>

የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክን ከታሪክ መድረክ አፈና ተገቢ አይደለም (አበበ ሀረገወይን)

የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክን ከታሪክ መድረክ አፈና ተገቢ አይደለም

አበበ ሀረገወይን

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ሲጻፍ የንግሥት ዘውዲቱ ለ13 አመት ባገራችን ታሪክ ታይቶ የማያውቅ የሰላም ዘመን ከነገሱበት 1908 እስከ 1921 አልፏል። ታሪካቸው ሲጻፍ ግን በሳቸው ዘመን የተደረገው ነገር ሁሉ በንጉሥ ተፈሪ ብቻ እንደተደረገ ፣ እሳቸው ግን ከጾምና ከጸሎት ሌላ ምንም መሀይም ነበሩ የሚል ግምት የሚሰጥ የህይወት ታሪክ ነው ያላቸው።
የዋህ ልጅን እናቱም አትወደውም እንደሚባለው ፣ የኛ ትውልድም የስማቸው መጥፋት መሰሪነት ሳይለየው የኝህን በስነ ስርአት ነግሰው እሳቸው ካልፈረሙበት ትልቅ ውሳኔ የማይተላለፍ የነበሩትን ንግስት እንዳልተፈጠሩ የማድረግ በደልና የታሪክ ሰለባና ውምብድና  አሁንም እንደ ቀጠለ ነው።
ስለ እቴጌ አንዳንድ ማሳሰቢያዎችን ብንመለከት ስለሳቸው ያለን ንቀት ይቀንስ ይሆናል፨
፠ እቴጌ ዘውዲቱን ከህጻንነታቸው ጀምረው በስነ ስርአት ያሳደጓቸው ጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ ነበሩ።  የጀግና ልጅ ጀግና ነው።
፠ እቴጌ ዘውዲቱ የሀያ አመት ወጣት ሆነው ከቴጌ ጣይቱ ጎን ተሰልፈው የቆሰሉትን እርዳታ መስጠትና የታመሙትን በማጽናናት የአድዋ አርበኛ ናቸው
፠ እቶጌ ጣይቱ ከስልጣን ተወግደው በእንጦጦ የቁም እስር ላይ ሆነው ብዙ የቀድሞ የባላቸው የእምዬ ምኒልክ ባለሟሎች ሲከዷቸው እስከመጨረሻ እድሜያቸው ድረስ ሳይለዩዋቸውና መጨረሻም ሲሞቱ እንደ ልጅ ሆነው በክብር የቀበሯቸው እሳቸው ናቸው
፠ ባርነትን ያስቀረውን ሕግ እንዲወጣ ያደረጉትና በስራ እንዲውል የተደረገው በሳቸው ዘመን ነው
፠ ኢትዮጵያ የአለም ሊግ አባል እንድትሆንና ንጉስ ተፈሪ አገራቸውን እንዲወክሉ የፈቀዱት እሳቸው ናቸው
፠ የአጼ ቴዎድሮስ ዘውድ ከተሰረቀበት እንግሊዝ አገር እንዲመለስ ያደረጉት እሳቸው ናቸው
፠  እቴጌ ዘውዲቱ የዘመናዊዋ አፍሪካ የመጀመሪያ ሴት ያገር መሪ ነበሩ
፠ እቴጌ ሩህሩህና ለተጎዱ አዛኝ በመሆናቸው የአዲስ አበባውና የቢሲዲሞው የስጋ ደዌ ሆስፒታሎች እንዲከፈቱ ያደረጉ እሳቸው ናቸው
እቴጌ ዘውዲቱ ሲሞቱ ብጹእ አቡነ አብርሐም ፤ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንቺው አልቅሺ ፣ የዋህ ጠባቂሽን አጥተሻልና ብለው የተሰበሰበውን ህዝብ አላቅሰውታል።  እቴጌን ማንም በክፋት የሚያነሳቸው ኑሮ አያውቅም።
ዘመዶቼ ጡር ፈርተን እቴጌ ዘውዲቱን የሚገባቸውን ቦታ እናሲዛቸው። እርግማኑም ይቀርልን ይሆናል።
የንግስተ ነገስታት ዘውዱቱን ነፍስ በገነት ያኑርልን!
Filed in: Amharic