>
5:21 pm - Tuesday July 20, 2832

ከጅብ ስነ ልቦና ያነሰዉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ስነ - አፈጣጠር...!!!( ሸንቁጥ አየለ)

ከጅብ ስነ ልቦና ያነሰዉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ስነ – አፈጣጠር…!!!
ሸንቁጥ አየለ

የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች መሰረታዊ አቋማቸዉ ሲመረመር ከጅብ ስነልቦና ያነሰ ነዉ::ይሄም ላለፉት ሰላሳ አንድ አመታት የዘለቀ እዉነታ ነዉ::
ልክ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተፈቅዷል ሲባል ወደ ፖለቲካ ትግል ጎራ ካሉት ሰዎች ዉስጥ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር አስራት ነበሩ::
ወያኔዎች በጥልቅ መርሃቸዉ”አማራን በማሰር እና በመግደል እናንበረክከዋለን::ኦሮሞን ደግሞ እያታለልን እንዳሰኘን እንጫወትበታለን” ብለዉ ገና ከመጀመሪያዉ ስትራቴጂ ነድፈዉ ነበር::
እናም ኦሮሞዉ መራራ እና አማራዉ አስራት ያነሱት የህዝብ ጥያቄ ተመሳሳይ ቢሆንም ወያኔዎች ለመራራ ጉዲና ለስላሳ ልብ ያለቸዉ በመምሰል አንዴ ቆጣ አንዴም ጨበጥ እያደረጉ ይልቁት ስለነበረ መራራ እራሱን ብልጥ አድርጎ “እኔ እምታገለዉ ቀዝቃዛ ቢራ እየጠጣሁ ነዉ” እያለ ይዘባነን ነበረ::
ወያኔዎች እነ ፕሮፌሰር አስራትን እስከ ሞት ድረስ አስረዉ ሲያሰቃዩዋቸዉም እነ መራራ ባላዬንም ባልሰማንም ያልፉት ነበር::በእነ መራራ ቤት ወያኔ ለእነሱ የተሻለ የስልጣን እድል የምትፈጥርላቸዉ እየመሰላቸዉም አንዳንዴ አደባባይ እየወጡ አንዳንዴም በድራፍት ቤት “እነ አስራት አክራሪ የኢትዮጵያዊነት/የአማራነት ፖለቲካ ስለሚያራምዱ ነዉ ወደ ወህኒ የተጣሉት” እስከማለት ይደርሱ ነበር::
መሰሎቻቸዉ ተቃዋሚዎች ሲታሰሩ ሲገደሉ ሲሳደዱ እነሱ ብልጥ ተቃዋሚ የሆኑ እየመሰላቸዉ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በዝምታም ከወያኔ ጋር በመተባበር ሌሎች ተቃዋሚዎችን ያስበሉ ነበር::
ከተቃዋሚዎች ይልቅ ወያኔን አምነዉ 27 አመታት ተጉዘዋል:: ሆኖም ወያኔ የቋመጡለትን ስልጣን ሳታልሳቸዉ ከራሳቸዉ ከወያኔዎች ጉያ የተወለዱት እነ አቢይ ስልጣኑን አፈፍ አድርገዉ ያንኑ የአንባ ገነነት እና የጎሳ ፖለቲካቸዉን ቀጥለዋል::እነ መራራም አሁን ድረስ እጃቸዉ ስልጣን ስላልገባ ከነሱ በአላማ በምንም የማይለዬዉን አቢይንም ተቃዋሚ ሆነዉ ቀጥለዋል::
አሁንም የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ተመሳሳይ ከጅብ ስነልቦና ያነሰ የስነ ፍጥረት ስሪታቸዉን እያስመሰከሩ ነዉ:: እስክንድር ነጋ እና ከእርሱ ጋር ያሉ ጠንከር ያለ ተቃዉሞ በአቢይ ላይ ቢያነሱ ዘብጥያ ወርደዋል::የተለያዩት ተቃዋሚዎች ግን ያንኑ ከጅብ ስነልቦና ያነሰ አካሂያዳቸዉን እየተከተሉ ነዉ::
አንዳንዶቹ እነሱ ምርጫ የሚያሸንፉ መስሏቸዉ አቢይ ላይ ተንጠላጥለዉ የኦህዴድን ጎሰኛ ሀይል ደግፈዉ የእነ እስክንድርን ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሀሳብ አክራሪነት ነዉ ሲሉ ከረሙ::
ሌሎችም የክልል ስልጣን አባዝኗኗቸዉ የእነ እስክንድርን ነገር ያነሳ ዉሾ ሲሉ ከረሙ::እንዴዉም እርስ በርሳቸዉ ከመተባበር እርስ በርሳቸዉ መነጣጠል እና መፈረካከስን እንደ ትልቅ ግብ ወስደዉ በምርጫ ምንም ዉጤት ሳያስመዘግቡ ባዶ እጃቸዉን አጨብጭበዉ ወጡ::ትግላቸዉንም እርስ በርስ በማድረግ ደመደሙ::
አሁንም አብዛኛዉ ተቃዋሚ በሚባል መልኩ እነ እስክንድርን በአክራሪነታቸዉ ታሰሩ የሚል እና የዝምታ ተባባሪነቱን ቀጥሎበታል::ይባስ ብሎም አቢይን ወደ ማምለክ የተሸጋገሩም ተቃዋሚዎች እየበዙ ነዉ::
አቢይ ስልጣኑን ካደላደለ ብኋላ እያንዳንዱን ተቃዋሚ እንደ መለስ ዜናዊ ሰብስቦ እንደሚያስረዉ በመርሳት አሁን በገፍ ስለታሰሩ ወገኖች ምንም አለማለትን መርጧል::የእነ እስክንድርን ነገር ያነሳ ዉሾ ነዉ ተባብለዋል::
ይህ ወቅት ለተቃዋሚዎች መንግስትን ለመምከር ብሎም በገፍ ያሰራቸዉን ለማስፈታት በጋራ እንዲቆሙ ጥሩ የድርድር መሰረት ፈጥሮላቸዉ ነበር::
ግን ተቃዋሚዎች ከጅብ ስነልቦና ያነሰ መሰረት ላይ ቆመዋል እና ከቶም ስለ ሌላዉ ተቃዋሚ ፍትህ ግድም አይሰጣቸዉም::
ጅብ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር ብለህ ጠይቅ:: ጅብ ሊበላዉ የሚያስበዉን እንስሳ ከማጥቃቱ በፊት አንዴ እየቆመ አንዴም እየተቀመጠ አንዴም እየተንቆራጠጠ ይለካዋል::
ተቃዋሚዎች የራሳቸዉን የነገ የመታሰር እጣ ፈንታ የጅብን እስትራቴጅ እንኳን በመጠቀም ለማስቀረት አይግተረተሩም::
—–
ለማንኛዉም በዚህ አዲስ አመት ተቃዋሚ ነን የምትሉ ሁሉ በጋራ ሆናችሁ አላግባብ የታሰሩት:ፍትህ በላያቸዉ ላይ የተደፋባቸዉ እነ እስክንድርን መንግስት ተብዬዉ በአስቸኳይ እንዲለቅ የጋራ መግለጫ አዉጡ::ይሄ አጭር ምክር እና ማሳሰቢያ ነዉ:: በዚህች ጉዳይ ላይ እንኳን እስኪ ከጅብ ያነሰ የስነ ልቦና ስሪት አይኑራችሁ !
Filed in: Amharic