>
5:18 pm - Tuesday June 14, 1983

ኢትዮጵያ እና ሳማንታ ፓወር በሰብዓዊ እርዳታ ስም ፣ወታደራዊ ጡንቻን የማጠንከር አባዜ (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ኢትዮጵያ እና ሳማንታ ፓወር በሰብዓዊ እርዳታ ስም ፣ወታደራዊ ጡንቻን የማጠንከር አባዜ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


 

የተባበረችው አሜሪካ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድ ዋና ሃላፊ የሆኑት ሳማንታ ፓወር ወደ ኢትዮጵያ ምድር ከባድ ተልእኮ ነበር ይዘው የመጡት፡፡ ሳማንታ ወደ ኢትዮጵያ ከማቅናታቸው በፊት የሞቀ እና ደማቅ አቀባበል እንደሚገጥማቸው ጠብቀው ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ማናቸውም የአሜሪካ ልኡካን ቡድን ወደ አንድ ወደ ሌላ ሀገር ለጉብኝት ሲሄዱ የሞቀ አቀባበል እንዲደረግላቸው ይጠብቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ ምድር የጠበቃቸው አቀባበል ቀዝቃዛ ክንድ ነበር፡፡ ከጉብኝታቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚንስትር ለማግኘት ፕሮግራም እንዲያዝላቸው ቢጠይቁም በተለያዩ ምክንያቶች ያሰቡት አልተሳካም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ባመይገኙበት በማናቸውም ግዜያት ተክተዋቸው የሚሰሩትን ምክትል እና የውጭጭ ጉዳይ ሚስትር አቶ ደመቀንም ማነጋገር እድሉ አልገጠማቸውም ነበር፡፡ ሳማንታ የኢትዮጵያን ምድር ከረገጡ  በኋላ የመጡበትን ጉዳይ ያስረዱት በሚንስትር ደረጃ ላሉ አንዲት ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣን ነበር፡፡

ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የተነሳ የተባበረችው አሜሪካ ሁነኛ የፖለቲካ ሰው የሆኑት ሚስስ ሳማንታ በእርዳታ አዘገያለሁ ወይም እከለክላለሁ በሚል የተለመደ ጫና ለማሳደር ሁኔታዎች አልተመቻቹላቸውም ነበር፡፡ ከአሜሪካ ፕሬዜዴንት ሚስተር ጆ ባይደንም በቀጥታ ይዘው የመጡትንም መልእክት በቀጥታ ለማስፈጸም አስበው ነበር፡፡ ቀጥተኛ መልእክቱ የሚከተለው ነበር፡፡‹‹ ተቐመጡ እና ከአሸባሪው ህውሃት ጋር ተነጋገሩ የሚል ነበር›› ይህ ትእዛዝ ነበር፡፡

ሚስስ ሳማንታ አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ነሀሴ 4 ቀን 2021 በሸራተን አዲስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይን ማግኘት እንዳልቻሉ ከገለጹ በኋላ ገለልተኝነታቸውን አጠራጣሪ የሚያደርግ ዲስኩር አሰምተዋል፡፡ ይህ የሚያስገርም አይደለም፡፡ የአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች ከብሔራዊ ጥቅማቸው አኳያ የሚሰጡት አስተያየት ምንግዜም ቢሆን ተመሳሳይነት አለው፡፡ ሴትየዋም የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ እሩቅ እንደሚጓዙ እሙን ነው፡፡ ‹‹ ሁሉም አማራጭ በጠረቤዛው ላይ ተቀምጠዋል ››All options are on the table, ካሉ በኋላ ስለ የተባበረችው አሜሪካ ጣልቃ ገብነት በተመለከተ፣ በሱዳን በኩል የሰብዓዊ እርዳታ ኮሪደር (humanitarian corridor from Sudan ) መከፈት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ እጅግ መጠነ ሰፊ እና አውዳሚ የሆነውን የአሸባሪውን የወያኔ ጥቃት መከላከሏ፣ በአፍሪካው ቀንድ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳይከሰት የምታደርገው ጥረት ለተባበረችው አሜሪካ እንደ አጋርነት የሚቆጠር መሆን ነበረበት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የባይደን አስተዳደር ግራ የሚያጋባ እና ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል መግለጫ ሲያወጣ መስማት የጠለመደ ሆኗል፡፡

ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደሚሰማው በአፍሪካው ቀንድ የተባበረችው አሜሪካ ልዩ ልኡክ ሆነው የተሾሙት ጄፈሪ ፌልት ማን በመባል ይጠራሉ፡፡  (The administration appointed Jeffrey Feltman as a Special Envoy for the Horn of Africa.) እኚህ ሰው (ጄፍሪን ማለቴ ) ነው የፖለቲካው ጨዋታ ቴክኒሻን ናቸው፡፡ ስለሆነም በውስጥ አሸባሪ ቡድን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እና ጥቃት በደረሰበት የኢትዮጵያ መንግስት ፣ እንዲሁም በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጠብ ጫሪነት የተነሳ አስከፊ ውጤት ሊከሰትባት በሚቸችልባት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ስልጣን በጄፍሪን እጅ ስር ወድቃለች፡፡

ከረን ዲፕሎማሲ (Karen diplomacy) ከረን( Karen) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአማርና ቋንቋ ሲተረጎም ከትክክለኛ ወይም አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሴቶች ባህሪን የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ ነጭ ሴቶች በተለይም የምእራቡ አለም ፖለቲከኞች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ እንዲራዳቸው የሚያቀርቡትን ጥያቄ የሚያመላክት ቃል ነው፡፡ ለአብነት ያህል ሳማንታ ፓወር በቅርቡ ለኢትዮጵያ መንግስት ያቀረቡት ጥያቄ ይሄን ቃል ያመላክታል፡፡ ለማናቸውም ካረን ምን ማለት እንደሆነ የእንግሊዝኛው ትርጉሙን እንደሚከተለው ባቀርበው ሳይሻል አይቀርም፡፡

Karen is a pejorative term for a woman  seeming to be entitled or demanding beyond the scope of what is normal .the term also refers to memes depicting white women who use their privilege to demand their own way

ከተለመደው የዲፕሎማቲክ አካሄድ ወጣ በማለት ሚስስ ሳማንታ ፓወር በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተቆጥተው ለኢትዮጵያ መንግስት ባስተላለፉት መልእክት ገለልተኛ አቋም እንደሌላቸው ለኢትዮጵያ እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡ አንዱ እና ዋነኛው መልእክታቸው በሰብዓዊ እርዳታ ስም ወደ ሱዳን የሚወስድ ኮሪደር እንዲከፈት የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ መሬት ላይ ካለው እውነት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በርካታ የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኞቸ እንደሚስማሙበት ከሆነ የኮሪደሩ መከፈት የተከሰተውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስበው ይሆናል፡፡ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ለማድረስ በርካታ አማራጮች እንዳሉ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

በነገራችን ላይ በድንበር ይገባኛል እና በአባይ  ወንዝ  እሰጥ እገባ (Nile dispute )ጉዳይ ላይ የራሷ የፖለቲካ ጨዋታ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሳምሪ በመባል የሚጠሩት ተዋጊ ሚሊሻዎች በሱዳን ምድር ወታራዊ ስልጣና ይሰጣቸዋል ይባላል፡፡ ( ሳምሪ የተሰኙት ኢመደበኛ የወጣቶች ቡድን በማይካድራ ከተማ ይኖሩ በነበሩ የአማራ ተወላጆች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፈጸሙ በኋላ ወደ ሱዳን የሸሹ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ከዚህ ባሻግር በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ቀውስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር በሃይል መያዛቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ወ/ሮ ሳማንታ ፓወር በሱዳን የሶስት ቀን የስራ ቆይታቸው ከሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር ባደረጉት ንግግር ወይም ውይይት ሱዳን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ሽምግልና እንድትቀመጥ ወይም የሰላም አደራዳሪ እንድትሆን ከመጠየቃቸው ባሻግር በሱዳን ስደተኛ ካምፕ ውስጥ ተደባልቀው የሚኖሩ የትግራይ ኢትዮጵያዊ ተወላጆችን እና የህውሃት ታጣቂዎችን ጎብኝተዋል፡፡ 

አሁንም ቢሆን ሳማንታ በስብዓዊ እርዳታ ስም በኢትዮጵያ ምድር ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እውን እንዲሆን ጫና ማሳደር ፍላጎታቸው ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አስከፊ ችግር (ሰብዓዊ ቀውስ)   በኢትዮጵያ እንዳይከሰት  ለመከላከል ነው የሚል ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይሀውም የሚከተለው ጥያቄ ነው፡፡ ለምንድን አንድ የአለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት ሃላፊ የሆኑ ሴት ታማኝነት በጎደለው የፖለቲካ ፍላጎት የተነሳ ነጻ የመተላለፊያ ኮሪደር እንዲከፈት የፈለጉት ? ይህ የሴትየዋ ፍላጎት በአለም አቀፍ ባህልና ኖርም ሳይቀር ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አቀራረብ የተባበረችው አሜሪካን አለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድን (USAID ) ተቀባይነት ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡

በነገራችን ላይ አንዳንድ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው የኢትዮ-አሜሪካን ዜጎች ኢትዮጵያ በዚህ አስጨናቂ ግዜ ውስጥ በተዶለችበት አጋጣሚ ሳማንታ የራሷን አጀንዳ በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን እየገሰገሰች እንደሆነ ይሰማቻዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ወ/ሮ ሳማንታ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደጠቀሱት ኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ የአሸባሪውን የወያኔን ቡድን ካንሰር እና አረም ብለው መሰየማቸው እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ ሳማንታ አስተያየት ከሆነ ይህ የጥላቻ ንግግር ነው፡፡ ግጭትንም ያባብሳል ባይ ናቸው፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት እንደተናገሩት ከሆነ የወያኔን ቡድን አሸበሪ ብድን ነው ብሎ መሰየም እነርሱን ከሰውነት ደረጃ ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ የብቀላ ሰበዝም ሊመዘዝባቸውም ይቻለዋል ሲሉ ተሟግተውላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የተባበረችው አሜሪካ የጎን ውጋት የነበረውን አልቃኢዳን በተመለከተ መንግስታቸው አሸባሪ ከማለታቸው ባሻግር የአለም ካንሰር ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ለአብነት ያህል በአዲሲቷ አሜሪካ ማእከል በግዜው የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር የነበሩት ሊኦን ፓኔታ  (the then-Defense Secretary Leon Panetta ) እንደ ጎርጎሲያኑ አቆጣጠር 2012 ላይ አልቃይዳን በተመለከተ ለዜና ሰዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት አልቃይዳ ለተባበረችው አሜሪካ እና ለቀሪው አለም ሰይጣን እና ካንሰር ነው ሲሉ ነበር የሰየሙት፡፡ ምናልባት አብዛኞቹ የአሜሪካ መንግስት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የፋሺስት ጣሊያን የመንፈስ ልጅ የሆነው ፋሺስቱ የወያኔ ቡድን በብዙ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነተመለከተ የሚደማ ልብ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ገን ይሁንና ወያኔ የፈጸመው ግፍ የአሜሪካ መንፈስ እና አንዳንድ ለእውነት የቆሙ እና የሞራል ልእልና ያለቸው አሜሪካዊ የፖለቲካ አዋቂዎችን እና የመብት ተሟጋቾችን ልብ ያርዳል፡፡ ህሊናንም ያደማል፡፡ ወያኔ አሸባሪ ተብሎ ቢሰየም የሚቃወሙ አይደለም፡፡ ለማናቸውም አሜሪካ አልቃይዳን አሸባሪ በማለት ለመሰየም እንደበቃችው ሁሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ግፍ የፈጸሙትን ወያኔዎች አሸባሪ ብሎ መሰየም አግባብነት ያለው ነው፡፡

ከገሃዱ አለም ውጭ ያለው ወታደራዊ ሃሳብ (Militaristic idealism )

በሚስስ ሳማንታ ፓወር የአይምሮ ጓዳ ውስጥ የተጻፈው የግል እውቀት ወይም የህይወት ልምድ በሚከተለው አስተምህሮ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይኀውም ‹‹ የሃሳባውያን ትምህርት ›› (“The Education of an Idealist.”) ይሰኛል፡፡ እርሳቸው ለብዙ ግዜያት ሀሳባዊ በመሆናቸው ከገሃዱ አለም ጋር ሲጋጩ ይስተዋላሉ፡፡ የአለምን ሰላም ለማረጋጋት ሃሳባዊ መሆን ወይም እውነታ ላይ መቆም ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ተገቢውን መልስ መፈለግ ያሻል፡፡ የሳማንታ ችግር ይሄው ይመስለኛል፡፡ ሳማንታ ለዚች ሰላሟን ላጣች አለም፣ለተሰበረች አለም መፍትሄው የምእራባውያን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ነው የሚል ሃሳብ አላቸው ሃሳባቸው ግን ብዙ ግዜ ፈሩን የሳተ ወይም መሬት ላይ ካለው ተጨባጩ እውነታ ጋር የሚገጥም አልነበረም፡፡በሌላ አነጋገር በብዙ የአለም ክፍሎች የተቀጣጠሉ ግጭቶችን ለመቆጣጠር በሚል የምእራባውያን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ቢኖርም ውጤቱ አጥጋቢ እንዳልሆነ በገቢርም በነቢብም የታየ ነው፡፡ ( ምንአልባት አንዳንድ የአለም ክፍሎች ውስጥ ሰላም በማስፈን፣የሰብዓዊ እርዳታ ከማቅረብ አኳያ ተሳክቶላቸው ሊሆን ይችላል፡፡)

በሃሳባዊው አለም የራሶትን ሃሳብ እውነት አድርገው ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ የወይዘሮ ሳማንታ ሃሳብ ከቻሉ በብእር፣ በፕሮፓጋንዳ አንድን የሚጠሉትን ሀገር መሪ በሌላ መቀየር ይቻላል የሚል ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ በሰብዓዊ እርዳታ ስም ወይም በጦር ሀይል ጡንቻ በመጠቀም የአንድን ሀገር መሪ መቀየር ይቻላል ብለው ያስባሉ፡፡

ምንም እንኳን ለማስመሰል ያህል ተቆጣጥረናቸዋል ቢባልም ወይም እየቀነሱ ነው ቢባልም ጦርነት፣ውድመት፣የብዙሃን ሰቆቃ፣ርሃብ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ማናቸውም ሰው ሰራሽ ስቃይ፣ ረቂቅ ዘረኝነት ወዘተ ወዘተ የሰው ልጅ ታሪክ አንዱ አካል ናቸው፡፡ አሁን ለጠቀስኳቸው ችግሮች መፍትሔው እጅግ የተወሳሰበ ነው፡፡ ሰራሄ መፍትሔ ለመሻት እውነታውን መረዳት እጅጉን ጠቃሚ ይሆናል፡፡ እውነትን መጋፈጥ አስፈላጊ ነው፡፡ የቢሆን ግምቶች ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡ ሃሳባውያን በመሬት ላይ ያለውን ነባራዊ እውነት መጋፈጥ ይከብዳቸዋል፡፡ አንድ ነገር ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በሀገራት ላይ የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ብለው የሚያምኑ ( እንደ ወ/ሮ  ሳማንታን የመሰሉ ሃሳባውያን ማለቴ ነው ) ውጤት እንዳላስገኙ በኢራቅ፣ሊቢያ፣አፍጋኒስታን፣ሶሪያ፣ ሀይቲ እና ቬትናም ላይ ታይተዋል፡፡ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ክስረትን እንጂ ውጤትን እንዳላሳየ በአለም የፖለቲካ ታሪክ ላይ ፍንትው ብሎ የተቀመጠ እውነት ነው፡፡

በነገራችን ላይ የተባበረችው አሜሪካ የውጭ ተራድኦ ድርጅት( USAID) አስተዳዳሪ ኢትዮጵያን ከመጎብኘታቸው በፊት አንዳንድ የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች የባለስልጣኗን አመለካከት አጉልተው ያሰሙ ነበር፡፡ርእስ አንቀጹ ድምጸት ነበረው፡፡ ይህ በምእራቡ አለም የተለመደ ስትራቴጂ ሲሆን የሶስተኛውን አለም አንዳንድ አገሮች ወደ ራሳቸው አጀንዳ ውስጥ ለመዶል ይረዳቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የምእራቡ አለም ፖለቲከኞች እና ውሳኔ ሰጪዎች መገናና ብዙሃንን በመጠቀም አለማቸውን እንዲስፈጽሙላቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እነርሱ ምንግዜም ቢሆን ከአለማቸው ተጻራሪ የሆኑ አገሮችን ፍርሃት እና ጭንቀት ውስጥ መዶላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሚስስ ሳማንታ ፓወር የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ያደረጉ አሜሪካዊ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አኚህ ባለስልጣን ዘረኛውን እና አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የሚታወቀውን አሸባሪውን የወያኔ ቡድን በተመለከተ አያውቁትም ወይም ለማወቅ አልፈለጉም፡፡ (  ወያኔ ባለፉት 27 አመታት ሰለፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ስላስከተለው የተወሳሰበ ችግር በተመለከተ ማለቴ ነው፡፡) ባለፉት 27 የሊቀ ሴጣን ወያኔ አገዛዝ ዘመን ስለተፈጸሙት፡-

  • ጅምላ ግድያ
  • ጥልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰት
  • ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ግድያ
  • አሰገድዶ መድፈር ወንጀል
  • በቀን ብርሃን እና ጨለማን ተገን በማድረግ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እስር፣ ህዝቡን ሲያሸብሩ ወዘተ ወዘተ በአፓርታይድ አገዛዙ ሲፈጸም የሰብዓዊ ስሜት አለን የሚሉት እነ ሳማንታ ፓወር የት ነበሩ ? የትም አልነበሩም፡፡ የትም ቦታ ድምጻው አልተሰማም፡፡
  • እውን ሳማንታ ፓወር የወያኔ አገዛዝ የአፍሪካ ችግር እንደሆነ የሚገልጽ ምስክርነት በተባበረችው አሜሪካ መዝገበ ቃላት ውስጥ ስለመገኘቱ መናገር ይችሉ ይሆን ? አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በጥናቶቻቸው ላይ ፍንትው አድርገው እንዳስቀመጡት ከሆነ የወያኔ አገዛዝ የምኒሊክ ቤተመንግስት ዘው ብሎ ከመግባቱ በፊት እና የማእከላዊ መንግስት ስልጣኑን ከመቆጣጠሩ 1991 ( እ.ኤ.አ.)  እረጅም አመታት በፊት( የገንጣይ አስገንጣይ ተልእኳቸውን በሚወጡበት አመታት ማለቴ ነው) በተባበረችው አሜሪካ መዝገበ ቃላት ውስጥ በአሸባሪነት ስሙ የተመዘገበ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  ምንግዜም ቢሆን የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ የምታስቀድመው አሜሪካ ዞር ብላ ዛሬ የወያኔ ደጋፊ ሆናለች፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት ይህ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያ አዛዥ ናዛዥ በነበረበት ዘመን እነ ሱዛን ራይስ (Susan Rice) እና ጋይሌ ስሚዝን (Gayle Smith) የመሰሉ ወዳጆችን አፍርቷል፡፡ የክሊንተን አስተዳደር በበኩሉ አለም አቀፍ አሸባሪዎችን ለመዋጋት በሚል መንፈስ እንደ ወያኔ የመሰሉ የግፈኛ ስብስብ ድርጅቶችን በአጋርነት አቅፎ አንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ 
  • the trust of powerful friends like Susan Rice and Gayle Smith, among others, in the Clinton administration and managed to become Washington’s pampered adoptee through a “partnership in the global war on the war on terror.” 

ከአይርላንድ ወደ ስልጣን   

ሳማንታ ወደ ተባበረችው አሜሪካ የመጡት የአየርላንድ ተወላጅ እና በሙያቸው የህክምና ዶክተር ከሆኑት እናታቸው ጋር እንደነበር በህይወት ታሪካቸው ዙሪያ ከተጻፉ ሰነዶች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ዛሬ ሳማንታ ፓወር አጅግ ተጽእኖ ፈጣሪ እና አለምን በራሳቸው ምስል ለመቅረጽ ወደኋላ የማይሉ ታላቅ ሴት ለመሆን በቅተዋል፡፡

ሴትዮዋ የቀድሞው የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት የሚተማመኑባቸው ፣ እንዲሁም በብይነ መንግስታቱ ማህበር እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2013-2017 ድረስ የአሜሪካ ፕሬዜዴንት የነበሩ፣ በፕሬዜዴንት ጆባይደን ዘመን የህግ አውጭው ሁነኛ ሰው፣ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የአሜሪካው የውጭ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ተራ ድርጅት አይደለም፡፡ ሚስስ ሳማንታ የድርጅቱ መሪ እንደመሆናቸው መጠን በብሄራዊው ጸጥታ ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ (As the head of USAID, she sits on the National Security Council ) ( የጸጥታው ምክር ቤት በፕሬዜዴንቱ አመሃኝነት የአሜሪካንን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚወስን ሁነኛ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዜዴንትም ቀኝ ህግ ነው፡፡)

እንደ የአሜሪካ ፖለቲካ ተንታኞች የጥናት ውጤት ከሆነ አመታዊው የአሜሪካ የውጭ ተራድኦ አመታዊ ባጀት 40 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመሆኑ የተነሳ የሳማንታን ሃሳባዊ የሰብዓዊ አላማ ለማራመድ ጠንካራ ክንድ ሊሆናቸው በቅቷል፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ኢትዮጵ ባሉ ድህነት ቤቱን በሰራባቸው ሀገራት የአሜሪካ የውጭ ተራድኦ የሰብዓዊ እርዳታ እንደው ዝም ብሎ አይሰጥም፡፡ ከጀርባው ብዙ ግዴታዎችን ተሸክሞ የሚመጣ ነው፡፡ ምንም እንኳን የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ገዳይና አስከፊ ቢሆንም ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ እርዳታ አይገኝም፡፡

ሚስስ ሳማንታ የዝነኛው ሀርቫርድ ዩንቨርስቲ ምሁር ከመሆናቸው በፊት ጋዜጠኛ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ኦባማ እንዲመረጡ ከፊት መስመር ሆነው ሲቀሰቅሱ የነበረ ሲሆን፣ በባልካን ባህር አካባቢ የነበረውን የርስበርስ ጦርነት ላይ ደግሞ ነዳጅ በማርከፍከፍ ይታወቃሉ፡፡ ( የባልካን ባህር አካባቢ ዩጎዝላቪያና ቼኮዝላቫኪያ የሚገኙባቸው ሀገራት መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ሳማንታ የፎሪያን ፖሊሲ መጽሔት የስራ ባልደረባ መሆናቸውን የሚያሳይ መታወቂያ በማሰራት በባልካን ሀገራት የጦርነት ዘጋቢ ጋዜጠኛ መስለው እኩይ ተልእኳቸውን ይወጡ እንደነበር የሚያሳይ ጽሁፍ ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ከአዘጋጀው ጽሁፍ እንዳነበበኩ አስታውሳለሁ፡፡

ከገሃነም የመነጨው የአፍሪካ ችግር

እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር 2002 ‹‹A Problem from Hell>>  በተሰኘው መጽፋቸው ላይ ዘግናኙን የሩዋንዳ የዘር ፍጅት በተመለከተ በስፋት ሄደውበታል፡፡ ከዚህ ባሻግር የተባበረችው አሜሪካ እና አጋሮቿ የምእራቡ አለም ሀገራት መንግስታት የሩዋንዳ አስከፊ የዘር ፍጅት ከመከሰቱ በፊት መከላከል ባለመቻላቸው ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ነበር በመጽሐፋቸው ላይ የጠቀሱት፡፡ ምንም እንኳን በዘር ፍጅት ላይ ጥልቅ ጥናት ያደረጉና የተመራመሩ ምሁር ቢሆኑም በኢትዮጵያ ስላለው አስከፊ ውድቀት በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ነው፡፡ ሴትየዋ በሰብዓዊ እርዳታ ስም የራሳቸውን አጀንዳ ገቢራዊ ለማድረግ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ይህንኑ እኩይ ምግባራቸውን የተረዱትና የሚተቿቸው የምርመራ ጋዜጠኛዋ አና ጋሪሰን( investigative journalist Ann Garrison) ናቸው፡፡ ጋዜጠኛ አና ጋሪሰን ሳማንታ ፓወር ‹‹ አፍሪካን ወደ ገሃነም ›› የሚወስዱ ናቸው ሲሉ ነበር የተቿቸው፡፡ (calls her “Africa’s problem from hell.” )

ጋዜጠኛ ጋሪሰን በአንድ ጽሁፍ ላይ እንደጠቀሰችው‹‹ እርሷ ሳማንታን ማለቷ ነው በአንድ አካባቢ አስከፊ የዘር ፍጅት እየተፈጸመ ነው በማለት ለአሜሪካ መንግስት ማሳሰቢያ ከሰጡ የአሜሪካ መንግስት የዘር ፍጅት ተፈጽሟል ተብሎ በሳማንታ በተገለጸው ስፍራ ልዩ ወታደሮቹን ይልካል ሲሉ ነበር የሴትየዋን ሃያልነት የገለጹት፡፡ ሳማንታ ያሉት ነገር በነጩ ቤተመንግስት ተሰሚነት አለው፡፡

የተባበረችው አሜሪካ የውጭ ተራድኦ ድርጅት አስተዳዳሪ እነደመሆናቸው መጠን የውጭ እርዳታ ላይ ተጽኗቸው ከባድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አሜሪካ መራሹ የናቶ ጦር (US-led NATO bombings in Libya and Syria) በሊቢያና ሶሪያ ምድር ላይ በጦር አይሮፕላን እንዲደበድብ ዋነኛዋ ቀስቃሽ ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ ውጤቱ ሰላም አላስገኘም፡፡ የናቶ የጦር አይሮፕላን ቦምብ ዝናብ በተጠቀሱት ሀገራት ግጭቶችን ነበር እንደ ነዳጅ ያቀጣጠለው፡፡

ሳማንታ ፓወር የሚያቀነቅኑት የሰብዓዊነት ስሜት አለማችንን ወደ ተሻለ ቦታ እንደሚያስቀምጣት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሚያከራክረው አስተሳሰባቸው ነው፡፡ የሰብኣዊ እርዳታ በአንድ ሀገር ላይ ለማድረስ እስከ ወታደራዊ ስምሪት የሚደርስው የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት አከራካሪ ነው፡፡ ሁልግዜ ‹‹ እሳትን፣ በእሳት የማጥፋት ሰትራቴጂ ላይሰራ ይችላል፡፡. (Putting out fire with fire is always a dubious strategy.) የአሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በብዙ ሀገራት ክሽፈትን አስከትሏ፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1992 የቢል ክሊንተን አስተዳደር የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ በሚል ምክንያት ‹‹ Operation Restore Hope ›› የተሰኘ ዘመቻ በሶማሊያ ምድር ላይ ቢከፍትም ውድቀትን ነበር ያስከተለው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሶማሊያን አንድነት ነው ያናጋው፣ ሶማሊያውያን ዜጎች በአለም ላይ እንደ ጨው ዘር አንዲበተኑ ነው ያደረጋቸው፡፡ ምናልባት በሶማሊያ ምድር የአሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እና ውጊያ ጠቃሚነቱ ለሆሊዉድ ፊልም ሰሪዎች ( አምራቾች) ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሽብርተኝነት የእኛን ፍላጎት እስካሟላ ድረስ አለማውገዙ ያዋጣ ይሆን ?

ኢትዮጵያውን በተለይም ኢትዮጵያዊ-አሜሪካውያን በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ፣አፋርና አማራ ክልሎች ስለተከሰተው የሰብዓዊ ቀውስ በተመለከተ፣ የአሸባሪው ወያኔ ቡድን ስለጫረው የጦርነት እሳትና ወረራ በተመለከተ አንቶኒ ብሊንከን እና ሳማንታ ፓወር በያዙት ገለልተኛ ያልሆነ አቋም የተነሳ ቅሬታቸውን በአገኙት አጋጣሚ ሲተቹ ማየት የተለመደ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተፈናቃይ ዜጎች በፍጥነተ ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ምንም ክርክር አይፈጥርም፡፡የሞራልም ግዴታ ነው፡፡ እነ ሳማንታ እና ብሊንከን ለእኩይ አላማቸው ሲሉ በሰብዓዊ እርዳታ ስም በሱዳን በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሚወስድ መንገድ መከፈት አለበት የሚሉት ቅድመ ግዴታ የራሳቸውን ድብቅ አላማ እና ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ነው፡፡ ሳማንታ በአካባቢው የተከሰተውን ግጭት ለማወሳሰብ ይፈልጋሉ፡፡ በታላቁ የአባይ ግድብ ግንባታ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር አይንና ናጫ የሆኑት፣ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረሙት ሱዳንና ግብጽ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ለማድማት መንገድ የሚከፍት ነው፡፡ የሳማንታ እቅድ፡፡ ይህም ማለት በወያኔ የአሸባሪነት ባህሪ ምክንያት ጦርነቱ ሰፊ አካባቢ፣ብዙ ሀገራት  ሚካፈሉበት ሊሆን ይቻለዋል፡፡

የግዜ ጉዳይ እንጂ የጦር ወንጀለኞች የትም ይደቁ፣የትም ይሸሸጉ መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ በሰሜናዊት ኢትዮጵ ትግራይ ለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂዎቹ አካላት ብዙ ናቸው፡፡    በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተደቁሶ ከመቀሌ ከተማ  የተባረረው ወደ ተራራዎች እና ዋሻዎች ውሰጥ የተደበቀው የወያኔ አሸባሪ ቡድን  ከእስር ማጎሪያዎች የለቀቃቸው በ10ሺህዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችም ቢሆኑ ተጠያቂ ናቸው፡፡

ፍርድ ከመስጠት በፊት ፍጹም ገለልተኛ የሆነ ምርመራ ግድ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ  በውሸት ፣የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተሰላችቷል፡፡ እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር ህዳር 4 2021 የወያኔ የሽብር ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከከፈተ ጀምሮ እውነተኛ ዜና ይፈልጋል፡፡ ከአንድ ወገን ብቻ የሚሰሙ ዜናዎች ህዝብን ያደናግራሉ፡፡ የአሳዛኙ ጥቃት ዋነኛ አላማ የሰሜን እዝን ትጥቅ መማረክ እና የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ ያለመ እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡

ምንም አይነት ምክንያት ይሰጠው በሰሜን እዝ ላይ ለተፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት በዋነኝነት ተጠያቂው የወያኔ አሸባሪ ቡድን ነው፡፡ በርግጥ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በኢትዮጵያ ምድር ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ በመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂ ናቸው፣ ሌሎችም አንዳንድ የመንግስት አካላት ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ ወረራውን የጀመሩት ወያኔዎች በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ ምድር ለተፈጠረው ምስቅልቅል ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡

የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች መብረቃዊ ጥቃት በሚል የሰየሙት  አላማ የነበረው የሰሜን እዝን ትጥቅ ማስፈታት ከተቻለን ወደ መሃል ሀገር በቀላሉ እንገሰግሳለን በሚል እሳቤ ነበር፡፡ ዋነኛ አላማቸው የ27 አመታቱን አስከፊ አገዛዝ መልሶ ለማንበር ያለመ ነበር፡፡

በአንድ የአሜሪካ ግዛት እንዲህ አይነት የጦር ወንጀል ቢፈጸም ምን ይፈጠራል ? በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ቢገደሉ ምን ይከተላል ? የተባበረችው አሜሪካን አቋም ምን ይሆን ነበር ? በተባበረችው አሜሪካ ወታደራዊ ሀይል ድንገተኛ ጥቃት ቢደርስበት የአሜሪካ እርምጃ ምን ይሆን ነበር  ? እውን የአሜሪካው ፕሬዘዴንት ባይደን ለጥቃት አድራሾቹ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት በመላክ ቁጭ ብልን እንደራደር ይሏቸው ይሆን ? ነገሩ ቀላል አይደለም ፡፡ ለማናቸውም እስቲ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 4 2020 በኢትዮጵያ የተፈጠረውንና ጥር 6 ቀን 2021 የተባበረችውን አሜሪካ የካፒቶል ማእከልን ሰብረው የገቡት  በመላዋ የተባበረችው አሜሪካ  ያሳደረውን ከባድ ስጋት አወዳድሩት ያንዬ ታላቋ  አሜሪካ ያላዘመተችው የጦር ሀይል አልነበረም፡፡ በሰው ሀገር ለሚፈጠር ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ ብቻ ሲሉ ለምንድን ነው የህሊና ሚዛናቸው የተሰበረው? ለማናቸውም መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡

የተባበረችው አሜሪካ የኢትዮጵያ ወዳጅ እንደነበረች በሰፊው የሚታመን ጉዳይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ኢትዮጵ በጥልቅ ውድቀት በተዘፈቀችበት በዚህ ክፉ ግዜ ብዙ ኢትዮጵውያን በተባበረችው አሜሪካ እንደተከዱ ይሰማቸዋል፡፡ የባይደን አስተዳደር የአማራ ሃይሎች ምእራብ ትግራይን ለቀው መውጣት አለባቸው የሚለው ትእዛዝ መሰል ጥሪ ሚዛናዊ ወይም ምክንያታዊ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ከአርባ አመታት በፊት ሰሜን ኢትዮጵያ የጥንቱን የቤጌምድር ግዛት አካል የነበረውን የወልቃይት ምድር በሃይል በጉልበት የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ወስዶታል፡፡ ወይም የትህራይ ክልል እንዳደረገው ምእራባውያን ሊረዱት ይገባል፡፡ ወያኔ ባለፉት 40 አመታት በወልቃይት አዛውንቶች፣ወንድሞችና እህቶች ላይ ግፍ ፈጽሟል፡፡ የጎሳ ማጽዳት ወንጀልም ፈጽማል፡፡አንድ ቀን የዚህ ግፍ ፈጻሚዎች በፍትህ አደባባይ እንደሚቆሙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ወልቃይት ጸገዴ የሰው ልጆች መኖሪያ መሆን አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ በዚህ ለም መሬት ኢትዮጵያውያን በፍቅርና አንድነት እንዲኖሩ ምኞቴ ነው፡፡ በተባበረችው አሜሪካ ለላስቬጋዝም ሆነ አላባማ፣ለካሊፎኒያም ሆነ አላስካ፣ ለዋሽንግተንም ሆነ ቨርጂኒያ የየራሳቸው አስተዳዳሪ እንዳላቸው ሁሉ ወልቃይት ጸገዴም የራሱ አስተዳዳሪ ያስፈልገዋል፡፡ የወልቃይት የአስተዳዳር ክልል ደግሞ በጎንደር ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ ምድር የጎንደርም ሆነ የትግራይ ወንድሞቻችን በሰላም ሰርተው መኖር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምእራቡ አለምም ሆነ የተባበረችው አሜሪካ ለራሳችው ብሔራዊ ጥቅም መከበር ሲሉ እንዲህ አድርጉ፣ እንዲህ አታድርጉ ማለታቸው ከትዝብት በቀር የሚያመጣው ፋይዳ የለም፡፡ ምእራባውያን ይህ ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ እንደሆነ ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡ ይህ የተከፈተ ቁስል የኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳይ ነው፡፡

For almost three decades, they committed ethnic cleansing and mass atrocities against Amhara habitants of Welkait and Humera. This is a sensitive issue, an open wound that must be left for Ethiopians to address internally. 

በሌላ ሀገር ጦርነት እንዲፈጠር የሚሰብኩ ሃሳባውያን

እነ ሳማታ ፓወር አንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት፣የአሸባሪውን ወያኔ ቡድን አይነት ከጀርባ መደገፍ እና ማበረታታት፣ ሃይል እንዲያገኝ ሁኔታዎች ማመቻቸት ሰላም እንዳይፈጠር መረጋጋት እንዳይኖር ይረዳል የሚል ሃሳብ ካነገቡ አመታት ተቆጠሩ፡፡

በቅርብ ግዜ ውስጥ For almost three decades, they committed ethnic cleansing and mass atrocities against Amhara habitants of Welkait and Humera. This is a sensitive issue, an open wound that must be left for Ethiopians to address internally. 

በቅርብ ግዜ ውስጥ ጋሪሰን ውስጥ የአለም አቀፍ ህግ ፕሮፌሰር የሆኑት ቦይል (Boyle) በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ሳማንታ ፓወር በአንድ ሀገር ጦርነት የሚገኙ የጦር አውርድ ቡድኖችን የመደገፍ ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ሳማንታ በሊቢያ እና ሶሪያ ለተከሰተው እልቂት ማነው ተጠያቂው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ አደገኛ ነው ካሉ በኋላ በሰብዓዊነት ስም በኢትዮጵያ ምድር የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ መሞከር ውጤቱ አደገኛ ነው ሲሉ ነበር ስጋታቸውን የገለጹት፡፡

እነ ሳማንታ ፓወር የሚያራምዱት በሰብዓዊ እርዳታ ስም የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በእሳት ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ የሚቆጠር ነው፡፡ ታሪክ የተባበረችው አሜሪካ በሊቢያ፣ሶሪያ፣ሶማሊያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ወይም ቬትናም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ክሽፈትን እንጂ ውጤትን እንዳልተጎናጸፈች ፍንትው አድርጎ አስተምሮናል፡፡ የጨነገፉ ሀገራት የሃያላን ጣልቃ ገብነት ክብደት መሸከም አይችሉም፡፡

ከታሪክ ለመማር ምርጡ መንገድ ካለፈው ስህተት በመማር ‹ያንኑ ታሪክ ላለመድገም መመለከሩ ነው፡፡ የተባበረችው አሜሪካ የራሷ ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ስትል ( የሌላውን ሀገር ጥቅም አፈር ድሜ በማስጋጥ) ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር ያደረገችው ሽርክና ወይም በመሻረክ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማድረጓ ሀገራቱን ተመልሰው እንዳይነሱ አድርገው ነው የአሜሪካን ወታደሮች ጥለው የወጡት፡፡ አሜሪካን ከ20 አመታት የአፍጋኒስታ ቆይታቸው በኋላ ያቺን ሀገር ጥለው የወጡት ለጽንፈኛ እስልምና እምነት አራማጆቹ ታሊባኖች ነው፡፡ ታሊባኖች ከ20 አመታት በፊት አፍጋስታንን ለአምስት አመታት ሲገዙ የነበረበት አስከፊ አገዛዛቸው የተቀየረ ቢመስልም የተቀየረው እውነተኛ ማንነታቸው ወደፊት በግዜ ሂደት የሚታይ ነው፡፡ ስለሆነም የእነ ሳማንታ ፓወር የተባበረችው አሜሪካ አሸባሪውን የወያኔ ቡድን እሽሩሩ ማለት ለኢትዮጵያ ጥፋትን እንጂ እድገትን እንደማያመጣ ተገንዘበው ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ ቸእንማጸናለን፡፡ በእኔ የግል አስተያየት ከ100 አመታት በላይ የቆየ ዲፕሎማቲክ ወደጃነት ያላቸው ኢትዮጵያና የተባበረችው አሜሪካ ወያኔ ለሚባል አደገኛ ዘረኛ እና አሸባሪ ቡድን ሲባል መበላሸት ለበት አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታም ዝግጁ ነኝ፡፡

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን ያስከበረችው እንደው በዋዛ በፈዛዛ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውንና ሉአላዊነታቸውን ለማስከበር ከባድ መስእዋትነት ከፍለዋል፡፡ እልፍ አእላፍ ቅድመ አያቶቻችን፣አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰዋል ደማቸውን አፍሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለየት ያለ ታሪክ እና ዋጋ ያለው ስርዓት ያላት ሀገር ናት፡፡ ስለሆነም የተባበረችው አሜሪካ ይችን ቁልፍ ሀገር ለየት ባለ ሁኔታ መመልከት አለባት፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካው ቀንድ መረጋጋት ሁነኛ ሚና ያላት ሀገር በመሆኗ የተነሳ አሜሪካ ኢትዮጵያን በእኩልነት፣በፍትህና ባለማዳላት አጋሯ ትሆን ዘንድ ይመከራል፡፡

በመጨረሻም ማስታወስ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ‹‹ ሰላም የሚመጣው እብደት ሲቆም ነው፡፡ ›› ብዬ አስባለሁ፡፡ ከመሃልም ከሰሜን ኢትዮጵያ የፖለቲካ እብደት መቆም አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ በደቦ ፍርድ፣ በብሔራዊ እብደት ፣በስሜት ፖለቲካ ኢትዮጵያን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር አያወጣትም፡፡ የሮማው የታሪክ ጠበብት የነበረው ታኪተስ እንደጻፈው ‹‹ መጥፎ ሰላም ከጦርነት የበለጠ የከፋ ነው›› ሰላም የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋ መሆን የለበትም፡፡ ለሰላም ሲባል የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት መናጋት የለበትም፡፡ የአሸባሪውን ወያኔ ህልውና ለማቆየት የታለመ ሰላም ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት አይመስለኝም፡፡ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በጦር ወንጀለኝነት መጠየቅ አለባቸው፡፡

as the Roman historian Tacitus is quoted as saying: “A bad peace is even worse than war.”

የዛሪዬቱ የአሜሪካ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በተለይም እንደ ሳማንታ ያሉቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተባበረችው አሜሪካ አምባሳደር ሮበርት ፒ.ሰኪነር እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር ታህሳስ 1903 አዲስ አበባ አንደደረሱ ያደረጉትን ታካዊ ንግግር ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እጠቅሳለሁ፡፡

‹‹ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ሌሎች ሀገራት በአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዞች ፍዳቸውን በሚቆጥሩበት ግዜ ኢትዮጵያ ነጻነቷናን ሉአላዊነቷን ያስከበረች ሀገር ናት፡፡››

When the first U.S. American Ambassador to Ethiopia, Rober P. Skinner arrived in Addis Ababa in December 1903, he admiringly recognized Ethiopia’s greatness, pride, independence, and sovereignty at a time when most of the world was suffering under the tyranny of European colonialism

ሀላፊነት የሚሰማቸው አለም አቀፍ መሪዎች

የአሸባሪው ህውሃት ቡድን ወረራ በመፈጸሙ ምክንያት ለሽብርና ለጦርነት እና ለሽብር የተጋለጠችውን ኢትዮጵያ ዝም ብሎ መተው ለረጅም ዘመናት በቆየው የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ታካዊ ግንኙነት ላይ የማይሻር ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊ ወታደሮች ከአሜሪካ ወታደሮች ጋር አጋር በመሆን በሶማሊያ ምድር ከአልሻባብ ጋር ሲፋለሙ መውደቃቸውን አሜሪካውያ ማስታወስ ይገባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮ-አሜሪካውያን የተባበረችው አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በወታደራ ጣልቃ ገብነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የሀገርን ሉአላዊነት ባከበረ መልኩ ነው በማለት የሚከራከሩት፡፡ 

በነገራችን ላይ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዜዴንት ትራምፕ ዘመነ መንግስት የጠፋው የተባበረችው አሜሪካን አለምን የመምራት ሚና በባይደን አስተዳደር አየተመለሰ መሆኑ መልካም ዜና ነው፡፡ ስለሆነም አሜሪካ ለአለም  ሰላም መስፈን ታላቅ ሃላፊነት አለባት፡፡

በአጼ ሐይለስላሴ ቃል የዛሬውን ጽሁፌን ልቋጭ  ‹‹ አመራር ማለት ተጽእኖ ማድረግ አይደለም›› ነበር ያሉት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ (“Leadership does not mean domination) በነገራችን ላይ አለም ሁል ግዜ ተጽእኖ በሚያደርጉ ግለሰቦች እና በሚመሩ ሰዎች የተሞላች ናት፡፡ አውነተኛ መሪ ከዚህ በተቃራኒው የቆመ ይመስለኛል፡፡ እውነተኛ መሪ ሌሎች እንደጠቀሙ ፣ህይወታቸው እንዲሻሻል የሚተጋ ነው፡፡ሌሎች የእርሱን ቀና መንገድ እንዲከተሉ፣የእርሱን ጥበብ እንዲለኩሱ፣ ያስተምራል፡፡ ህብረተሰቡ በእውነተኛ መንገድ እንዲጓዝ ያደርጋል፡፡ እውነተኛ መሪ ለግሉ ምኞትና ህልም የሚሰራ ሳይሆን፣ ለምልአተ ህዝቡ አጠቃላይ እድገትም የሚሰራ ነው፡፡

Filed in: Amharic