>

ዛሬ ጋይንት ነበርኩ...!!! (ጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ)

ዛሬ ጋይንት ነበርኩ…!!!

(ጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ)


የወያኔ ጉድና ጉዳጉድ ተወርቶ ስለማያልቅ እንደተለመደው በሪፖርታዥ አቀርብላችኋለሁ:: እስከዛው ግን ካየኋቸው ጥቂቱን ብቻ ላንሳ::
በዓለም አቀፍ ሕጎች በግልፅ እንደተቀመጠው ሆስፒታሎችን ሆን ብሎ ማጥቃት የተወገዘ የተነወረ ድርጊት ነው:: በነፋስ መውጫ ሆስፒታልና በከተማይቱ የሚገኙ ሌሎች 7 ክሊኒኮች ላይ የተፈፀመው ጥቃት እጅግ አሳፋሪ ነው::

የምፅፈው በቦታው ተገኝቼ ያየሁትን ብቻ በመሆኑ እንጂ ተመሳሳይ ጥፋቶች በሌሎችም ቦታዎች መፈፀማቸውን እናውቃለን:: ሆን ተብሎ በክፋትና በሸር በመነሳሳት ብቻ ወያኔዎች ወንበሮችን ነድለዋል:: መስኮቶችን ሰባብረዋል:: የሆስፒታል አልጋዎችን:በውድ የተገዙ የሕክምና መሣሪያዎችን ሰባብረው ኮምፒውተሮችን አድቅቀው የተረፉትንም አንድ በአንድ እየዞሩ ሀርድ ዲስኮቻቸውን በማውለቅ በፌስታል ሞልተው ወስደዋል::

የሆስፒታሉ ሠራተኞችን መኖሪያ ቤቶችና የትምህርት ክፍሎችን ከጥቅም ውጪ አድርገው መድኃኒቶችን ደፍተው በመሄዳቸው ዛሬ ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ ሥራውን አቁሟል። በኀዘን ልባቸው የተሰበረ ዶክተሮች ነርሶችና የጤና ባለሙያዎች ባዶ እጃቸውን ቀርተው ዛሬም ከየገጠሩ በቃሬዛ መጥተው የሚቃትቱትን ሕሙማን እያዩ ሃዘናቸው እጥፍ ሆኗል።  ለመውለድ መጥተው በምጥ ሥቃይ የሚያዩዋቸውን ወላዶች ለመታደግ ያለ አንዳች የህክምና መሣሪያ የሚችሉትን ለማድረግ ደክመዋል። ልብ ይሰብራል።
ያሳዝናል።
በዚህ ሁሉ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ከመካከላቸው አንዱ ሰብዕናው ጨርሶ ያልተሟጠጠበት የህወሃት ወታደር ያደረገውን ልንገራችሁ። ጓደኞቹ በየክፍሉ እየተዘዋወሩ ያነክታሉ ይዘርፋሉ ይሰባብራሉ። እሱ የገባበት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ቆሞ ዙሪያውን የከበበው የጥፋት ሥራ ሕሊናውን ዕረፍት ነስቶታል።

ከፊቱ ከጠረጴዛው ላይ ከተዘረጉት ወረቀቶች አንዱ  ላይ የተፃፈ ስልክ ቁጥር ያያል። ከሆስፒታሉ ሠራተኞች ያንዷ ነው። ሞባይሉን ያነሳና ይደውልላታል “ይውልሽ እዛ ማነው ስሙ … ያለውን ክፍል እኔ አልነካሁም። ሌላውን ይሄው እየሰባበሩ ነው። ግን ይሄ ያንቺ ቢሮ ከሆኔ እ እ እኔ አልነካሁም ። እንዳለ ታገኝዋለሽ” ብሎ ዘጋ። ከሕሊና ወቀሳ ማምለጥ ስለማይቻል እሱን የማይመለከተው መሆኑን ለማሳየት ይሆን? ዛሬ ያነጋገርኳቸው ብዙ ተጠቂዎች እንደሚሉት እግዚአብሔር የሥራቸውን ይስጣቸው ብዬ ላብቃ።

Filed in: Amharic