>
5:09 pm - Monday March 3, 4702

ጦርነቱ ይቁም! የምንለው ማንም አሸናፊ የማይሆንበት የወንድማማቾች መጨራረስ ስለሆነ ነው...!!! (ጎዳና ያእቆብ)

ጦርነቱ ይቁም! የምንለው ማንም አሸናፊ የማይሆንበት የወንድማማቾች መጨራረስ ስለሆነ ነው…!!!
ጎዳና ያእቆብ

False Equivalence: ድርድር ውይይት ሲባል አማራው ለህልውና መታገል የለበትም ማለት አይደለም:: ከጦርነት በኃላ የሚመጣውን ንግግር ታሳቢ ያድርግ ማለት ነው:: የተኩስ አቁም ስምምነት ለምሳሌ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው ይዞታ(Status quo ante bellum) ይከበር ወይም የተያዘው ይዞታ እንደተያዘና ሁሉም ባለበት ቆሞ የሚለውም የሚመጣም ንግግር ሲጀመር ነው:: Status quo ante bellum  የሚለው በእርግጥ ይዞት የሚያመጣው የዛሬ አስር ወር ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የነበረው ይዞታ ወይስ ማእከላዊ መንግስቱ የተናጥል ተኩስ አቁም አዋጅ በታወጀበት ጊዜ የነበረው ይዞታ የሚለው የሚያስነሳው ውዝግብ አለ::

ውይይትን መፍራትና ጦርነትን እንደ ብቸኛ አማራጭ የማየቱ አዝማሚያ ስረ መሰረቱ ይሄም ስጋትነው ብዬ አስባለሁ:: የዛሬ አስር ወር ወደነበረው ይዞታ ከተባለ ወልቃይትና ራያ ወደ ትግራይ ሊመለሱ ነው:: ወደ ሱዳን የሚያስወጦ ኮሪዶርም የሚለውን የህዋሃትን ጥያቄ ሲመልስ ለአማራው ግን ክስረት ብቻ ይሆናል:: ከዚህም አንፃር ሰላም አክሳሪ ይሆናል:: ማእከላዊ መንግስቱ የተኩስ አቁም አዋጅ ሲያውጅ የነበረው ይዞታ ከተባለ ደግሞ ወልቃይና ራያ በአማራው ክልል ይዞታ ስር ይሆንና ለትግራይ ክልል አክሳሪ ይሆናል::

ሁሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚለው የህዋሃትና የአማራ ክልል አካሄድ ከክልላዊ ጥቅምና ጉዳታቸው አንፃር ትክክል ቢሆንም ኢትዮጵያ አማራ እና ትግራይ ክልል ብቻ አይደለችም:: ውድመቱና ክስረቱም የሁለት ክልልሎች ብቻ አይደለም:: ስለዚህ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ጉዳይ ሊመክበት ይገባል::

ባልቀበለውም አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት መሬት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው ይላል እንጂ የእከሌ ወይም የእከሊት ነው ስለሚል በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ያለ መሄት ላይ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ባለቤት ናቸው:: ያገባቸዋልም:: ከዚህ አንፃር ገለልተኛ የሆነና የራሱ ቅምጥ ፍላጎት የሌለው ማእከላዊ መንግስት ኖሮ ቢሆን ኖሮ ደም አፋሳሽ ለሆነው ውዝግብ win win የሆነ ዝላቂ መፍትሄ ያመጣ ነበር:: አልታደልንምና ያ! አልሆነም::

ስለዚህ መፍትሄው ምንድነው? ሲጨራረሱ መኖር እንደው ጥይት ሲጨርሱ ማብቃቱ አይቀሬ ነው:: በዘላቂነት በአሸናፊነት የሚወጣ አካል ይኖራል ብዬ አላስብም:: ለትውልድ የሚተላለፍ ቁርሾ ማስተላለፍ ሀገራዊ ባህሪያችን እየሆነ መጥቶአልና ያው በደም የተሳለ እና በቪዲዮ የታጀበ ቁርሾ በመሰነድ ላይ ነን:: ይህንን ጦርነት የምናቆመም ስለወደድን ወይም የሰላም ሰዎች ስለሆንን አይደለም::

ያ! እንዳልሆነማ የእምነት አባቶችም በለው ግፋው ገስግስ ሲሉ በአግርሞት ታዝበናል:: ገብቶናል:: ጦርነቱን የምናቆመው ማንም አሸናፊ የማይሆንበት ጦርነት ስለሆነ ነው:: ሰላም ከማን ጋር? ለሚሉት ደግሞ መልሱ ከደመኛህ ጋራ! ከፀበኛህ ጋራ እንጂ ከወዳጅህ ጋርማ ምን እርቀ ሰላም ያስፈልገዋል!

አይ ተጨራርሰንና ኢኮኖሚያችንን ጨርሰን ከዛ በኃላ በጠረጵዛ ዙሪያ እንቀመጥ ለሚሉ ግፋ በለዎችም እንግዲህ ምን ምርጫ አለ እስኪዋጣላችሁ ድረስ ቆሞ ከማየት ውጪ!!

በኔ እምነት ጦርነት ወይም ሞት የሚሉትን ሁሉ እንደ Halloween የወታደር ልብስ አልብሶ ማይክ እየሰጡ ማናገር ወይም ወጧ እንዳማረራል ሴት ከአንድ ቦታ ሌላ ቦታ ሽር ጉድ እንዲሉ ማድረግ ሳይሆን ጦርነቱ በተፋፋመበት ግንባር ሁሉ እየወሰዱ ከፊት ለፊት ማሰለፍ ነበር::

እንደማየው ከሆነ በሁሉም ወገን አመራሮቹ ሁሉ በየመድረኩና በየፎቶ ሲታዩ እንጂ ከዛ ሁሉ የጦነት ሰለባዎች አንዳቸው ሲሆኑ አላየንም:: ወይ ጥይቱ እንሱን አይመታም:: ካልሆነም የጦርነቱ አውድማ ውስጥ የሉም::

የነሱ ልጆች ይመረቃሉ የደሀው ልጆች ያልቃሉ::

Filed in: Amharic