>

የልጅ ኢያሱ አደገኛ ጥፊ....!!! (አበበ ሀረገወይን)

የልጅ ኢያሱ አደገኛ ጥፊ….!!!

አበበ ሀረገወይን

ልጅ ኢያሱ የእምዬ ምኒልክ አልጋወራሽ ፣ አያታቸው ሲሞቱ እድሜያቸው ገና 13 ስለ ነበር ፣ አቅመ አዳም እስኪደርሱ በራስ ተሰማ ናደው ሞግዚትነት እየተመሩ አገር እንዲገዙ ነበር ኑዛዜው። እምዬም ከቃሌ የወጣ ጥቁር ውሻ ይውለድ ብለው እርግማን ጨምረውበት ነበር።
ልጅ ኢያሱ ግን አንድ ቦታ መቀመጥ የማይችሉና ፣ ከተከበረ ያገር መሪ የማይጠበቁ በድርጊት የተደገፉ ጠባዮች ነበሯቸው። ራስ ተሰማ እምዬ በሞቱ ባንድ አመት ውስጥ ታመው ሲሞቱ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ፣ አክስታቸው ዘውዲቱና ፣ የቅርብ ዘመዳቸው ተፈሪ ራስ ተሰማን ተክተው አማካሪ እንዲሆኑ ተወሰነ። ከሶስቱም ይበልጥ ለእምዬ ታማኝ በመሆን ፣ በበሳልነትና ፣ በህዝብ ተከባሪነት ከፍተኛውን ቦታ የነበራቸው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ነበሩ። እስካሁንም እንደተከበሩ ናቸው። ልጅ ኢያሱ ግን ብስለት የጎደላቸው ጮርቃ ስለነበሩ እንደ አገር ባህልና ህግ ንግሥናቸውን ትተው አባታቸውን ራስ ሚካኤልን የእምዬን ዘውድና የክብር ልብስ አስለብሰው ንጉሥ ሲያደርጉ  ብዙ ጉምጉምታና አለመረጋጋት ፈጥሯል።
የልጅ ኢያሱ አለመብሰል በተለይ ከፊታውራሪ ጋር እያጋጫቸው መጣ። አንድ ቀን ሁለቱ በበቅሎ ተቀምጠው መንገድ ሲገናኙ ልጅ ኢያሱ ሪህ ያማቸው የነበሩትን ፊታውራሪን ከበቅሎ ወርደህ አቀርቅረህ አሳልፍ ብለው አዘዋቸው ፊታውራሪም ትእዛዛቸውን አክብረው አሳለፏቸው። ሶስቱ አማካሪዎች በችሎት ላይ ሕዝብ በተሰበሰበበት ልጅ ኢያሱ ፊታውራሪን የመሰሉ ያገር ጀግና በድፍረት በጥፊ ሲመቱ ብዙ ሰው ረግሟቸዋል። ስህተታቸውን ያባባሰው ደሞ ፊታውራሪን አስራለሁ ሲሉ አቡኑ በመሀል ገብተው እንዲቀር አርገዋል።  ልጅ ኢያሱ ምንም እንኳን አንዳንድ ውሳኔዎቻቸው ዘመናዊነትና ጥቅም ያላቸው ቢሆኑም የልጅ አምባ ገነንነታቸው በጊዜው የነበሩት ታላላቅ ሰዎችንና ተሰሚነት የነበራቸውን ያዲስ አበባ ባላባቶች እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል። መካር ያጣ ንጉስ ካላንድ አመት አይነግሥ የሚባለው አነጋገር ልጅ ኢያሱን ለመግለጽ የተፈጠረ ያስመስለዋል። የልጃቸው አለመብሰልንና መጠላት ከስልጣን የሚያወርድ አደጋ በመጠርጠር ንጉሥ ሚካኤል የወሎን ጦር ይዘው አዲስ አበባ ከትመው ነበር። ሀኔታው ያላማራቸው የሸዋ መኳንንትም ቀስ በቀስ ጦረኛ በመሰብሰብ አዲስ አበባን ማስከበብ ጀመሩ። ንጉሥ ሚካኤልም ልጃቸውን እንዳይመክሩ ልጅዬው አገር ላገር በተለይ አፋር ገብተው ብዙ ሚስት በማግባት አገር አስተባብራለሁ ባዩ ልጃቸው የውሀ ሽታ ሲሆኑባቸው ወንድም ለወንድም ደም የሚያፋስስ ጦርነት እንዳይመጣ ብለው ወደ ደሴ ተመለሱ።
በዚያ በአንደኛው የአለም ጦርነት አጥቢያ ልጅ ኢያሱ የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ከጀርመንና ከቱርክ ጋር የጀመሩት ስምምነት በእንግሊዝና በፈረንሳይ ጥርስ አስገባቸው። ታሪኩን ለማሳጠር የልጅ ኢያሱ ህይወት እንደ ተራ ሽፍታ አገር ላገር መንከራተት ሆነ። መጨረሻቸውም ፍቼ ታስረው ሞቱ ከሚለው ትርክት ወዲያ መቼ ፣ በምን ምክንያት ፣ የትስ ተቀቡሩ ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ የለንም።
Filed in: Amharic