>

ሕወሓት ለፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ላከ...!!! DW

ሕወሓት ለፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ላከ…!!!

 

 DW Amharic 


የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረ-ጺዮን ገብረሚካኤል፦ ለዘጠኝ ወራት የቆየው ጦርነት «በውይይት እንዲያበቃ» ፍላጎት ማሳየታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ምንጭ ዘገበ። ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ የተላከ እና የዜና ምንጩ ትናንት ዐየሁት ባለው ደብዳቤ ሕወሓት «ገለልተኛ አደራዳሪ» መኖሩን እንደ ቅድመ ኹኔታ ማስቀመጡን ጠቅሷል። ዋና ጽ/ቤቱን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪቃ ኅብረት «ለጦርነቱ ማንኛውንም መፍትኄ ሊያመጣ አይችልም» የሚል ሐሳብም ለተመድ በተላከው ደብዳቤ ላይ መሥፈሩን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የአፍሪቃ ኅብረት ኦሉሴጎ ኦባሳንጆን የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው አድርጎ መሾሙን ትናንት ይፋ አድርጓል። የቀድሞዉ የናጄሪያ የጦር ጄኔራል፣ ፕሬዝደንትና ዕውቅ ፖለቲከኛ በአፍሪቃ ቀንድ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሺን ሊቀመንበር የሙሳ ፋኪ መሐማት ልዩ መልዕክተኛ ሆነዉ የተሾሙት በያዝነዉ ሳምንት ነዉ። የአፍሪቃ ሕብረት ትናንት በድረ-ገፁ ባሳራጨዉ ዘገባ እንዳለዉ ኦባሳንጆ፣ በአፍሪቃ ቀንድ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ከሁሉም ወገኖች ጋር ይነጋገራሉ።
ሐሙስ ነሐሴ 20 ቀን፣ 2013 ዓ.ም የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ቃል አቀባይ (ፕሬስ ሤሴክሬታሪያት) ቢልለኔ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ኦነግ ሸኔ በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን በውይይቱ ተሳታፊ ይሆናሉ ወይ ተብለው ተጠይቀው ነበር። ቃል አቀባዩዋ «ማንኛውም ሕጋዊ የሆነ አካል በውይይቱ ተሳታፊ እንደሚሆን» ተናግረዋል። ውይይቱ አዲስ ሳይሆን ካለፉት ሦስት ዓመታት አንስቶ የቀጠለ ሲሆን፤ ከ54 በላይ  ፓርቲዎችና የተለያዩ የማኅበረሰቡ አካላትን» ያሳተፈ መሆኑንም አክለዋል ተናግረዋል።
ሕወሓት እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው «ኦነግ/ሸኔ» የተባለው ታጣቂ ቡድን በኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖች ናቸው።

Filed in: Amharic