>

‹‹ጦርነቱ የወንድማማቾች ሳይሆን አሸባሪዎች የሚያካሂዱትን ጅምላ ጭፍጨፋ ለማስቆም የሚካሄድ ነው...!!!››  – መምህር ታዬ ቦጋለ ደራሲ እና መምህር

‹‹ጦርነቱ የወንድማማቾች ሳይሆን አሸባሪዎች የሚያካሂዱትን ጅምላ ጭፍጨፋ ለማስቆም የሚካሄድ ነው…!!!››
 – መምህር ታዬ ቦጋለ ደራሲ እና መምህር

የኢትዮጵያ ህዝብ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን መከላከያ ሠራዊት ከጀርባው ከወጋው የሽብር ቡድን ጋር የሚደረገው ጦርነት በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ሳይሆን አሸባሪው ህወሓት በንጹሐን ላይ እያደረሰ ያለውን የጅምላ ጭፍጨፋ ለማስቆም የሚካሄድ መሆኑን የማህበረሰብ አንቂ ፣ ደራሲና መምህር ታዬ ቦጋለ አስታወቁ። አሸባሪዎቹ ሸኔ እና ህወሓት አብረን እንሠራለን ማለታቸው የየራሳቸው ዓላማና መርህ እንደሌላቸው ያመላከተ መሆኑን ጠቆሙ።
መምህር ታዬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ህዝብ ለ20 ዓመት ይጠብቅ በነበረው መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ሲኖትራክ የነዳ፤ ሴት የሠራዊት አባላትን ጡት እስከመቁረጥ የደረሰ እና በርካታ ኢሰብዓዊ ግፎች የፈፀመ ቡድን ነው።
ይህ እውነታ የአደባባይ ምስጢር በሆነበት ሁኔታ አንዳንድ አካላት ጦርነቱ በወንድማማች መካከል የሚደረግ ነው በሚል በህብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረውን ጠላትን በጋራ የማጥቃት መነሳሳት ለማዳከም እየሠሩ እንደሆነ አስታውቀ ዋል።
ይህ ጦርነት የወንድማማቾች ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝብና በስልጣን ላይ ለ27 ዓመታት በመቆየት ከፍ ያሉ ሰብዓዊ ወንጀሎችን ሲፈጽም ፣ የሀገርን ንብረት ሲዘርፍ፣ ሀገርን ለማፍረስ ቀን ተለሌት ሲሠራ ከቆየ አሁንም ደግሞ በየቦታው የጅምላ ጭፍጨፋ እያካሄደ ካለው በአሸባሪው ህወሓት መካከል የሚካሄድ ጦርነት እንደሆነ አመልክተዋል።
ወንድም በጋራ የጋራ ቤቱን ለማሳደግ ይሠራል ያሉት መምህር ታዬ፣ የሽብር ቡድኑ አባላት ግን ከዚህ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ትፍረስ እያሉ የሚናገሩ እሱንም ለማሳካት እላይ ታች የሚሉ ናቸው ብለዋል።
Filed in: Amharic