>
5:22 pm - Saturday July 21, 4468

በየቀኑ ልንሳቀቅ፣ በየቀኑ ልናፍር፣ በየቀኑ ልንቆጣ ይገባል...!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

በየቀኑ ልንሳቀቅ፣ በየቀኑ ልናፍር፣ በየቀኑ ልንቆጣ ይገባል…!!!
ጌታቸው ሽፈራው


1) እስኪ አስቡት! የምንፎክርባት፣ ደም መላሽ የምንላት ወልዲያንኮ ፈጥነን አልደረስንላትም። እንዳልሆች አድርገዋታል። በመልካም ጊዜ በወልዲያ የማይኮራባት ማን ነበር? ደም መላሽ ያላላት ማን ነው?  ለደም መለሻ እንዲህ ነው የሚደረገው? ግን ለደም መላሽ አልሆንንም። አወደሟት።  በጋይንት መስመር ለአንድ ሳምንት በነበራቸው ወረራ ያወደሙትን ምን ያህል ሰቅጣጭ እንደሆነ እያየን ነው። ወልዲያንኮ ከርመውባታል። ከበዋት ከረሙ። የንፁሃንን መኖርያ በከባድ መሳርያ  ደጋግመው ደብድበዋል። ገብተው ሰነበቱ። ወልዲያን አስረክበን እንቅልፍ ሊይዘን ይገባል ወይ? በየቀኑ መሳቀቅ ያለብን ሕዝብ ነንኮ። ወልዲያ ያለው ሕዝባችንን በተለየ ይጠሉታል። ያኔ ስልጣን ላይ እያሉ አሳፍሯቸዋል። ለእያንዳንዱ የወልዲያ ነዋሪ መሳቀቅ አለንንኮ። በጠላት እጅ ምን እያደረጉት ይሆን ማለት አለብን። እህቶቻችንና እናቶቻችን ፀረ አማራ ጥላቻ ወዝ ባጠገበው አሸባሪ አባል ይደፈራሉ። በየቀኑ። ህፃናትና አረጋዊያን ይገደላሉ። ወጣቶች ይረሸናሉ። ከሱቅ በደረቴ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ተዘርፎ ወደ ትግራይ ተወስዷል። በምድብ ተከፋፍለውታል። ሰቀቅን ሲያንሰን ነው። እናቶቻችን በጠላት እጅ ሆነው እንቅልፍ መተኛት አልነበረብንም። ማፈር አለብን። አልደረስንላቸውምኮ። የሚሆንባቸውን አስበን መቆጣት አለብን። መቆጣት ያንሰናል!

2) ዓለም የሚያውቀው፣ እኛ ምልክት የምናደርገው ላሊበላ በወንበዴ እጅ ነው የከረመው። ጥንታዊት ከተማ፣ ቅርሳችን፣ ሕዝባችን በጠላት እጅ ነው። ምን እንደሚያደርጉት እያሰብን እንቅልፍ ማጣት፣ ባለመድረሳችን ማፈር አለብንኮ። እያሰብን መቆጣት አለብንኮ። በደረሰብን በደል ልክ፣ ሊያዋርዱን በመጡት ልክ አልተቆጣንም!

4) ሰቆጣና አካባቢው በአሸባሪው ትህነግ እጅ ነው። ልማት ተነፍጎት፣ ሩቅ ሆኖ የኖረ ወገናችን ነው። አሸባሪው መጥቶ የዚህን ሕዝብ መከራ አክፍቶብናል። እህትና እናቶቻችን ተደፍረዋል። ታላላቆች ያለ እድሜያቸው ተከላትመዋል። ህፃንና አዋቂ ሳይሉ እየገደሉ ነው። በየቀኑ በትህነግ እጅ ምን እየሆኑ እንዳሉ አስበን መቆጨት አለብን። ቶሎ ስላልደረስንላቸው ልናፍር ይገባል። ቶሎ ለመድረስ የመጨረሻውን ብስጭትና ንዴት፣ እልህና መቆጣት ያስፈልገናል። አልተቆጣንም! መቆጣት ያንሰናል!

5) አሸባሪው ትህነግ በአዲሱ ወረራው መጀመርያ  ከፍ ያለ በቀሉን ያደረሰው ቆቦ ላይ ነው። ቆቦ በከባድ መሳርያ አሳሯን አይታለች። ቆቦ እንደ ጉድ ተዘርፋለች። የተቀደደ ኬሻ አልቀረም። ሰባራ ሰንጣራ አልተውም። ደግሞ ከሁሉም ቆቦ ላይ ከረሙ። ኦነግ ሸኔ የሚባል አረመኔ ያፈናቀላቸው ወገኖቻችን እንኳን ከቆቦ ዳግመኛ ተፈናቃይ ሆኑ። ቆቦ አሳሯን አይታብናለች። ምን እየተፈፀመ እንዳለ እያሰብን በየቀኑ መሳቀቅ አለብን። እንደ ሕዝብ አቅም ሳያንሰን በአስቸኳይ ደርሰን ይህን አረመኔ ቡድን ጠራርገን ስላላስወጣን ማፈር አለብን። ውርደት ነውኮ! አሁንም መቆጨት አለብን። መቆጣት! መቆጣት! መቆጣት!

6) መሻገር የሌለባቸውን ተከዜን ተሻግረው እስከ ዋልድባ ብዙ ጥፋት ፈፀሙ። መናኝ  አባቶቻችንም ሳይቀር ተገደሉ፣ በአሸባሪ እጅ ተዋረዱ፣ ተሰቃዩ፣ በቀን አንዴ የሚመገቧት ጭብጥ ለማትሞላ  ምግብ የምትሆን ዱቄትም ተዘረፈች። ተበላሸች። ጭራሽ ስልጣን ላይ እያሉም የእኛ ፋኖዎች “ዱር ቤቴ” ያሉበት አካባቢም ጭምር የትህነግ አሸባሪ ኃይል እኛ ላይ ጥቃት የሚያደርስበት ሆኗልኮ። ተከዜን የተሻገረ ኃይል አድርቃይ እስከ ሰቆጣ ሲገባ እንደ ሕዝብ ተግተልትሎ ነው። በዛ መንገድ ከመመለስ ይልቅ  የማይሆን ነገር ስናኝክ፣ የሚያጠራጥር ነገር አውጥተን ስናሰጣ እንጅ ስንቆጣ አንታይምኮ።

7) አያያዛችንን አይተው ባሕርዳር ሊገቡ ነበርኮ። በጋይንት መስመር ተጋድሎ ባይደረግ፣ ገበሬው በግሉም ባይፋለም፣ እኛም ትንሽ ባንቆጣ ባሕርዳር ገብተው አማራው ለዘመናት የሞራል ውድቀት ውስጥ እንዲገባ ሊሰሩብን ነበር። ጌታቸው ረዳ በአማራ ቲቪ ተጎልቶ እጁን እያወናጨፈ በአማራ ሕዝብ ላይ ሊቀልድ  ነበር ፍላጎቱ። በዚህ በኩል እንኳን በመጠኑ ተቆጣን! በሳምንት አሳፍረን መለስናቸው። ግን  ከዚህ እንዲደርሱ ያደረጋቸው አለመቆጣታችን ነው!

8/ ከተሞችን ያነሳሁት ማጣቀሻ እንዲሆኑ እንጅ የገጠሩ የባሰ ነው። የከተማው ሰው ትነስም ትብዛም በባንክ ይኖረዋል። አርሶ አደሩ ባንኩ ጎተራው ነው፣ የገበሬው ባንክ በረቱ ነው። ጎተራውንም ዘርፈው፣ ቀሪውን ደፍተው አበላሽተውታል። በረቱ ውስጥ ገብተው አርደው በልተዋል። ሌላውን ፈጅተዋል። ማሳውን እንዳያርስ አድርገውታል።  ወረራው ሲብስበት ቀዬውን ጥሎ ተፈናቅሏል። አርሶ አደር ቀየውን ጥሎ ተፈናቅሎ ሲመለስ ምንድን ነው የሚያገኘው? ጭራሽ ደሳሳ ጎጆውንም አቃጥለውታል። ሲመለስ ምን ያገኛል? ሰብሉን የተረፉት እንሰሳት ጋጥ አድርገው ይበሉታል። ከአሸባሪው አባላት አምልጠው ሻካ የገቡ ፍየሎች የቀበሮ፣ ዶሮዎቹ የዱር ድመት፣ ላሞቹ የጅብ ራት ናቸው።  ቤት የሚውሉት ግልገልና ጥጆች እንኳን መጠለያም የላቸውም። የአውሬ ምግብ ናቸው። ሲመለስ ምንም አያገኝም! በገጠሩ ሕዝብ ላይ የደረሰብን የትህነግ ወረራ እጅጉን አስከፊ ውድመት ያደረሰ ነው። ለአርሶ አደሩ ወገናችን እንኳን ፈጥነን፣ በወረራው ልክ አልደረስንምኮ። በአርሶ አደሩ ላይ እንደተፈፀመው አልተቆጣንምኮ!

ግን ለመቆጣት ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረብርሃን፣ አዲስ አበባ መድረስ የለባቸውም። ክብራችን የተነካው፣ የተዋረድነው አንድ ስንዝር መሬት መርገጥ ሲጀምሩ ነው። በኦፍላ ገብተው ሙስሊም ወገኖቻችን ሲጨፈጭፉ ክፉኛ ተቆጥተን ቢሆን ኖሮ አንደኛዋ የልብ ትርታችን የሆነችውን ወልዲያን አያወድሟትም ነበር። ቆቦን አይጨክኑባትም ነበር። ላሊበላን የመሰለ ምልክታችን በእነሱ እጅ አይወድቅም ነበር።  ጋይንት ድረስ አይደፍሩንም ነበር። ተከዜን ለመሻገር ሲክለፈለፉ ብልጨክን ኖሮ ይህ ሁሉ ውድመት አይደርስም ነበር።

እንዴት እንቅልፍ ይይዘናል?

ገበሬው እርሻውን ትቶ ጠላት ጋር እየተፋለመ ነውኮ! ምስኪን እናት በረንዳ ላይ ፀሐይ ሲደበድባት ውላ ያፈራችውን፣ ወጣቱ መንገድ ላይ ሸጦ ያገኘው ሳይቀር ተዘርፏል። የነገ ተስፋዎች እየተረሸኑ ነው። አሉን ያልናቸው ተቋማት ተመዝብረው፣ ወድመዋል። እናቶች እንደ ድሮው ቤታቸው ሲወልዱ እንዲሞቱ የሕክምና ተቋማት በሙሉ ወድመዋል። ህፃናት እንዳይማሩ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ወንደመዋል። ለመሸከም  የማይመቸው አግዳሚ ወንበራቸው እንኳን አልቀረም። ይህ ሁሉ ሆኖ በወረራው ልክ መቆጣትኮ አልቻልንም።

እንደ ሕዝብ በየቀኑ ልንሳቀቅ፣ በየቀኑ  ልናፍር፣ በየቀኑ ልንቆጣ ይገባናል!

ማፈርማ ያንሰናል። ይህን ሁሉ ወረራ ለመቀልበስ በግላቸው ተደራጅተው ቀያቸውን አናስነካም ብለውኮ እየተፋለሙ ለሚገኙት ፈጥነን አልደረስንም። በቃታ ብረት አውቶማቲክ መሳርያን ብቻ ሳይሆን ታንክ ጋር እየተፋለሙ ለሚገኙት ጀግኖቻችንኮ በሚገባን መጠን ደጀን አልሆንንም። እነሱ በዝናብ፣ ብርድ፣ በፅሐይ ወዘተ ከምሽግ አልወጡም። እኛ ግን ይህን እያስታወስን በአስተዋፅኦችን ማነስ አላፈርንም። ለሚያደርጉት ተጋድሎ የሚገባውን እገዛ ባለማድረጋችን አልተቆጨንም። እየደረሰብን ባለው ልክ አልተቆጣንም!

እንደተወረርን ነን! ያውም በደመኛ ጠላታችን!

ሕዝባችን በጠላት እጅ ነው!

ልናፍር! እንቅልፍ ልናጣ! ልንቆጣ ይገባል!

መቆጨት!

መቆጣት!

መቁረጥ! ያንሰናል!

Filed in: Amharic