችን፣ መሥራታችን…፤’’ በማለት እንደመለሱላቸው አወጉን፡፡

የክቡር ልዑል ራስ ራስ መንገሻ ሥዩምን ወግ/ትዝታ፣ ‘‘የትውልድ አደራ’’ በሚለው መጽሐፋቸው ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ባስተላለፉት መልእክታቸው ልቋጨው ወደድኹ፡፡

ባለፉት ረጅም ዘመናት አባቶቻችንና እናቶቻችን ስለኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነት ፀንቶ መኖር፣ ያደረጉት ትግልና የከፈሉት መሥዋዕትነት፣ የአሁኑ ትውልድ አልቆ ድርሻውን እንዲወጣ አደራ እላለኹ፡፡ ከማንም ከምንም በላይ፣ ሁላችንም በአንድነት፣ የፍቅር ሠንሠለት አያይዞ የሚያኖረን ኢትዮጵያዊነታችንን እንጠብቅ፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!!

 

የሰላም እንደራሴ፣ የሀገር ሽማግሌ፣ ኩሩው ኢትዮጵያዊ፣ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ፈጣሪ ጤናንና ረጅም ዕድሜን ያድልልን!!

እንኳን ለእመቤታችን፣ ድንግል ማርያም ትንሳኤዋ፣ ፍልሰቷ አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!

Filed in: Amharic