“አሸባሪው ሸኔ በጊዳ ኪራሙ ያደረሰው ጥቃት የሰው ልጅ ጠላት መሆኑን በግልጽ ያመለክታል* ”
አቶ ጌታቸው ባልቻ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ
(ኢ ፕ ድ)
አሸባሪዉ ሸኔ እምነትና ብሄር ሳይለይ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪራሙ ወረዳ በንፁሐን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጥቃት የሰው ልጅ ጠላት መሆኑን በግልጽ የሚያመለክት እንደሆነ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ አስታወቁ።
አቶ ጌታቸው ባልቻ በጥቃቱ ዙሪያ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አሸባሪው ሸኔ እምነትና ብሄር ሳይለይ በምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ያደረሰው ጥቃት አረመኔያዊነቱንና የሰው ልጅ ጠላትነቱን ያሳየ ነው።
አሻባሪዎቹ ሸኔና ህወሓት ለሰው ልጅ የማይራሩ ዘግናኝ ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎች መሆናቸውን ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪራሙ ወረዳ የደረሰው ጥቃት ማሳያ ነው ብለዋል።
አሸባሪው ባካባቢው ባደረሰው ጥቃት ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አርባ ሺ የሚጠጉ ዜጎች መፈናቀላቸውን ያስታወቁት አቶ ጌታቸው፤ መንግሥት ድርጊቱን በፈፀሙ አሸባሪ ኃይሎች ላይ ህግን የማስከበር ሥራ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
በብሄራቸው ስብጥር መግለጽ ከተፈለገ የሞቱና የተፈናቀሉም ሰዎች ኦሮሞ፤ አማራና ሌሎች የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ናቸው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ አንድ አንድ ፅንፈኛ ኃይሎች ጥቃቱን እምነትና ብሄር መልክ በማላበስ ሌላ አጀንዳ ለመፍጠር መሞከራቸው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።
በሰዉ ልጅ ደም አጀንዳቸው ግብ እንዲመታ የሚፈልጉ ኃይሎች ሊታረሙ ይገባል ያሉት አቶ ጌታቸው ፣ እስከአሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሸባሪው ሸኔ ውእምነትና ብሄር የለውም ፤ የሰዉ ልጅ ጠላት ነው ብለዋል።