>

በጦርነት እሳት ላይ የጣዱትን አማራ መሬቱን የመውረሩ ኦህዴዳዊ ሴራና ስራ....!!! (ወንድወሰን ተክሉ)

በጦርነት እሳት ላይ የጣዱትን አማራ መሬቱን የመውረሩ ኦህዴዳዊ ሴራና ስራ….!!!

ወንድወሰን ተክሉ

ከአጣዬ እስከ ከሚሴ ያለውን የአማራ ክልል ግዛት ወደ ኦሮሚያ  የማካለልን ተልእኮን ይዞ ወደ ከሚሴ የተጋዘውን የዶ/ር አለሙ ስሜን የወሎ ምስጢራዊ ስራና ሴራ
ዛሬ አማራው ሀገር ለማፍረስ ተነስቷል ተብሎ በእነ አቢይ በሚወራው  ትህነግ ጋር  በሁለት የአማራ ዞን ግዛት ውስጥ ብቻውን እየተፋለመ ባለበት ሁኔታ የአቢይ መራሹ ኤህዴድ የአማራን ግዛቶች የመሰልቀጥ ዘመቻ ላይ የአገኘሁ ተሻገር መራሹ ቡድን ሙሉ በሙሉ ተባባሪነትና ተስማሚነት ምክንያት ከሰሜን ሸዋ አጣዬ ጀምሮ እስከ ከሚሴ ያለውን ግዛት ወደ ኦሮሚያ የማካለል ስልታዊ ግን ይፋዊ ስራ በመሰራት ላይ ነው ያለው።
በሰሜን ሸዋ ሰንበቴ ስር ባሉ በርካታ የአማራን  ክልል ቀበሌዎች ወደ ኦሮሚያ የማካላለ ስራ ዛሬ ሀሙስ መፈጸሙን እና እየተፈጸመም ያለ ስለመሆኑ የሰበቴ ቀበሌ አስተዳደር ኮምኒኬሽን መግለጫ ላይ መረዳት የተቻለ ሲሆን ይህንን ተልእኮ ለመፈጸም ዶ/ር አለሙ ስሜ ወደ ከሚሴ መጔዙን ከሁለት ሳምንት በፊት መዘገቤ ይታወሳል።
በወቅቱ የዶክተሩ የሁለት ቀን የከሚሴ ጉዞ የአቶ አገኘሁ ተሻገር ሚና እንዲሁም በአጣዬ በከሚሴ እና በመተከል መሬት ጉዳይ የአገኘሁ ተሻገር ለኦህዴድ ተላልፎ መሰጠትን ጉዳይ እንዴት ተስማሚና ተባባሪ ፈጻሚና አስፈጻሚ ሊሆን እንደቻለ ጭምር አስፍሬ ያሰራጨሁትን ዛኔ ዛሬ በድጋሚ እንዳለ አቅርቤያለሁና ለግንዛቤ ይሆናችሁ ዘንድ ተመልክቱት
 
፠ የኦህዴዱ ቱባ ባለስልጣን ዶ/ር አለሙ ስሜ በአማራ ክልላዊ መንግስት ስር ባለቺው የከሚሴ ዞን ምን ሊሰሩ ነው የሄዱት? ለምንስ ይህንን ተልእኮ እንዲፈጽሙ ነጻነት ተሰጣቸው??
የኦሮሚያ ክልሉ ብልጽግና /ኤህዴድ ከፍተኛ ባለስልጣን በመሆን በፌደራሉ መዋቅር ውስጥ የአቢይ አህመድ አማካሪነትና ጉዳይ አስፈጻሚነቱ የአቢይ ቀኝ እጅ እንደሆነ የሚነገርለት ካድሬው ዶ/ር አከሙ ስሜ ለሁለት ቀናት ጠፈጀ የመስክ ጉብኝት በቤተ አማራዋ ወሎ ከሚሴ ዞን ውስጥ ሲያካሄድ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል።
የዶ/ሩን የከሚሴ ጉብኝትን ዜና  ያስተጋባው ሚዲያ ጉብኝቱ በወሎ ከሚሴ የሚኖሩትን የኦሮሞ ማህበረሰብ አግባብቶ በትግራይ ላይ ለማዘመት ነው ብሎ ድርጊቱን በኩነና መልክ ያቀረበው ቢሆንም እውኑታው ግን የዶ/ር አለሙ ስሜ የከሚሴ ጉብኝት ያልተጠበቀና የአማራ ክልላዊ መንግስት የማያውቀው እንግዳ የሆነ ሳይሆን የተመስገን ጥሩነህ የደህንነትና መረጃ ቢሮ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድድ አቶ አገኘሁ ተሻገር ጽ/ቤትና የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጽ/ቤት በተላለፈ  ትእዛዝ እንዲያውቁት ተደርገው የተሳትፎአቸውን አሻራ ባሳረፉበት ሁኔታ የተፈጸመ መሆኑን በመጀመሪያ ለመጠቆም እወዳለሁ።
የዶ/ር አለሙ ስሜ በአማራ ክልላዊ መስተዳድር ውስጥ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ተብላ በምትጠራው የከሚሴ ዞን ተገኝቶ ከነዋሪው ህዝብ ጋር ለሁሉት ቀናት የተካሄደው ምክክርና ውይይት በከሚሴ ያሉትን ኦሮሞዎች በጸረ ትህነግ ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ባለመ የማግባባት ስራን ለመስራት ሳይሆን በአጠቃላይ ከህወሃት ወታደራዊ ግስጋሴ አኴያ በቀጣይነት ከደሴና ከኮምቦልቻ ቀጥሎ ያለው የከሚሴ ዞን እንደመሆኑ መጠንና ይህ ዞን ደግሞ በአማራ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ያለ የኦሮሚያ ልዩ ዞንነቱ ባህርይ «እኛ ኦሮሞዎች ነን ወደ ወገናችን ኦሮሚያ ክልል እንቀላቀል » የሚል ኦነጋዊ ጥያቄ የተነሳበት አካባቢ በመሆኑ የዶ/ሩ ተልእኮ ይህንን መሰረት ያደረገ እንጂ  ህዝቡን በትህነግ ላይ በማዝመት ደረጃ ለማግባባት ያለመ እንዳልሆነ ነው ከስፍራው የደረሰን መረጃ የሚያመላክተው።
የኦሮሚያው ብልጽግና ኦህዴድ ከዓሙትና ሁለት ዓመት በፊት ለአቻው የአማራ ክልሉ አስተዳዳሪ ብአዴን የወሎ ከሚሴን ዞን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማጠቃለል እንዲሰጣቸው በይፋ ጠይቀው የእንቢታ መልስ የተሰጣቸው መሆኑን እሳቤና ግንዛቤ ውስጥ እንዳስገባን የዶ/ር አለሙ ስሜን የከሚሴን ተልእኮ ውስጠ ሚስጥር ስንመለከት ኦህዴድ እመሰርታታለሁ ብሎ ከወጠንውና በሰሜን ከትግራይ ጋር ከምትዋሰነው ግዙፏን የኦሮሚያን ካርታ እውን ከማድረግ አኴያ ለግዛት ማስፋፋት ጉዳይን ከከሚሴ ህዝብ ጋር  የመከረ፣የዘከረና መመሪያና አቅጣጫ አመላካች መሙሪያና  ትእዛዝ ሰጥቶ መመለሱን ነው መረዳት የቻልነው። ይህ ግን እየሆነ ያለው በራሱ በአገኘሁ ተሻገር በሚመራው የአማራ ብልጽግና  አመራር እውቅና እና ሙሉ በሙሉ ተባባሪነት የመሆኑ ጉዳይ ግን ከሁሉም በበለጠ ጉዳይ የትኩረት አቅጣጫችንን እንድንቸረውና ጠጋ ብለን በጥልቀት እንድንመረምረው ያደርገናል።
የዶ/ር አለሙ ስሜ ከሚሴ ሄዶ  ኦሮሞ የሆነውን የዞኑን ህዝብ በጸረ ትህነግ ዘመቻ ላይ እንዲሳተፉ ሊያግባባ ሞከረ ወይም መከረ የሚለው መንግስታዊውና ኦፊሴላዊውን ዜና ዋጋ ቢስ የሚያደርገው ሲጀመር የከሚሴ ህዝብ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ነው በማለት እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን በአማራ ክልላዊ መንግስት የተመሰረተ ልዩ የራስ ገዝ ዞን በመፍጠር ዞኑን የኦሮሚያ ዞን ብሎ ሰየመው እንጂ  በአጠቃላይ ከበጀት አንስቶ አጠቃላይ ማህበረሰባዊ አስተዳደሩን በአማራ ክልላዊ መንግስት ስር አድርጎ ያለ ከመሆኑ አኴያ ህዝቡን የማዝመትም ሆነ አስተዋጽኦውን እንዲያደርግ የሚያዘውም ሆነ የሚያግባባው ይህው የአማራ ክልላዊ መንግስት እንጂ ጎረቤቱ የኦሮሚያ ክልል ሊሆን አይገባም -አይቻለውምም። በሚሊዮን የሚቆጠር አማራ በሚኖርበት ኦሮሚያ ውስጥ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ሄደው እንዲያነጋግሩና ብሎም ለክልሉ መንግስት ታዛዥና ተገዢ እንዲሆኑ የመከሩበት ወቅትና ሁኔታ ተፈጥሮ ያውቃልን?
ታዲያ ዛሬ ለምንድነው በጸረ አማራነቱና በተለይ በተለይ አማራን ከወለጋ ከመተከልና ከአጣዬ ጨፍጭፎ በማፈናቀሉ እርምጃ ላይ ከበስተጀርባ ሆኖ እንደ ቀያሽ መሀንዲስ እጁን በትልቁ እንዳስገባ የሚነገርለትን የአቢይ አህመድ ቀኝ እጅ ዶ/ር አለሙ ስሜን ወደ የውዝግብ ማእከል የሆነቺው ከሚሴ በመላክ ከህዝቡ ጋር በኦሮሚኛ ብቻ እንዲመካከር የተደረገው ? የተፈቀደውስ ብለን ስንጠይቅ በዚህ የኦሮሚያን ግዛት በማስፋፋቱ ምስጢራዊና ህልመኛ ዘመቻ ላይ የአማራን ህዝብ እንወክላለን ብለው በህዝባችን ጫንቃ ላይ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ያህል የተጎለተውን የብአዴንና አመራሩን ግልጽ የተሳትፎ ሚናን እናያለን ማለት ነው።
እዚህጋ ይህንን ሁኔታ በተጨባጫ ከሚያረጋግጥሉን እጅግ በርካታ ክስተቶች ውስጥ ሁለት ምሳሌያዊ ክስተቶችን ብቻ ለአብኑት ያህልጥቀስ።
የአማራይቱ ኤፌሶን/አጣዬና ከመተከል ተፈናቅለው በቻግኒ መጠለያ ውስጥ ያሉትን ተፈናቃይ አማሮችን ጉዳይ በማሳየት በአቶ አገኘሁ ተሻገር የሚመራው የአማራ ክልላዊ መንግስት የኦህዴድን የግዛት ተስፋፊነት እውን በማድረግ ደረጃ እየተጫወተ ያለውን የሙሉ በሙሉ ተባባሪነትን ሚና ለማሳየት እወዳለሁ።
አጣዬ በወራሪውና ጨፍጫፊው የኤነግ ተብዬ ሰራዊት ግን በሽመልስ አብዲሳ የሚመራ ሽፍታ ሰራዊት ጦርነት የተከፈተባት እለት የከተማዋ ከምቲባ ወደ አዲስ አበባ የፌዴራሉ መረጃና ደህንነት ምኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህና ወደ ባህርዳሩ አቶ አገኘሁ ተሻገርጋ ደጋግሞ በመደወል ከአቅማቸው በላይ በሆነና እስከአፍንጫው በታጠቀ ሰራዊት መወረራቸውን በመግለጽ አስቸኴይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሲማጸኑ ሁለቱም ባለስልጣናት እንቢ ከማለትም አልፈው ስልካቸውን እስከማጥፈትና ግንኙነት እስከማቌረጥ በደረሰ እርምጃ የአጣዬ ህዝብ ድጋፍ እንዳያገኝና ጦርነት በከፈተበት የኦሮሚያ ወራሪ ሰራዊት ተጨፍጭፎ እንዲጠፋ ያደረጉ ናቸው። በዚህ ድርጊታቸውም ሳይታቀቡ አጣዬ ሙሉ በሙሉ ከወደመችም በኋላ እስከዛሬዋ  እለት ድረስ አንድም የአማራ ክልልና የፌዴራሉ ባለስልጣን ዝር ብሎ ባለመጎብኘትና የፈረሰውንም ከተማ ዞር ብሎ ባለማየት ህዝቡ ተማርሮ እንዲጠፋ እያደረጉ ያሉ መሆናቸውን ለማስታወስ እወዳለሁ። ሁለተኛው የአገኘሁ ተሻገር አስተዳደር ቻግኒ ሄዶ ከመተከል ተፈናቅለው ያሉትን አማሮች ወደ ተፈናቀሉበት ከመመለስ ይልቅ ለተፉናቃዩ ህዝባችን ያሰበና ያዘነ በመምሰል ወደ ጎንደርና ጎጃም ወስደን እናስፍራችሁ በማለት የኦህዴድን አማራን ከመተከል የማጽዳት ዘመቻን ለመተግበር መጣሩን ለማስታወስ አወዳለሁ።
ሁለቱ ክስተቶች የአገኘሁ ተሻገርን ከኦህዴድ ጋር ያለውን እጅግ ስር የሰደደ ግንኙነት ታማኝ አገልጋይነትን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን ለአማራ ህዝብ ደግሞ እጅግ አሰቃቂ ስቃይ ምንጭና መንስኤ መሆኑንም ያሳያል።
ዛሬም የአገኘሁ ተሻገር ብአዴን የወሎ ከሚሴን ህዝብ በትማኝነት ለሚያገለግለው ኦህዴድ ሙሉ በሙሉ አሳልፎ በመሸጥ የተስማማ ይመስል ለዶ/ር አለሙ ስሜ ወደ ከሚሴ ሄዶ ህዝቡን ኡንዲያዘጋጀ እንዲቀሰቅስና ትእዛዛዊ አመራር እንዲሰጥ በማድረግ ተግባሩ ሲተባበር ለማወቅ ነው የቻልነው። ግን ለምን??
፠ ትኩረት ያልተሰጠው የኦነግ ወታደራዊ ዘመቻ በኦሮሚያ፦
ኦነግ በአምስቱ የኦሮሞ ታጋዮቻ ስም የሰየመው የጸረ ብልጽግና ወታደራዊ ዘመቻ በአጭሩ ሲቃኝ።
የኦህዴዶቹ ደደቡ ታዬ ደንደአ እና አዲሱ አረጋ ኦነግ ከትህነግ ጋር የጋራ ጥምረታዊ ግንባር በመፍጠሩ በውስጣዊ አመጽና እርሰበርስ ጦርነት እየናጠ ነው እያሉ በተከታታይ በሚያስተጋቡበትና የመላው ኢትዮጲያዊ ሁለንተናዊ አትኩሮት በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ በሆነበት ሁኔታ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ኦነስ [OROMO LIBERATION ARMY/ OLA ብሎ የሚገልጸው የኦነግ ኋይል በታዋቂ አምስት የኦሮሞ ታጋዮች ስም የሰየመውን ጸረ ብልጽግና ወታደራዊ ዘመቻን በአራቱም የኦሮሚያ አቅጣጫ ከፍቶ በማጧጧፍ ላይ ስለመሆኑ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
በደቡብ፣ በዱቡብ ምእራብና በደቡብ ምስራቅ በታጋዮቹ ኤሌሞ ቂልጡና ነዲ ገመዳ ስም በተሰየመው ወታደራዊ ዘሙቻ በቦረና እና በጉጂ ለገደንቢ (ሻኪሶ የወርቅ ማምረቻ ያለበት) አካባቢ በለስ እንደቀናው የዞኑን ዋና ከተማን ጨምሮ የሞያሌ ሀዋሳን ዋና አውራ መንገድን መቆጣጠር መቻሉን አውጃል። ይህ ጸሃፊ የጉጂ ዞንን ማጣራት ባይችልም ባለው የግል ኔትዎርክ በሞያሌና አካባቢው ያለውን ሁኔታ ደውሎ ለማረጋገጥ የቻለ ሲሆን በርካታ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኋይሎች በወደ ገብነት ከእነትጥቃቸው ወደ አማጺው ጎራ መቀላቀላቸውንም ማወቅ ችሏል።
በመሀል በምእራብና በስሜን ኦሮሚያ በታጋይ ለገሰ ወጊ ጄ/ል ታደሰ ብሩና በታጋይ ሀሰን አሚ ስም በተሰየመ ወታደራዊ ዘመቻ በሸዋ በተለይም በምእራብ ሸዋ ኦሮሚያ ዞን ከጋንጪ እስከ ግንደበረት – ማለትም  በጋሌሳ ጀልዱ ሽኩቴ ግንደበረት/ካችሲ በሜታ በክልቤ በኦሶሌና ተጎራባች ወረዳዎችና አውራጃዎች ውስጥ የኦነግ ሰራዊት በስፋት እየተዋጋ መሆኒንና አብዛኞቹን መስተዳድሮችን በእዙ ስር ማስገባት መጫሉንም ይህ ጸሀፊ በቱጠቀሱት ወረዳዎች ውስጥ ባለው የግል ግንኙነታዊ ኔትዎርክ ደውሎ ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን በምእራብ ኦሮሚያ በአራቱ የወለጋ ዞን ውስጥ ኦነግ አገኘሁ ስለሚለው ድል በግል መረጃው ባይኖረኝም ከመግለጫቸው ላይ በመመስረት መግለጽ ዩሚቻለው የታዬ ደንደአ የትውልድ እድገት ስፍርን ጨምሮ በርካታ ስፍራ ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን መንግስት ከነቀምት በስተቀር ምእራብ ኦሮሚያን በአጠቃላይ የኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነትን እንደቆረጠን ነው ማወቅ የተቻለው።
መቀጫውን ነቀምት ላይ ያደረገውና በቄንጠኛው ብ/ጄ ባጫ ደበሌ የማመራው የምእራብ ኦሮሚያ ኮምንድ ፖስት በወለጋ ሆሮጉዱሩ እየተካሄደ ያለውን አማራ ተኮር ጭፍጨፋን ከአካባቢው ታጣቂዎች ጋር ሆኖ የሚያስፈጽምና የሚፈጽምም ሰራዊት ነው የሆነው እንጂ በአማጺው ላይ ጦርነት ከፍቶ የሚዋጋ አልሆነም በማለት ነው የጭፍጨፋው ሰለባ ተራፊዎች በግለጽ የኦነግን ወታደራዊ ዘመቻን ከሞላ ጎደል ያረጋገጡት።
ከሳምንት በፊት የኦሮሚያው ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ አዲስ አበባ ላይ በጠራው ሰልፍ ላይ ያስተላለፈውን መልእክት የሰማ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ጸረ ብልጽግና ወዳጄ  እንደነገረኝ «ሽመልስ እጅግ ከመፍራቱ የተነሳ ህዝቡን ሲማጸን ነው የዋለው። ግን እንዲህም ተማጽኖ እሱና አቢይ ዛሬ ከአዲስ አበባ ወጥተው ወደ የትኛውም የኦሮሚያ ወረዳ መሄድ የማይችሉ ናቸው። ብቸኛ የመሄጃ ስፍራቸው አዳማና አምቦ እንኴን ዛሬ መሄድ የማይችሉ የአዲስ አበባ እስረኞች ናቸው» በማለት የኦሮሚያው ብልጽግና ያለበትን ድምጽ አልባ ህዝባዊ አመጽና በህዝብ መተፋትን የገለጸልኝ።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የአቢይ መንግስት ያለውን ተቁባይነትና ያልፈነዳ ግን ውስጥ ውስጡን የተቀጣጠለን ከፍተኛ ቁጣ አመጽና ጸረ አቢይ አቌሞችን በቅርበትና በጥልቀት አውቃለሁ። ሆኖም ይህ ውስጥ ለውስጥ ኡሚብላላ ታላቅ ቁጣና አመጽ ወዱዬት እንደሚያመራ አላውቅም።
የትህኑግና ኦነግን ጥምረታዊ ስምምነት ጥሩ ነው መጥፎ ነው በሚል ምዝና ውስጥ ሳልገባ በአጠቃላይ በሰሜኑ ኢትዮጲያ በአማራ መሬት ላይ እየተካሄደ ካለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወጣ ስንል የኦሮሚያን ወቅታዊ  ሁኔታን ለማሳየት በትክክል ነው ትክክል አይደለም ምዘና ውስጣ ሳልገባ በተቻለ መጠን የተከሰቱትን ክስተቶችን እንዳለ ለማቅሩብ በማሰብ ነው።
ግን ግን ይህ ጦርነት ወዴየት እያመራ ይሆን ? ወዴየትስ አቅጣጫ እየወሰደን ይሆን? ይህ ሁሉስ እልቂት ለምን አስፈለገ? ችግሮቻችንን በጦርነት መፍታት ይቻለን ይሆን? በጦርነት ችግር የፈታስ አለ? በዚህ የእርሰ በርስ ጦርነትስ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ማን ይሆን? አሸናፊነቱስ ምን አይነት አሸናፊነት ይሆን በሚሉ ጥያቄዎች እራሴን መጠየቄ መልሳቸውንም ከተለያየ አቅጣጫ ለመቃረም መጣሬ ግን ይቀጥላል።
Filed in: Amharic