ባልደራስ ለእውነተኛ ዴምክራሲ ፓርቲ
በምስራቅ ወለጋ ኪረሞ ወረዳ በአሸባሪው የኦነግ ሰራዊትና በኦህዴድ ብልፅግና መዋቅር ውስጥ ባሉ አመራሮች እገዛ ጭምር ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው አማራ በመሆናቸው
ብቻ በግፍ ተገድለዋል። አብዛኛዎቹ ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸውል ። ከሞት ያመለጡት ደግሞ የተፈናቀሉ መሆኑን የሚገልጽ መረጃ ደርሶናል።
ነሃሴ 12 ቀን ከረፋዱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 11ሰዓት ድረስ በኦነግ የሽብር ቡድን ጭፍጨፋው ተደርጓል። የዘር ጭፍጨፋውን እጅግ ከሰብዓዊነት የወጣ የሚያደርገው ደግሞ የአዕምሮ ህሙማንን፣ አካል ጉዳተኞችን እና ህፃናትን ያለየ መሆኑ ነው።
ከቀናት በፊት በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ የኦነግ ሰራዊት የተለያዩ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ መሆኑን ነዋሪዎች ጠቅሰው የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥበቃ እንዲያደርግለቸው በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበው እንደ ነበር ለማወቅ ችለናል። ነገር ግን ለጥሪው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጌታቸው ባልቻ የተባሉ የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሓላፊ “ኦነግ የተቆጣጠረውም ሆነ የዘጋው መንገድ የለም” በሚል ከእውነት የራቀ መረጃ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መስጠታቸው የወንጀሉ አንድ አካል እንደሆኑ ያሳያል።
የኦሮሚያ ክልል ልዮ ኃይሎች መርጋ ጅሬኛ ቀበሌ የነበሩ ቢሆንም፣ በስፍራው በመቆየት ንፁሃን ዜጎችን ከጭፍጨፋ መታደግ ሲገባቸው ነሃሴ 11 ቀን ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ የዘር ማጥፋቱ ሊፈፀም አንድ ቀን ሲቀረው ወንጀሉ ከተፈፀመበት መርጋ ጅሬኛ ቀበሌ በኪረሙ ወረዳ አስተዳድሮች ትዕዛዝ ለቀው እንዲወጣ ተደርገዋል። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው በወለጋ የሚካሄደው ጭፍጨፋ መንግሥታዊ ድጋፍ እና ሽፋን ያለው ለመሆኑን በቂ ማስረጃ ነው።
የመንግሥትና የግለሰብ የሰሌዳ ቁጥር ባላቸው መኪኖች ተጭነው እንደመጡ የሚነገርላቸው የኦነግ አባላት በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ መርጋ ጅሬኛ ቀበሌ የሚገኙ አማሮችን ሴት፣ ወንድ፣ ህፃን፣ የአዕምሮ ህሙማን፣ አረጋውያን እና አከል ጉዳተኛ ሳይሉ በግፍ መግድላቸው ዕጅግ የሚያሳዝን ነው።
በኦነግ ከተገደሉ የአዕምሮ ህሙማን፣ አካል ጉዳተኞች እና የቤተ ክርስትያን አባቶች መካከል
~ቄስ መምህሬ ንብረት
~ የአቶ ካሴ ሦስት ልጆች ሀብታሙ ካሴ፣ መልካሙ ካሴ እና ሳሳው ካሴ፣
~ ወ/ሮ ሙጨታ አበጋዝ እና ወ/ሮ አገሬ ሙላት (ለረጅም ጊዜ የዐዕምሮ ህሙማን የነበሩ)
~ አቶ አድማሱ ተረፈ (በክራንች የሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኛ)
~ አባ ሙሉየ ባዬ የለኮ ሙሉ ቤተ ክርስትያን ጥበቃ የነበሩ እና አቢ የተባሉ ሹፌር ይገኙበታል።
ይህ ድርጊት አሸባሪው ኦነግ ብቻ ሳይሆን የትህነግን የጥላቻ መርዝ ሲጋቱ ያደጉት የኦህዴድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ያሳየ ነው።
አሁን ላይ አገሪቱ በዕርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሆና እንኳን ኦነግና ኦህዴድ ተስማምተው በአንድ ጎሳ ላይ የሚፈፅሙትን የዘር ማጥፋት አጠናክረው መቀጠላቸው ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ያላቸውን ጥላቻ የሚያረጋግጥ ነው።
ከሞት አምልጠው የሸሹ ከ40 ሺህ በላይ አማሮች አሁንም ያለጠያቂ ሃሮ አዲስ ዓለም ቀበሌ ያለ ጠያቂ መውደቃቸው እና በርሃብና በውሃ ጥም ለዳግም ቅጣት መዳረጋቸው የዚሁ አንድ አካል ነው።
ከዘር ማጥፋቱ በተጨማሪ የአማሮች የቁም እንስሳት፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እና ሌሎችም ንብረቶች ተዘርፈዋል። ማሳዎቻቸውም ተቀጥለዋል።
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ የአማራ ተወላጆች ያሉበትን መከራ እንኳን እንዳያሳውቁ በአካባቢው የኦህዴድ ሰዎች ኔት ወርክ እንዲቋረጥ መደረጉ የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ያሳያል።
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት፣ ዲፕሎማቶች፣ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ኦነግ ከግብር ወንድሙ ኦህዴድ ጋር በመሆን በጦርነቱ ሽፋን በወለጋ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚፈፀመውን ጥቃት በማጋለጥና እንዲቆም እንዲጠይቁ ጥሪ እናቀርባለን።
ሀገሪቱን የሚገዛው የፌደራል መንግሥት የወንጀሉን መጠን ባስቸኳይ አጣርቶ ለህዝብ እንዲያሳውቅ እና ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ እናሳስባለን።
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ነሃሴ 17/2013 ዓ.ም.