>

ሕወሓት ምንድነው..? ለማን ታገለ..? አሁንስ በትራፊው ለማን እየታገለ ነው...? (ኢትዮ 12)

ሕወሓት ምንድነው..? ለማን ታገለ..? አሁንስ በትራፊው ለማን እየታገለ ነው…?
ኢትዮ 12


« …. አርባ ምናምን ዓመታት ከጥፋት መማር ዕዳው የሆነ ‹‹ነፃ አውጪ›› ተብዬ ቡድን የተጣባት የትግራይ እናት፣ ለዚህ ትግል ልጆቿንና ቁራሿን ስትገብር፣ ከዛሬ ነገ ቀን ይወጣልኛል እያለች ስትጓጓ ኖራለች፡፡ ለዚች እናት ‹‹አይዞሽ ደረስንልሽ›› የሚሏት ልጆች አሏት ወይስ እየጓጉ መሳቀቅ፣ በጦርነት መታመስ፣ እያነቡ ወደ ፈጣሪ ማመልከት፣ መሰደድና ከምፅዋት ጋር መቁረብ የዕድሜ ዘመን ዕጣዋ ነው?»

የትግራይ ሕዝብ ለሕወሓት ጦረኞች ምናቸው ነው..?

የ‹‹ሕወሓት›› ስሙ የሚናገረው ስለ‹‹ሕዝብ ሐርነት›› ነው፡፡ ለ‹‹ሕዝብ ሐርነት›› ደግሞ፣ ከድህነትና ከአፋኝ አገዛዝ የሕዝብ ነፃ መውጣት ዝቅተኛ ትርጉሙ ነው፡፡ ሕወሓት ግን ከበረሃ ትግሉ ጊዜ አንስቶ በትግራይ ምድር ውስጥ ሌላ የፖለቲካ ሐሳብና የድርጅት አማራጭ ብቅ እንዳይል አፍኖ (ብቅ ያሉትን ገድሎ) የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት ጋር ብቻ እንዲቆራኝ፣ ከሌላ የኢትዮጵያ ቡድኖችና ትግሎች ጋር እንዳይሸራረብና ፈጣን የለውጥ ውጤት እንዳያገኝ ያደረገ (በዚህም የትግራይን ወጣት ልጆች መስዋዕትነት በገፍ ያበዛ) ቡድን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለምን? ተፎካካሪ ሐሳብና ድርጅት አጠገቡ እንዳይኖር ሲል ብቻ፡፡ የትግራይን ሕዝብ የአንድ ሕወሓት አምላኪና አንጋጣጭ አድርጎ በመጨረሻ ያስገኘው ውጤት ቢኖር ትግል በማስፋፋት ስም መሬት መስረቅ (‹‹ነፃ ማውጣት››) ብቻ ነበር፡፡

ሕወሓት በኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ብሔርተኛ ሎሌ ገዥዎች ዘርግቶ  ‹‹በብሔር እኩልነት›› እያጭበረበረ፣ በስላላ፣ በሸርና በኃይል ሰቅዞ አፄነቱን እያካሄደ ሳለ፣ ትግራይ ላይ የፍትሕንና የፖለቲካ ነፃነትን ፀሐይ ሊያበራ አይችልም፡፡ በሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ይካሄድ የነበረው በደል ሁሉ በትግራይ ውስጥም ነበር፡፡ የፖለቲካ መብቶች አልባነቱ፣ ሕወሓትን መቃዋም ትግራይን እንደ መካድ መቆጠሩ፣ የብሔረሰቦች እኩልነት በቋንቋ ደረጃ እንኳ መጓደሉ፣ በአንድ ለአምስት መዋቅር የሰዎች መንደር ድረስ መቀርቀብ ሁሉ ትግራይ ውስጥ ነበር፡፡ የኢሮብ ሕዝብ፣ የአጋሜ ሕዝብ፣ የእንደርታ ሕዝብ… የየራሱ ብሶት እንዳለው አሁን አሁን ብዙ እየሰማን ነው፡፡ በራያና በወልቃይት ሕዝብ ላይ የደረሰው ደግሞ ከአፈናም በላይ ነው፡፡ የማንነት መገለጫ አካል የሆነውን ዝንቅ ባህልንና/አማርኛ ተናጋሪነትን ደፍጥጦ የትግርኛ ብቻ ተናጋሪ ማድረግ፣ የሕዝብ ክምችትን በስግሰጋና በማሰደድ መቀየር ሁሉ የተካሄደበት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የተካሄደው ከሕዝብ ይልቅ መሬት ለሕወሓቶች በልጦባቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በነፃነት ትግል ስም የሰረቁትን መሬት እንኳ፣ ሕዝብን በመብትና በልማት በመንከባከብ አማካይነት በትግራይ ውስጥ እንዲዘልቅ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በግፍ ሥራቸው የወልቃይት ጠገዴና የራያ ሕዝብ ከትግራይ ልቡ እንዲሸፍት (መሬቱም እንዲሸፍት) አደረጉ፡፡ ይህንን በደንብ ያስተዋለ ፈራጅ ማለት ያለበት የአማራ ክልል መሬት ነጠቀ ሳይሆን፣ ሕወሓቶች መሬት ካልወሰድክ ብለው ሰጡት ነው፡፡ በዚህም ዳፍንታምነታቸው ‹‹የነፃ አውጪነታቸውን›› ብቸኛ ቀሪ ይዘት (መሬትን) እንኳ ከትግራይ ጋር እንዲቆይ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ‹‹ነፃ አውጪነታቸው›› ኦናውን ቀረ፡፡

ኦናነቱ በመሬት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በትግራዊ ፓርቲነት ከትግራይ ሕዝብ ጋር ያላቸው ተዛመዶ ከቅርፊት ያልዘለለም ነው፡፡ የዚህ ቡድን ትግራዊነት ለትግራይ ሕዝብ ዕዳ ነበር፡፡ በቡድኑ ግፈኛነት፣ ሸርና ዘረፋ የትግራይ ሕዝብ የተረፈው የስሙ መነሳት/መታማት ነበር፡፡ በትግራይ ውስጥ ቡድኑ ያቋቋማቸው ኩባንያዎችም ከትግራይ ሕዝብ ጋር ያላቸውም ዝምድና የልጥ ነው፡፡ የሕወሓት ጎጠኝነትም ሆነ ብሔርተኛነትም ልጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ በፊት ተገልጦልኝ ነበር? በፍፁም፡፡ በፊት ሕወሓትን ‹‹ጎጠኛ/ብሔርተኛ›› አድርጌ ነበር የማስበው፡፡ የቡድኑ አውራዎች ከአዲስ አበባ ዘወር ብለው መቀሌ ከተሰባሰቡ በኋላ የሄዱበት ጎዳና እስከ ዛሬ በጠቅላላ በኢትዮጵያም ሆነ በትግራይ ሕዝብ ላይ ባደረሱት በደል ተፀፅቶ ወደ መካስ (ወደ ዕርቅ፣ ወደ ፍትሕና ልማት) ከመመለስ ይልቅ፣ ወደ ባሰበት ጥፋት መሆኑ ዓይኔን ገለጠው፡፡ 27 ዓመታት ቡድኑ በገዛበት ከፋፍሎ የማናቆር ሸር እንደማፈር ጭራሽ በየአቅጣጫው ግጭትና ቁርቁስ እያያያዘ ኢትዮጵያን ለመበታተን በማሴር ተጠመደ፡፡ ከሰማይ የተሰጠው ዕጣው እስኪመስል ድረስ የጦርነት ማሳነት የለማበትን የትግራይን ሕዝብ፣ እንደገና ወደ ጦርነት ለመክተት በጀትና ጥሪቱን እየተሻማ ወታደር ማሰናዳት ውስጥ ገባ፡፡ ወዲህ ቢል ወዲያ፣ ኢትዮጵያ አልበታተን ስትለውና የአገሪቱ የመከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስና የደኅንነቱ አውታራት ከ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› እየተላቀቁና ኅብረ ብሔራዊ አመራራቸው እየጨመረ ሲሄድ፣ ኢትዮጵያን በትኖ ኤርትራን ወርሮ ‹‹ታላቋን ትግራይ›› የመፍጠር ቅዠታም ዕቅዱ ከዓይኑ እየራቀ መሄዱ ተሰምቶት፣ ወገኔ ብሎ ያመነውን የሰሜን ዕዝ የትም ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን ጨፈጨፈ፡፡ በዚህም አድራጎቱ ዝምድና ነሽ፣ ውለታና ምሥጋና ነሽ የማያውቅ ግፈኛ መሆኑን ለኢትዮጵያም ለትግራይም ሕዝብ ያጋለጠ የፖለቲካ ሞት መሞቱን አረጋገጠ፡፡ የትግራይ ሕዝብም በብሔር ስሙ ስለሚነግደው ውለታና ዝምድና የማያውቅ ጨካኝነት ተሰቀቀ፣ አፈረ፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በማጅራት ከመታረድና ከመታገት የተረፈውንና ለክህደት ያልተበገረውን ቀሪ የሰሜን ሠራዊት አሰባስቦ ነፈሰ ገዳዮችን እየቀጣ ድል በድል ላይ ደርቦ በዋና ዋና የትግራይ ከተሞች ሲገባ፣ የትግራይ ሕዝብ ያለ ኮሽታ (ለሕወሓቶች ‹‹ተነስ! ተኩስ!›› የሚል ቅስቀሳ ጆሮ ሳይሰጥ) መቀበሉ፣ ከሕወሓት የተሻለ አማራጭ የመሻቱ ምስክር ነበር፡፡

ነገር ግን በፖለቲካ ድጋፍና በድርጅታዊ መዋቅር የረባ የሕዝብ ሥር ያላበጁት፣ እንዲያበጁም ዕድል ያላገኙትና የሕወሓት ወመኔ ገዥዎች ‹‹ባንዳ›› የሚል ስም የለጠፉባቸው በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ የሚያስቡት የሕወሓት ተቃዋሚዎች በየትኛው አቅማቸው በሜዳ የተዘራውን የሕወሓት ካድሬ ሸር ሊቋቋሙ! ለሕዝብ ማሰብ ያልፈጠረባቸው የሕወሓት ወመኔዎች ሰነድ አጥፍተው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የወህኒ እስረኞችን በትነዋል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መዋቅር ውስጥ ደህና መስለው የተሰገሰጉ የወመኔው ቡድን ተቀፅላዎች ጊዜያዊ አስተዳዳሩን ከወሮበላ እንኳ የማያድን አድርጎ ሸፍጥ ለመሥራት ችግር አልነበረባቸውም፡፡ ሕዝብን በሰላም ማጣት፣ በግጭትና በዝርፊያ መድረሻ እንዲያጣ አድርጎ ኢሕአዴግ ሕወሓትን ሙጥኝ እንዲል ማድረግ፣ (ፍንዳታ አፈንድቶ ተቃዋሚን ማስጠርጠርና መወንጀል፣ የትግራይ ሰዎችን ሳይቀር በትግራይ ሆቴልና በሌሎችም ሥፍራዎች በፈንጂ ረፍርፎ ትግራዊ በፀረ-ትግራዮች እንደተጠቃ ማስመሰልና ያለ ሕወሓት በቀር መጠጊያ የለሾች እንደሆኑ እንዲያስቡ ማድረግ) 27 ዓመታት ሙሉ የተካኑበት ነው፡፡ የሸር ቁንጮዎቹ ከመቀሌ ከወጡም በኋላ ቢሆን፣ አስቀድሞ ያዘጋጁት የሸር ፋብሪካቸው ከውስጥም ከውጭም ሥራውን በደንብ ይሠራ ነበር፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሠራዊት የደንብ ልብሶችን አልብሶ ዘረፋ፣ ግድያዎች፣ የሴቶች ደፈራ የማካሄድ፣ በቤተ እምነት ላይ ጥቃት የመፈጸም ሻጥሮችን ያካሂድ ነበር፡፡ ያልተፈጸሙ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን በምሥልና ‹‹በዓይን ምስክሮች›› አስደግፎ ይፈበርክ ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ በውጭ በከፈተው ሚዲያ እያራገበ የትግራይን ሕዝብና የዓለምን ግንዛቤ ለማደናገር ሠርቷል፡፡ ከሕወሓት ፍላጎትና መረብ ጋር ውስጠ ሚስጥር ያላቸው ምዕራባዊ አገሮችና ሚዲያቸውም ደህና አድርገው አራገቡለት፡፡ ማደናገሩም በውስጥና በውጭ ያዘለት (ከቀጣፊ ድርጊታዊና ምሥላዊ ቅንብሮቹ ባሻገር፣ የወልቃይት ጠገዴና የራያ ከሕወሓት ግፍ መላቀቅ ከትግራይ ከመቀነስ ጋር አንድ ተደርጎ መቆጠሩም የትግራይን ሕዝብ ለማሸፈት ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል)፡፡

እናም በፊት መሣሪያ እዚህ አለ ብሎ መምራት ጀምሮ የነበር ሕዝብ በስተኋላ ደግሞ ለሕወሓቶች ጫካ ከመሆን አልፎ የጥቃት ተሳታፊ ወደ መሆን ይዞር ገባ፡፡ ከዚሁ ጋር ክረምቱም መጣ፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የአካባቢ መንግሥታት በርብርብ ወደ ትግራይ ያፈሰሱት ከአቅም በላይ ዕርዳታ (የምዕራቡ ዕርዳታ የረባ ባልሆነበት ሁኔታ) ሲያልቅ እየተኩ ሊቀጥሉበት የማይችሉት (ለመቀጠል ቢሞከር ተያይዞ በዕጦት መንኮታኮት ይሆን) ነበርና፣ የዚህ ክረምት ግብርና እንኳን ሊዘለል ስኬታማ መሆኑም የህልውና ግድ ነበር፡፡ እናም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር ለግብርና የሚያስፈልገው የሰላምና የደኅንነት ነገር እየባሰበት ከመጣ፣ የትግራይ ሕዝብ አነሰም በዛ ግብርናው ላይ አተኩሮ ከረሃብ ነፍሱን እንዲያድን፣ የፌዴራል መንግሥት መጠባበቂያ የዕርዳታ ክምችትንና የግብርና ግብዓቶችን አሰናድቶ፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ በተናጠል ተኩስ ማቆሙና ጦር ከትግራይ ማውጣቱ ኃላፊነት የሚሰማው ተግባር ነበር፡፡

የተናጠል ተኩስ ማቆሙ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ተካሂዶ የተከተለው ነገር ግን፣ የሕወሓት ጦረኞች ወገኔ የሚል ርኅራኄና አሳቢነት ከቶም የሌላቸው መሆናቸውን ለእኔም ለሌላውም ወለል ያደረገ ነበር፡፡ ለሕወሓት ሎሌ ከመሆን አፈንግጠው ነበር የተባሉ ሰዎችን፣ የጊዜያዊው አስተዳደር ታማኝ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎችንና የኤርትራ ስደተኞችን በበቀል መግደልና ማጥቃት ውስጥ መግባታቸው በአድራጎትነቱ አይደንቅም፣ በቀል ልማዳቸው ነውና፡፡ የትግራይ ሕዝብም እንደ መካከለኛው ዘመን ሰው ለሕወሓት አበጋዞች መስገድና መገበር የኑሮ ግዴታው ነው፡፡ እንዲህ እየኖረም ለዚህ ክረምት ያህል እንኳ የዕርዳታ ያህል እየበላ ተረጋግቶ እንዲያርስ ቢታዘንለት ደግ ነበር፡፡ እነሱ ግን ለትግራይ ሕዝብና ለስደተኛ የተከማቸ የዕርዳታ እህል ከመዝረፍ አልፈው፣ ሴትና ወንድ ሕፃናትን ለውትድርና እየመለመሉና ከአዛውንቶች ጋር ጋፍፈው ከፊት እያጎረፉ ከጦርነት ጋር አጋፈጡት፡፡ ይህንን እንዴት ያለ ህሊና ይችለዋል! የጭካኔ ሥራቸው፣ ሕፃናቱና አዛውንቱ ከፊት የቀደሙት ወደው ነው ወይስ በግዳጅ ከሚል ጥያቄ ጋር አይያያዝም፡፡ ወደው እናድርግ ቢሉ እንኳ የሕዝባዊነት ቅንጣት ነፍስ ያለው ቡድን ፍላጎታቸውን አይጠቀምበትም፡፡ የሕወሓት ጦረኞች ግን ዱርዬ የፖለቲካ ጥቅም ለመግዛት የማይሸጡት ምንም ነገር እንደሌለ፣ (አገር፣ የአገር ልጅ፣ የብሔር/የወንዝ ልጅ የሚባለው ሁሉ ሊቀወር እንደሚችል) በጠራራ ፀሐይ አሳዩን፡፡ ይህ ወሰን የለሽ ባለጌ ንግዳቸው በህሊናዬ ውስጥ ሲከመር፣ ከዚህ በፊት ለአንዴም አምኜውና በጽሑፌም ተጠቅሜበት የማላውቀውን፣ የትግራይ ተወላጆች ጭምር ይመሰክሩት የነበረው የሕወሓቶች ወንጀል ፊቴ ተደቀነብኝ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከደርግ ተቆራርጦ ወደ በረሃ ልጆቹን እንዲያተምምለት ሕወሓት የሐውዜን ጭፍጨፋን በሥውር እጅ ጋብዟል፡፡ በ1977 ዓ.ም. ረሃብ ጊዜም የዕርዳታ እህል ከረሃብተኛ ጉሮሮ ቀንሶ ጦር መሣሪያ ገዝቶበታል ሲባል የቆየውን ክስ ዛሬ ምን ይዤ ልጠራጠረው? የእነሱን ልጆች ፈረንጅ አገር አሽሽተው የትግራይ መናጢ ሕፃናትንና አዛውንቶችን እንደ ከሰልና እንደ ጭራሮ ሲማግዱ እየታዘብኩ፣ እንዲህ አድራጊዎቹን ምናቸውን ይዤ ብሔርተኛ/ጎጠኛ ልበላቸው? ቢጤዎቻቸው (ከፈረንጅ አገር) በሞቅታ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም! ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን!›› ሲሉ፣ እየሠሩ ያሉትን እውነት ማመናቸው ነበር፡፡ የአገርንና የወገን ትርጉም ሳያውቁ፣ የአፄ ዮሐንስና የራስ አሉላ የተጋድሎ ልጅነት ሳይኖርባቸውና ለትግራይ ሕዝብ ጉስቁልና ትንሽም ርኅራኄ ሳይፈጥርባቸው ‹‹ትግራዋይ ነን›› ብለው በአፋቸው ሙሉ ለመናገር መድፈራቸው ግን የሚያንከተክት ነው፡፡

ሕወሓቶች ‹‹ማርክሲስትነታቸው››፣ ‹‹አብዮተኛነታቸው››፣ ‹‹ተራማጅነታቸው››፣ ብሔርተኛነታቸው›› እና ጎጠኝነታቸው …

ሁሉ እንደ ቀይ ሽንኩርት ተልጦ ተልጦ ምን ተፈጥሮ ቀራቸው? ቀይ ሽንኩርትን ልጠን ልጠን እንደምንደርስበት እንጨትማ ዘንግ ከእነሱም የቀረው ጥላቻና ቂምን፣ ሸርና ሴራን፣ የሐሰት ቱልቱላን፣ በቀልን፣ ነፍሰ ገዳይነትንና አጋዳይነትን፣ ዘርፎ በሌነትንና ጦረኛነትን ምሱ ያደረገ የዲያቢሎስ ቁራጭነት ነው፡፡ ከእነ ጌታቸው ረዳ ጠመንጃ ነካሽነት እስከ ‹‹ዲጅታል ወያኔ›› ድረስ ያለው ትስስር የዲያቢሎስ ቁራጮች ክበብ ነው፡፡ ነጋ ጠባ የሚያባዝታቸው ለሕዝብ ማሰብ ሳይሆን፣ ምሳቸውን የማሟላት ረሃብ ነው!!

የጽሑፌ ዋና ጉዳይ ውጊያዎችን በማሳደድ ላይ የተጠመደ አይደለም፡፡ ውጊያዎች በፍጥነት የሚለዋወጥ ውጣ ውረድ ሊኖራቸው ይችላልና መልዕክትን በእነሱ ላይ ለማቋቋም መሞከር ከማይረጋ ነገርና በቀላሉ መረጃ ከማይገኝለት (ቢገኝም እንዳሻ ሊጠቀሙበት ከማይችሉት) ነገር ጋር ልወዛወዝ ከማለት አይሻልም፡፡ የሕወሓት ክበብ በሙጣጭ ቀረ፣ ከክላሽንኮቭ በላይ የሌለው ሆነ ብለን እንዳላሰብነው ዋል አደር ብሎ ታንክና መድፍ ወደ መተኮስ ማለፉን ሰማን፡፡ የትግራይን ሕፃናትና አረጋዊያን የጦርነት እሳት ውስጥ ስለመማገዱ ሰምተን ከመንገብገባችን ደግሞ ሲቪል የአማራና የአፋር ሕዝብ ላይ መልከ ብዙ በቀል (አዋቂና ሕፃናትን የመረፍረፍ፣ ሰዎችን በገፍ ከኑሮ/ከግብርና ሥራ የማፈናቀል፣ ሴቶችን የመድፈር፣ ጉርስና ተሽከርካሪ ነክ ንብረት የመዝረፍ፣ አልዘረፍ ያለን በመጋዘን የተከማቸ እህልን ጭምር የማውደም) ማካሄዱን ሰማን፡፡ ምን በደለኝ ብሎ? ማንንስ እጠቅም ብሎ? የትግራይን ሕዝብ እንደ እሱ ዘርፎ በሌ በማድረግ ሊጠቅመው ፈልጎ? ወይስ ትኩስ ግፍ የተካሄደበት የአማራና የአፋር ሕዝብ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከተዘመተብኝማ ብሎ እንዲዘምት በጨካኝ ትንኮሳ ማባበሉ?

የዲያቢሎስ ቁራጮቹ ክበብ የትግራይ ሕፃንና አዋቂ ከልታሞችን ከፊት እያንጋጉ በአማራ ክልልና በአፋር ክልል ላይ ጦር ያዘመቱት ምሳቸው በምስነቱ አቅነዝንዟቸው ብቻ አልነበረም፡፡ ሲቪል ሕዝብ ከሲቪል የሚተጫጨድበት (ገድለው አይፎከርበት) የእርስ በርስ ጦርነት በኢትዮጵያ ተከፈተ የሚያስብል ትርፍን ፈጅቶ በማስፈጀት የሁለት በኩል ደም መግዛት አንዱ ሴራቸው ነበር፡፡ ይህ አልሆን ቢልና በማገዷቸው የትግራይ ሕፃናትና አዛውንት ላይ ዕልቂቱ ቢያይል ደግሞ፣ ‹የትግራይ ሕዝብ (ሕፃናት ከአዛውንት ሳይለይ) የጅምላ ፍጅት ተካሄደበት! እዩ የሬሳ መዓት!!› እያሉ በዓለም ሚዲያ መድረኮች የኡኡታ ቴአትር መሥራት ሌላው አማራጫቸው ነው፡፡ በዚህ ግፈኛ ንግድ ውስጥ የምዕራብ ጌታ አገሮችም እጅ አዳፋ ነው፡፡

ለዲያቢሎስ ቁራጮቹ ክበብ አሜሪካና አውሮፓውያኑ ሙጭጭ ያለ ድጋፍ የመስጠታቸው ሚስጥሩ ምን እንደሆነ መፍታት እስካሁን እንቆቅልሽ ሆኖብን ነበር፡፡ አሁን ግን ከድጋፋቸውም በላይ ትግራይን የራሷ መከላከያ ጦር እንዳላት አገር  የማሽሞንሞናቸው ሚስጥር ኢትዮጵያን ብዙ ትንንሽ አድርጎ ከመበጣጠስ ሴራ ተጋሪነት ጋር የተገናኘ መሆኑን የፈነጠቁ መረጃዎች ብቅ ብለዋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ሌላም ፍንጭ ይፈነጥቃሉ፡፡ የሕወሓት የሰይጣን ቁራጮች ቀደም ብለው፣ የዓብይን መንግሥት ‹‹የፌዴራሊዝም ቀልባሽ››፣ ‹‹የአሃዳዊነት መላሽ›› አድርገው ሲሥሉና ‹‹ፌዴራሊዝምን እናድን›› እያሉ ከቅንጥብጣቢ አሻንጉሊቶቻቸው ጋር የአዳራሽ ቴአትር ሲሠሩ የነበሩት ለእኛ ያህል ብቻ አልነበረም ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያን መበጣጠስ ለአካባቢው ሰላም መፍትሔ አድርጎ ለምዕራባውያኑ የማቅረብ/የማስተማመን ሥራን በቴአትሩና በቴአትሩ በስተጀርባ ሲሠሩ እንደነበር ብንጠረጥር፣ ከእነሱ ባህርይ ትንሿን ነገር መጠርጠራችን ነው፡፡ የሰሜን ጦርን ወግቶና ከዚያም የሚገኘውን ከዳተኛ ኃይልና መሣሪያ በኢትዮጵያ ላይ አዙሮ አዲስ አበባ መግባት፣ ኢትዮጵያን የመበጣጠስ ፕሮጀክትን የማስፈጸም የመጀመርያው ትልቁ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ያ ከከሸፈ በኋላ በረሃብ አደጋና በቀጣፊ ‹‹ጅምላ ጭፍጨፋ›› ውንጀላ የምዕራባዊያን የጦር ጣልቃ ገብነት ‹‹ሰውን ከፍጅት በማዳን ስም›› ቀዳዳ እንዲያገኝ ብዙ ሲሞከር ተቆይቷል፡፡ የአሁኑ የትግራይን ሲቪል ከልታሞች እሳት መማገድና በአፋርና በአማራ ሕዝቦች ላይ ጨካኝ ጥቃት መፈጸምም ያንኑ የምዕራባውያኑን ጣልቃ ገብነት ለመጋበዝ የቀረበ (የእርስ በርስ ፍጅትን ድግሴ ያለ) የደም ማዕድ መሆኑ ነው፡፡ ምዕራባውያኑም ይህንን ሕፃናትንና ሲቪሎችን የመማገድ ግፍ ዝም ያሉት፣ ማጋጆቹን ግፈኞች ትተው ወረራ በመጣባቸው የአፋርና የአማራ ልዩ ኃይል ላይ (ለምን እየሸሻችሁ አልተገደላችሁላቸውም ከሚል ትርጉም ያልራቀ) የጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀል የሚለጥፉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተከዜ ድረስ ሬሳ አውርዶ ምዕራባዊ አዋካቢዎቹን ዝመቱብኝ ብሎ እንደማይማፀን አስከሬኖቹ ራሳቸው አፍ አውጥተው እየተናገሩ ሳለ፣ ቀሽሙ ፕሮጋንዳ የማን ሥራ እንደሆነ በማጋለጥ ፈንታ ምዕራብያኑ የወሬ አናፋሽ የሆኑት፣ የግፍ ወረራ የአማራና የአፋር ሕዝብን ሲያበራይ ግን ድምፃቸው ‹‹ያሳስበናል›› ከማለት ያለፈ ዘለግ ያላለው (ለመኮነን የሚያፍረው)፣ ከአድልኦ ንፁህ ስላልሆኑ መሆኑ ነው፡፡

..ትግራይ ሕዝባዊ የፖለቲካ ልሂቃን አሏት…..?

አርባ ምናምን ዓመታት ከጥፋት መማር ዕዳው የሆነ ‹‹ነፃ አውጪ›› ተብዬ ቡድን የተጣባት የትግራይ እናት፣ ለዚህ ትግል ልጆቿንና ቁራሿን ስትገብር፣ ከዛሬ ነገ ቀን ይወጣልኛል እያለች ስትጓጓ ኖራለች፡፡ ለዚች እናት ‹‹አይዞሽ ደረስንልሽ›› የሚሏት ልጆች አሏት ወይስ እየጓጉ መሳቀቅ፣ በጦርነት መታመስ፣ እያነቡ ወደ ፈጣሪ ማመልከት፣ መሰደድና ከምፅዋት ጋር መቁረብ የዕድሜ ዘመን ዕጣዋ ነው? ይህ ሁሉ እየሆነም፣ ለዱርዬዎቹ የበቀል ምስ ሲባል ከእነ ሕፃናትሽ ነይ እሳት ተማገጅልን ስትባል፣ ‹‹አሁንስ በዛ! ወግዱ!!›› የሚሉ ልጆች ያሏት የት ጋር ነው? ከሕወሓት ውጪ ትግራይ ውስጥ ቡፍ እንኳ የሚሉ ልጆች የሏትም? በሕወሓት ውስጥስ ከዲያቢሎስ ቁራጮቹ የሸር ፖለቲካ የተፋቱ ልጆች አልተረፏትም? ውጊያዎች ላይ ታችና ወዲህ ወዲያ ቢሉም በጦርነታቸው ሲሰደሩ አሸናፊነቱ ወዴት በኩል እንደሆነ መረዳት ከባድ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ የእነ ጌታቸው ረዳ ክበብ እንዴት ያለ የህሊና ማጣት ውስጥ እንደሆነ፣ እየወረረ መጨፋጨፍን በማቀጣጠል ፕሮጀክቱ ከአማራና ከአፋር ሕዝብም ሆነ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ በትግራይ ሕዝብ ላይ ጠላት እንኳ የማይፈጽመውን ጭካኔ እየሠራ (ከማንም ይበልጥ የትግራይ ሕዝብ ሕይወት እንዲዳፋ እየደገሰ) እንደሆነ ማስተዋል ከባድ አይደለም፡፡ ታዲያ ለትግራይ ሕዝብ ልሳን በመሆን ረገድ የፖለቲካ ኦና የተፈጠረ እስኪመስል ድረስ፣ አዲስ አበባ ቢሮ ያላቸው ፌዴራላዊ አንድነት የህልውናና የግስጋሴ ኃይል መሆኑ የገባቸው ትግራዊ ቡድኖች ዝም ያሉት ከዚህ በላይ ምን እስኪፈጠር ነው? በእንቶ ፈንቶ የሚባክን የአየር ጊዜ በሞላበት አገር ውስጥ ኅብረት ቢጤ ፈጥሮ ከትግራይ ሕዝብ ጋር በተከታታይ በቀን ለተወሰነች ደቂቃዎች መነጋገር አልነበረባቸውም? ወይስ ለፖለቲካ ቡድን በልሳንነት ሚዲያ መፍቀድና ለኢትዮጵያ-ትግራይ ህልውና መዋደቅ ተምታቶ ይሆን? አይዞህ አለንልህ ብሎ ለዕጦቱ ማን በቅርብ ተስፋ ይሁነው? ብሶቱንና ጉጉቱን ለማዋየት ማን ነው ቅርቡ? ከኢትዮጵያዊ ዘመዶቹ ጋር ለመወያየት ድልድይ የመሆንስ ቀዳሚ ሚና የማን ይሆን? ከአማራ ክልል የፖለቲካ ልሂቃንና መንግሥት ጋር መክሮ ዘክሮ የመሬት ቅርጫ ጦርነት ውስጥ ሳይገባ የትግራይ ሕዝብን የልማት አቅም ማጠናከር የሚቻልባቸውን አማራጮች ከዙሪያ ወገኖቹ ጋር በመምከርና በዕርቅ መንገድ የመፈለግን ተግባር ከትግራይ ልጆች በላይ ማን ይብሰልሰልበት? የትግራይ ሕዝብ ልማትና ሰላም በጦርነት መንገድ እንደማይገኝ የዓለም ጎስቋላ አገሮች ልምድ ያረጋገጠውና ክርክር የማያስነሳ ነው፡፡ የሕወሓት ጦረኞች ኤርትራን ወርረው ቢሰለቅጡ ከዲያቢሎስ ቁራጮች ጉያ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ሰላምና ልማት ጠብ እንደማይል ቢያንስ የሰላሳ ዓመታት መንግሥትነታቸውና የዛሬ ክራንቻ ጥርሳቸው ትምህርቱን አጉርፎልናል፡፡ የኤርትራ ሕዝብ፣ የትግራይ ሕዝብና ቀሪ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰላምና የግስጋሴ ዕጣ የተሳሰረ መሆኑን ለትግራይ ሕዝብ ለማስረዳትስ ምን መረጃ ቸግሮ! የትግራይ ሕዝብ ሰላምና ግስጋሴ በመነጠል እንደማይገኝ የማሳየትም ነገር፣ አንጋጦ ጣሪያ እየቆጠሩ የሚያሳምን ነጥብ ማማጥን አይሻም፡፡ ኤርትራ ‹‹ነፃ›› አገር ከሆነች ወዲያ ሁለቱ አገሮች በ1990ዎች የመጀመርያ አጋማሽ ውስጥ ያካሄዱት ሰውና ንብረት ያጨደ ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ጦርነት (ዕጣቸው የማይነጣጠል መሆኑን ተቀብለው በሥርዓት ያለማስኬዳቸው የወለደው) ራሳቸውን በራሳቸው የቀጡበት የደም ሰነድ ነው፡፡ ሰነዱ ማንኛችንም እንድንማርበት ተገሽሮልናል፡፡ ከዚህ ባለፈ በእንስሳቱ ዓለም ያለ በህልውና የመቆየት ትግል ሳይቀር፣ በቁጥር በርክቶና በኅብረት ተጋግዞ መንቀሳቀስ ቢያንስ የደኅንነት አቅም ስለመሆኑ ያስተምረናል፡፡እና ምን ቸግሮ ነው በዝምታችሁ የትግራይን እናት የወላድ መሃን የምታደርጓት?

Filed in: Amharic