እኔ የምለው፣ የሽብርተኝነት መመዘኛ በአውሮፕላን ፎቅ ማፍረስ ብቻ ነው እንዴ?!
(በድሉ ዋቅጅራ)
አንዳንድ የመንግስት ሚዲያዎችና የማህበራዊ ሚድያ ዘጋቢዎች፣ የሳማንታ ፓዎርን አስተያየት በማየት፣ አሜሪካ የአቋም ለውጥ ማሳየት እንደጀመረች አድርገው ዘግበዋል፡፡ ለውጡ የቱ ጋ እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ሴትየዋ ያለችው፣(1) ትህነግ ከአማራና አፋር ክልሎች ይውጣ፣ (2) ተደራደሩ ነው፡፡
ሁለቱም ደግሞ የነበረ ነው፡፡ የተደረገው ለውጥ እስካሁን በገደምዳሜ ይሉት የነበረውን የትህነግ ከአማራና አፋር መውጣት ማጠንከራቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአቋም ለውጥ ሳይሆን፣ እንዲያውም በተቃራኒው ትህነግን መደገፍ ነው፡፡ ትህነግ እየተሸነፈና ከገባበት በግድ እየወጣ ስለሆነ፣ ለአወጣጡ የክብር መንገድ ሊከፍቱለት፡፡
ከሁሉም የሚገርመው ግን፣ ትህነግ በደረሰበት ያደረሰውን ጥፋት እየተመለከቱ አሁንም ተደራደሩ ማለታቸው ነው፡፡ የገበሬውን የኑሮ መሰረት የሆኑትን ከብቶች እየረሸነ፤ ሆስቲታል እየዘረፈ፣ መንደር እያቃጠለ፣ . . . ከሽብርተኛ የማይደራደሩት እነ አሜሪካ መንግስትን ተደራደር ይላሉ፡፡ እኔ የምለው፣ የስብርተኝነት መመዘኛ በአውሮፕላን ፎቅ ማፍረስ ብቻ ነው እንዴ?! ነው ወይስ ለመሸበር ነጭ መሆን ያስፈልጋል? ማርያምን በዛ!