>

የእነ እስክንድር መልእክት! (አትክልት አሰፋ)

የእነ እስክንድር መልእክት!

አትክልት አሰፋ

የዛሬ ቀጠሮዬ እስክንድርን ማየትና ማየት ብቻ ነበር። እስኬን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት ዳላስ ቴከሳስ ከብዙ ወደጆች ጋር በአንጋፋው ጋዜጠኛ አቶ ከፍያለ ማሞ ልጅ ሚሚዬ ቤት ነበር። ከታላላቅ እስከ ኔ ቢጤ ተሰብስበን የረጅም ጊዜውን የፕሬስ ተጋድሎ አውግተናል። ታጋቹን (እሰረኛ ላለማለት ነው) ወደጄን ለማየት ቂሊንጦ ከመሄዴ በፊት የነበረኝ መረጃ ለየት ያለ ነበር። አስቸጋሪ መሆኑንና ከአንድ ሰው ውጭ ማየት እንደማይፈቀድ ከተቻለም ከሰኞ እስከ አርብ እንድሞክር…!
ቅዳሜ ጠዋት 2 ሰዓት አካባቢ ስንደረስ ተሰለፈው የተቀመጡ በርካታ ጠያቂዎች ወደተሰበሰቡበት ዳስ አመራን።  እስክንደር ያለበትን ዞን ለማወቅ አንዱን የጥበቃ ፖሊስ ጠጋ ብዬ … እስክንድርን ለመጠየቅ ነበር አልኩት
እስክንደር… እስክንደር… እስክንደር እስክንደርስ… ስሙን ደጋገመው።
እስክንደርስ ነጋ አልኩት ለማረጋገጥ
ፖሊሱ እንደገና ስሙን ደጋገመ…
አያይዤ እንግዳ ነኝ ስል ጨመረኩ… ትንሽ ቆይቶ …እሽ ዞን አራት ላይ  ተመዘገብ አለኝ።
መዝጋቢው ጋር ስደረስ መታወቂያየን በትሕትና ጠይቆ መዝግቦ ከጨረሰ በኋላ አብሮኝ የነበረውን ታናሽ ወንድሜን እያየ እሱስ ይገባል ሲል ጠየቀ።
…እንዴ ጭራሽ ለራሴም ሳልጠይቅ እንዳልመለስ የፈረሁ ሰውዬ… ይሄ እድል ተገኝቶ ብዬ አዎ ይገባል ብየ ወንድሜንም አስመዘገብኩ።  330 ላይ  ወደውስጥ እንድንገባ ተፈቅዶልን ገባን። የጥበቃ ፖሊሶቹ ሁሉም ማለት ይቻላል በትሕትና ሲያስተናግዱ አስተውያለሁ…
እስክንድር ይወደዋል ያልኩትን መፅሀፍ (ፎቶ) እና መጽሔት እንዲሁም ቼኮሌት ማስገባት አይፈቀድም ስለተባልኩና በስራ ቀን ሞክር ብለዋልና በስራ ቀን ተመልሼ ለመሔድ ተሰማማሁ።
እስኬው ተጠረቶ ሲመጣ ትህትናው እንደተጠበቀ ሆኖ  ከመልካም አቋም ጋር ነበር ያገኘነው። ጥሩ ነው ያለኸው አልኩት ከሰለምታ በኋላ …እግዚአብሔር ይመሰገን ሰላም ነን አለኝ…
ከእስኬው ጋር ሰለወዳጅ ዘመዶች፣ ሰለመገናኛ ብዙሀን ስለአገራችን ሁኔታ  አወጋን… ስንታየሁ ቸኮልም ፀሎት ላይ ስለነበረ ዘግየት ብሎ መጣ። የመንፈስ ጥንካሬያቸው ደስ ያሰኛል። ብረቱው ሰው አሁንም በፖሊሶች ተከቦ እንኳን ሳይፈራ፣ ሳይሸማቀቅ ሲናገር መስማት እርካታ አለው። አሁንም ስላለው የካድሬዎች አሰራር… የህዝብ መንገላታት… ስለጦርነቱ ሲናገር ከጎናችን የነበሩ አራት ፖሊሶች አፋቸውን ከፍተው ሲሰሙ አይቻለሁ። ለነገሩ ትግሉስ ለእነሱ አይደለ? ለራሳቸው
የሚገርመው ሌላ ጠያቂ መጥቶ የእስክንድር ስም ሲጠራ ሰምቼ ዘወር ስል ሚሚዬ ከጎኔ ናት ሚሚዬ የታላቁ ጋዜጠኛ ከፍያለ ማሞ ልጅ… ሚሚ። ትንሽ አለም…  እስኬውን ዳላስ ቴክሳስ ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት እሷ ራሷ ሚሚዬ ግቢ ውስጥ ነው (ፎቶ)። አሁን ደግሞ ቂሊንጦ ልንጠይቀው ጎንና ጎን ሆነን በእሾህ አጥር እያየነው ነው። ለአንድ ሰዓት ጥቂት ደቂቃዎች እስኪቀሩት ከእስኬውና ስንታየሁ ጋር አወራንና ተለያየን። ሚሚ ወደ አዲስ አበባ ከመጣች ደጋግማ ጠይቀዋለች። እድለኛ ነኝ ከወንድሜ ጋር አስገቡኝ ሰላት ዛሬ ጥሩ ናቸው በስነስርአት ነው የሚያስተናግዱት አለችኝ። ትእዛዝ ሲመጣ ነው ሙዳቸው የሚቀየረው እንደማለት…
ስንታየሁ – እኛ በመታሰራችን ሀገራችን ሰላም የምታገኝ ከሆነ በመታሰራቸን አናዝንም
እስክንድር – ሁሉንም ሰላም በልልኝ። እከሌ ከከሌ ሳትሉ ለሁሉም ስላምታየን አድርሱልኝ!
ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ2014 አዲስ አመት አደረሳችሁ። አዲሱ አመት የሰላም የፍቅር የደስታ ይሁንላችሁ ብለዋል።
ድል ለዲሞክራሲ!
አድርሻለሁ
ኢትዮጵያ  እስከለዘለዓለም – ዓለም
Filed in: Amharic