የምእራባውያኑ ሴራ – ኢትዮጵያን ዘላቂ ወዳጅ ማሳጣት …!?!
ደረሰ አማረ
በመካከለኛው ምስራቅ እና በአፍሪካ ቀንድ የተከሰቱ የእርስ በርስ ጦርነቶች ሁሉ ፈጣሪና አድራጊዋ አሜሪካ ስለመሆኗ በግጭቶቹ ዙሪያ ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ለአብነትም፥ ለኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ መለየት፣እንደ ህወሓት እና ሸኔ ላሉ የሽብር ቡድኖች አቅም መዳበር፤ ለሶማሊያ አገረ መንግሥት መዳከም፤ ያን ተከትሎ በሃገሪቱ እንደ አልሸባብ ያሉ ጽንፈኛ የሽብር ቡድኖች መፈጠርና የአካባቢውን ሰላም ማወክ፤ ከሱዳን ለሁለት መከፈል ጋር ተያይዞ የሁለቱ ሱዳኖች ሰላም መናጋት ወዘተ ይጠቀሳሉ።
በቀይ ባህር ቀጣና ላይ አሜሪካ የምታንፀባርቀው አቋም ለጥቅማችን ስጋት እንደሚሆን የተገነዘቡ ሌሎች የዓለም ኃያላን አገራት በሰበብ አስባቡ በቀይ ባህር ላይ የጦር ኃይል እስከመገንባት ደርሰዋል፡፡
ዛሬም ድረስ የቀይ ባህር ቀጠና ጂኦፖለቲካ የሚዘወረው በዋነኞቹ ተዋናዮች ማለትም እንደነ ኢትዮጵያ፤ ኤርትራ፤ ሱዳን፤ ሱማሊያ እና ጅቡቲ ሳይሆን፤ እንደነ አሜሪካ፤ ፈረንሳይና እንግሊዝን በመሳሰሉ የውጭ ሀይሎች ነው፡፡ እነዚህ ሀያላን ሃገራት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የቀጠናው ዋነኛ ተወካዮች በአንድ እንዳይሰባሰቡ፤ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩና በጦርነት እንዲታመሱ በማድረግ ቀጠናውን ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአካባቢው አገራት ውስጥ እየተፈጠረ ያለው ጦርነት፤ የአፍሪካ ቀንድ የጂኦፓለቲካ ቀውስ አካል እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡
አሜሪካ ጥቅም አለኝ ወይም ጥቅም አገኝበታለሁ ብላ ካሰበች የማትፈነቅለው ድንጋይ፥ የማታወርደው መዓት የለም።
ጥቅሟ እስከተጠበቀላት ድረስ በአገራቱ ላይ ለሚደርሰው መመሰቃቀል ብሎም ለዜጎቻቸው ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ደንታም የላትም።
የኋይት ሃውስን አሁናዊ አካሄድ ከተመለከትን በአንድ ወቅት ዶናልድ ትራምፕ ‹ቻይና ደፍራናለች› እንዳሉት ሁሉ፤ ነገሩን በአፍሪካ ቀንድ የጂኦፖለቲካ አተያይ ከተስተዋለ ‹አሜሪካም የኢትዮጵያና ኤርትራን ሉዓላዊነት ደፍራለች› ለማለት ያስገድዳል፡፡
አሜሪካኖች የሚያስቡት በጉልበት፣ በጦር መሳሪያ እና በማዕቀብ እየሆነ ከመጣ ቆይቷል፡፡ ጥቅማቸውን የሚነካ ተፃራሪ ሀይል በማንኛውም ሁኔታ ሲያቆጠቁጥ በተለያዩ ማዕቀቦች እንዲሽመደመዱ በማድረግ በድህነት እንዲማቅቁ ማስገደድ አለም ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ልማዳቸው ነው፡፡
ከዚህ ቀደም አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሲቪል ባለስልጣናት እና በወታደራዊና የደህንነት ሹማምንት ላይ የቪዛ፣ የኢኮኖሚና የፀጥታ ድጋፍ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወቅ ነው፡፡
አሁን ደግሞ በኤርትራ መከላከከያ ሠራዊት፣ የጦር ኃይሎች አዛዥ ፊሊፖስ ወ/ዮሀንስ ላይ በጅምላ ፍጅት፣ በጾታዊ ጥቃት፣ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎችን በመንገድ ላይ ሆን ብለው እንዲገደሉ በማድረግ እና በሌሎችም የሰአብዊ መብት ጥሰቶች በመክሰስ በጥቁር መዝገብ እንዲመዘገቡ መሆናቸውን በግምጃ ቤቷ በኩል አስታውቃለች፡፡
የኤርትራ መንግስት በበኩሉ የጆ ባይደን አስተዳደር በጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ ላይ “ተቀባይነት የሌላቸውን ክሶች ሰንዝሯል” የኤርትራ መንግስትም የተቃጣበትን መሠረተ ቢስ ውንጀላና ክስ በደብዳቤም ሆነ በመንፈስ አይቀበልም ሲል አሳውቋል።
እነ አንቶንዮ ብሊንከን፤ ሳማንታ ፓውር፣ ሱሳን ራይዝ እና ሱሊቫኒን የመሳሰሉ የባይደን አስተዳደር ጋሻ ጃግሬዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ የመንግስት አስተዳደር ላይ እያሳደሩት ያለው ጫና እንደ አሸባሪው ህወሓት ካሉ አጋሮቻቸው ጥቅም አንፃር የተቃኘ፤ አደገኛ አድሏዊ ውሳኔ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡
ዛሬ ላይ ኤርትራ ከናት ሀገሯ ጋር ያላትን የፖለቲካ ቅራኔዎች ሁሉ መፍታት መቻሏ፤ ያልተዋጠላቸው ምዕራባውያኑ “ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም” በሚለው መርህ ዛሬም ኢትዮጵያን ጠላት አድርገው ማዳከምን ተያይዘዋል፡፡
በጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሀንስ ላይ የተጣለው ማዕቀብም የዚህ እኩይ አላማ አካል ነው፡፡
ምክንያቱም ሀገር በታኝ የፓለቲካ አጀንዳ ቀርጸው የኢትዮጵያን ህዝቦች ቢያንስ ለ27 ዓመታት ለእርስ በእርስ ጥላቻና ግድያ ዳርገው፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ የዘረፉትን ረብጣ ዶላሮች በአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አሽሽተው፤ በሠሩት መጠነ ሰፊ ግፍ በህዝብ ተቃውሞና አመጽ ተገደው ከመንበረ ስልጣን ከወረዱና መቀሌ ከመሸጉ በኋላ ህገ-ወጥ ምርጫ ሲያካሂዱ፤ እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገር ወታደር አሰልጥነው የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ሲወጉ፤ አሜሪካኖቹ እያዩ እንዳላዩ ሆነው አልፈውታል፡፡
ሀገር በታኙ ትህነግ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በውድቅት ሌሊት በጅምላ ያስገደሉ፣ የማይካድራ ሰላማዊ ዜጎችን አስጨፍጭፈው በየዋሻው እየተርመሰመሱ በሚገሉና በሚያስገድሉ የህወሓት የሞት ደጋሾች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ቀርቶ ድርጊቱን ለማውገዝ አንደበታቸው እንደታሰረ ነው፡፡
አሜሪካኖች ትህነግን የሚደግፉት፤ በአንድ በኩል በቀንዱ የእጅ አዙር ጦርነት ለማካሄድ የሚያግዛቸው አሸባሪው ትህነግ ታማኝ ተላላኪያቸው በመሆኑ፤ በሌላኛው ገፅ ደግሞ ህወኃት ለግብጽና ሱዳን ከጫካ ጀምሮ የነበረውን ታማኝነት በማስቀጠል በአፍሪካ ቀንድ የጂኦፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ የኢትጵያን ጥቅም ለማስከበር ከተፃራሪ ሀይላት ጋር መደራደር ባለመቻሉ ነው፡፡
ቀድሞውኑ የኤርትራ ከእናት ሀገሯ መነጠል የማይቀር በሆነበት ጊዜ አሜሪካና ደጋፊዎቿ የአስመራና አዲስ አበባ ፍቺ በአግባቡ እንዲፈፀም ማድረግ ቢችሉም አላደረጉትም፡፡
ለምን ቢባል ኢትዮጵያም ትሁን ኤርትራ ወደ ልማት እንዲሄዱ ስለማይፈለግ በዘላቂነት እየተቆራቆዙ እንዲኖሩ ከመፈለግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ዛሬ ትህነግን ከመቃብር አስነስተው ወደ ስልጣን ለመመለስ ሲሉ ሳያፍሩ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሲቪልና ወታደራዊ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ይጥሉ ጀመረዋል፡፡
እውነት አሜሪካ ሰላም ወዳድ አገር ከሆነች የኢትጵያን ግዛት በወረራ ይዘው የኢትዮጵያን አርሶ አደሮችና ንፁሀንን ህይወት እና ንብረት በሚያቃጥሉና ስምሪት በሚሰጡ የካርቱም ጀነራሎች ላይ ማዕቀብ በጣለች ነበር፡፡
ከኢትዮጵያ ውጪ የቀንዱን ቀጠና በታሪክ አጋጣሚ በቅኝ ግዛት ተቆጣጥራ የነበረችው እንግሊዝ እንኳን ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር መወዳጀቷ አልተዋጠላትም፡፡
ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የተረባረቡ የምዕራቡም ሆነ ጎረቤት ሀገራት እና የህወሓት አንጃዎች፤ ከኤርትራ መገንጠል በኋላ ምን ቁም ነገር አትርፈው ይሆን? የሚለው ለእነርሱ የሚተው ጥያቄ ይሆናል፡፡
የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ሀገር ከማፍረስ ያለፈ ግብ የለውም፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢራቅ፣ በሶማሊያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በየመን፣ በሊቢያ፣ በሰሜን ኮሪያ እና ኩባ፣ ወዘተ የፈጸመችውን ማየቱ በቂ ማሳያ ነው፡፡
የዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄው ታድያ ዜጎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው የሀገር ሉዓላዊነትን የሚዳፈርን የውስጥና የውጭ ሀይላትን በጋር መታገል ነው፡፡