>

ደብረ ደቢጥ ትልቅ ሽንፈት ወደ ሕሊናቸው ይመልሳቸው ይሆን ? ( ግርማ ካሳ)

ደብረ ደቢጥ ትልቅ ሽንፈት ወደ ሕሊናቸው ይመልሳቸው ይሆን ? 

ግርማ ካሳ

በጋይነት ግንባር፣  የሕወሃት ታጣቂዎች በጨጨሆና ደብረ  ደቢጥ ተሸንፈው ሽሽት ላይ እንደሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ የአማራ ሕዝባዊን ሰራዊትና መከላከያ ደብረ ደቢጥ ገብቷል፡፡
ደብረ ደቢጥ እጅግ በጣም ስትራቲጂክ የሆነች ከተማ ናት፡፡
ወያኔዎች ለሁለተኛ ጊዜ ነው ከደብረ ደቢጥ ተሸንፈው የለቀቁት፡፡ የመጀመሪያው ጊዜ ከ 10 ሺህ በላይ ሰራዊት አሰልፈው ከተማዋን ተቆጣጥረው ነበር። አቶ ደመቀ መኮንን ጨጨሆን የጎበኙ ሰሞን በተደረገው ዉጊያ ከደብረ ጠቢጥ ወያኔ ተሸንፋ ፣ እንደ ኮኪት ፍላቂት ያሉ ከተሞች ሁሉ ሳይቀሩ ተባራ ነበር።
ሆኖም በብዙ እጥፍ ሌላ ኃይል በማሰማራት ወያኔ መልሳ ደብረ ደቢጥን ያዘች።፡ ደብረ ዘቢጥ ብቻ አይደለም፣ ጨጨሆ፣ ንፋስ መውጫ ክምር ድንጋይ እያለች ጉባ ተራራን ሳይቀር ይዛ ፣ ደብረ ታቦር ደጃፍ ደረሰች። የደቡብ ጎንደር ሕዝብ ፋታ አልሰጣት አለ። በደቡብ ጎንደር ከፍተኛ ሽንፈት ከደረሰባት በኋላ ብዙ ውድመት ፈጽማ ወደ ደብረ ደቢጥ ሸሸች።፡
ወደ ደብረ ደቢት  የሸሹት  ወያኔዎች ዋናውን መንገድ ትተው፣ በኮን በኩል ጋሸና በመግባት፣  በጋሸና በኩል ወደ ላሊበላ ለማምለጥ እየሞከሩ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በኮን ለማምለጥ ወያኔዎች በአሁኑ ጊዜ ዉጊያ እያደረጉ ነው፡፡
የጋይንት/ደብረ ታቦር ግንባር ወያኔ  ሌሎች ቦታዎች ካሰማራቻቸው ኃይል እጅ በጣም የበዛውና የጠነከረው ነው፡፡ በሌሎች ግንባሮች ካሰማራቻቸው በ 4፣ 5 እጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡
የወያኔ መሪዎች በዚህ ግንባር በዚህ መልኩ ትልቅ ሽንፈት መከናነባቸው፣ ቆም ብለው እንዲያስቡ፣ ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ ሊረዳ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ያንን ያህል ከባድ መሳሪያና  ያንን ያህል ሰራዊት አሰልፈውም፣ ሁለት ሶስት ጊዜ ተጨማሪ ኃይልም ልከውም፣  ያውም አብዛኛው ተዋጊ ገበሬዉና ሚሊሺያዎች በሆኑበት ዉጊያዎች ከተሸነፉ፣  “እኛ በዉጊያ አንቻልም፡፡ ሌሎች መደምሰስ አያቅተንም” ከሚሉት ቅዠት በመውጣት፣   እነርሱ ብቻ ሳይሆን በዚያኛው ወገን የሚዋጋ እንዳለ ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡   ያሉ ልዩነቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ በዉይይትና በድርድር ለመፍታትም ይዘጋጃሉ ብዬ እጠበቃለሁ፡፡ ህሊና ካላቸው ማለቴ ነው፡፡
የስሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም ከስምንት ወር በፊት ጦርነት የቀሰቀሱት ሕወሃቶች ናቸው፡፡ አሁንም ደግሞ ተኩስ አቁም ሲታወጅ፣ ተኩስ አናቆምም ብለው ወሎ፣ ጎንደርና ኣፋር ዘልቀው በመሄድ ወረራ የፈጸሙት፣ ጦርነት የከፈቱት ሕወሃቶች ናቸው፡፡
በሕዳር ወር ምን እንደሆነ ያውቃሉ፡  አሁንም ደግሞ ምን እየሆነ እንዳለ እያዩ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የትግራይ ወጣት ማለቅ የለበትም፡፡ በጦርነት ምንም አይነት መፍትሄ እንደማይመጣ አውቀው ይልቅ ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅም ውሳኔ ያሳልፉ፡፡
1ኛ  በወልቃይት፣ በአፋር ዞን 4 እና ዞን 2 ግንባሮች ወያኔዎች 100% ተሸንፈዋል፡፡ ከደቡብ ጎንደር ዞን ብዙ ታጣቂ አልቆባቸው ለቀው ወጥተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ወሎ፣  በጠለምትና በዋገምራ  ዉጊያ እየተደረገ ነው፡፡ በአስቸኳይ ከነዚህ ቦታዎች ለቀው መውጣት አለባቸው፡፡ ራያ አወዛጋቢ ነው፡፡ ቢሆንም ከራያም ለቀው መውጣት አለባቸው፡፡
2ኛ  የተኩሳ አቁም ማወጀ አለባቸው፡፡
3ኛ  ሕወሃት አሸባሪ ድርጅት እንደመባሏ፣ እስከ አሁን ላለው ነገር ሕወሃት ተጠያቂ በመሆኗ፣ የሕወሃት አመራሮች ወደ ጎን ገለል ብለው፣  የትግራይ ኃይሎችን ወክሎ ለድርድር የሚቀርብ አዲስ አመራር ይዘጋጅ፡፡
ይህ ከሆነ በኋላ፣ በማንኛውም ጉዳይ ላይ የትግራይ ኃይሎችን የሚወክሉ ወገኖች ለድርድር  አጀንዳ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የትግራይ ማህብረሰብን በተመለከተ ፡ ለምሳሌ
– የሕወሃት አመራር ፣ ለሰላም ሲባል ፣ የማርያም በር ተከፍቶላቸው ከአገር እንዲወጡ
– ወልቃይትና ራያ የፖለቲካ መፍትሄ እስኪመጣ፣ ትግሪኛና አማርኛ የስራ ቋንቋ ሆኖ በፊዴራል  መንግስት ስር እንዲሆኑ
– የሕወሃት መሪዎች ገለል እንዲሉ እንደተደረገው፣  በፌዴራል መንግስቱም ሆነ በአማራ ክልል የችግሩ አካል የሆኑም አመራሮች በዋናነት ዶር አብይ አህመድ፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ አገኘው ተሻገር ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ
– ሁሉን አሳታፊ አገራዊ የብሄራዊ መግባባት ዉይይት እንዲደረግና የብሄራው እርቅ መንግስት እንዲቋቋም
የሚሉና ሌሎች አጀንዳዎችን ማቅረብ ይችላሉ፡፡
የትግራይ ወገኖች አሁንም በጡንቻ ተማምነው ግትርነት ከመረጡ ግን ፣ የበለጠ ነው የትግራይ ሕዝብ አደጋ ውስጥ የሚጥሉት፡፡ እነርሱ በተዋጉ ቁጥር ሌላው የበለጠ እያከረረ ነው የሚመጣው፡፡ በርግጠኝነት ምን አልባት በአሻጥረኛ የመከላከያ የጦር አዛዦች የሚመሩ የመከላከያ ጋንታ፣ ወይም ብርጌዶችን ያሸንፉ ይሆናል። ሕዝባዊ የሆነውን የአማራ ሕዝባዊ ሰራዊት ግን ማሸነፍ አይችሉም።
ምን አልባት ፣ እንደ ኮሶቮ ፣ እነ አሜሪካ ጣልጋ ይገቡልናል፣ ብለው አስበው ከሆነ ሞኞች ናቸው ማለት ነው፡፡ ከአፍጋኒስታን መማር አለባቸው፡፡ ደግሞም አሜሪካኖች ጫና እናድርግ ቢሉም የአብይ መንግስት ላይ ነው ጫና ማሳደር የሚችሉት፡፡ ዶር አብይ ከነርሱ ጋር ተስማምቶም እሺ ቢላቸው የአማራ ማህበረሰብ ዶር አብይ ስላለ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገውን የሕልውና ትግል የሚያቆም አይደለም፡፡ የአማራ ክልል ክተት ያወጀው፣ የፌዴራል መንግስቱ ተኩስ አቁሞ የነበረ ጊዜ መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡ አሜሪካ በአማራው ማህበረሰብ ላይ ምንም አይነት ሌቪረጅ የላትም፡፡
የኤርትራ ጉዳይም አለ። የኤርትራ መንግስት በማንኛውም ጊዜ የሰለጠነ፣ የታጠቀ ሰራዊቱን ወደ ትግራይ የማስገባት እድሉ በጣም ሰፊ ነው። ወደ ሰላምና ድርድር ካልተመጣ የኤርትራ መንግስት እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥበት ሁኔታ አይኖርም።
አሁንም እላለሁ  ተጋሩዎች ወደዱም ጠሉም ከአማራው፣ ከአፋሩና ከኤርትራው ማህበረሰብ ጋር ጥንትም አብረው ኖረዋል፣ ወደፊት አብረው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከነዚህ ማህበረሰብ ጋር መስማማት ነው የሚበጃቸው።
Filed in: Amharic