>

የባልደራስ አመራሮችን በመፍታት በየዕለቱ ከሚጠዘጥዝ ከሕሊና ስቃይ መገላገል ይበጃል!!  (በቃቢል ተሰማ)

የባልደራስ አመራሮችን በመፍታት በየዕለቱ ከሚጠዘጥዝ ከሕሊና ስቃይ መገላገል ይበጃል!! 
በቃቢል ተሰማ

በእስር ላይ የሚገኙ የባልደራስ አመራሮችን አንዳቸውንም በዓይነሥጋ አግኝቼያቸው አላውቅም፤ በድምፅም አነጋግሬያቸው አላውቅም። ነገር ግን ከአስካል ደምሌ በስተቀር ሁሉንም አሁን ከመታሰራቸው በፊት ስላሳለፉት ፖለቲካ ነክ የውጣ ውረድ ሕይወት ቢያንስ የአንድ ጊዜ ገጠመኞቻቸውን ለማወቅ ችያለሁ። ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው የሥራ ጓደኛው የሆነ ጋዜጠኛ ከአዲስ አበባ ታፍኖ ወደ ሰንዳፋ ተወስዶ ታስሮ በነበረበት ጊዜ፤ የጓደኛውን ችግር ሊጋራ በመጣሩ የደረሰበትን ችግርን ማንበቤን አስታውሳለሁ።
ከዚያ ቀደም ብሎ ጌጥዬን አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን በወቅቱ የጌጥዬ ታማኝነቱና ብርታቱ አስገርሞኝ ነበር። ጋሽ ታዲዮስ በቅንጅት ጊዜና ከዚያም በፊት ታስረው እንደነበርና፤ ከእስር ሲፈቱም በሚፅፉበት ጋዜጣ ላይ ከነበረው ፎቶዋቸው (ታዋቂው የፀጉር ስታይላቸውን ጠብቀው) በጣም መጎሳቆላቸውን ማየቴንና ልቤ ማዘኑን አስታውሳለሁ። ስንታየሁም በወያኔ ሲሳደድና ሲታሰር እንደነበር፤ ከዚያም መፈታቱን አስመልክቶ ይቀርቡ ከነበሩ የዜና ዘገባዎች ስለ ስንታየሁ ተረድቻለሁ። የዶ/ር ዐቢይን ወደሥልጣን መምጣት/የወያኔ ከማዕከላዊ መንግስት ትንሽ ራቅ መደረጉን ተከትሎ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይም በአዘጋጅነት የተሳተፈበትን ፕሮግራም አይቻለሁ። በቀለብ ስዩም ላይ ልብ የሚሰብሩ ተከታታይ ግፎች ሲፈፀሙባት እንደነበር ተከታትያለሁ።
ፍፁም ጨካኝ በሆነ መንገድ በተደጋጋሚ የተሰነዘሩባት ጥቃቶች በጣም እንዳቆሰልዋት ነገር ግን የአርማጮሂቷ ልጅ እንደልማዷ ሱሪዋን ታጥቃ መታገሉን እንጂ፤ በጥቃቶቹ ተንበርክካ በማፈግፈግ ከዓላማዋ እንዳልወጣች ከዜናዎችም ከመፅሃፉዋም ተከታትያለሁ። የእስክንድርን የእያንዳንዱ የግፍ እስርና በየጊዜው የሚደርስበትን አስነዋሪ ነውረኛ ርምጃም በየጊዜው “ወቸው ጉድ” እያልኩ ተከታትያለሁ። ፅናት ብርታቱን በተደጋጋሚ ያልመሰከረለት የለምና ልለፈው። ሰሞኑን እንኳን ብዙዎች ስለእነ እስክንድር የግፍ እስርና፤ “የእባካችሁ ፍቱዋቸው” ተማፅኖ ባቀረቡባቸው መልዕክቶች ብዙ ብለዋል። እኔ በዚህች አጭር ማስታወሻ ማንሳት የምፈልገው ዋና ጉዳይ የእስክንድር መግዘፍ ወይም የእስክንድር ታሪክ መድመቅ እስክንድር ከሰራው መልካምና ቀና ሥራ ባልተናነሰ መልኩ “ተቀናቃኞቹ” የእስክንድር ታሪክ በጉስቁልናቸው ስላደመቁት መሆኑን ለማሳየት ነው።
እስክንድርና ጓደኞቹ እንደ ፖለቲከኛ ለአዲስ አበባ ይበጃል ያሉትን ሀሳብ በሰላማዊ መንገድ ከማራመድ በላይ፤ እንደ ሰብዓዊ ተሟጋች ከተበደለ አዲስ አበቤ ጋር በአካል ተገኝተው “በሕግ አምላክ” ከማለት በላይ፤ እንደ ተራድዖ ሰራተኛ በመሆን ከተቸገሩ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ሕመም ችግራቸውን ሲካፈሉ አይተናል። ይህ ሲሆን ግን ሥራውን ያከናወኑት አልጋ በአልጋ በሆነ መድረክ አልነበረም።
 “እስክንድር መፈተን አለበት!” የሚል ሕግ ያለ እስኪመስል ድረስ እስክንድር በየቀኑ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ተፈትኗል። የእስክንድር መብት በኢትዮጵያ ውስጥ ከድጡ ወደማጡ እየሄደ ይመስላል። በወያኔ ዘመን እስክንድር በተደጋጋሚ ታሰረ፤ ልጁንም በወህኒ ወለደ፤ በለውጡ ጊዜም እስክንድር በተደጋጋሚ ታሰረ፤ የሚወደውን ባልደራስ በመንገድ ላይ ወለደ። እስክንድር ባልደራስን የወለደበት መንገድ፤ የእስክንድር ፈጣንነቱን፤ የላቀ ንቁነቱንና በቅፅበት ጥሩ ውሳኔ መወሰን የመቻል ክህሎቱን ያሳየበት አጋጣሚ ነበር።
ባልደራስ በመንገድ ላይ መወለዱንና ሥራውን ወዲያውኑ መንገዱ ላይ መጀመሩ ሲያበስር፤ ብዙዎች ተሳልቀውበት ነበር። እስክንድር ለፓርቲው ምስረታ ዝግጅት የተደረገበት ሆቴል በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ሲከለከል፤ አጥማጆቹ ያጠመዱበትን ወጥመዶች ብሩህና ፈጣን በሆነው አዕምሮው ተጠቅሞ በጣጥሶ ማለፉን ብዙዎች የተረዱት ሰንብተው ነበር። እዬዬ ሲል ወይም ሲቆዝም አልታየም። ይልቁንስ መንገድ ላይ የተወለደው ፓርቲ ሊላ ወጥመድ ሳያዘጋጁለት ፈጥኖ ሕጋዊ የሚሆንበትን መንገድ ላይ መትጋት ነበር። እንዳሰበውም አስፈላጊውን መስፈርቶቹን አሟልቶ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ያቀረበው ፈጥኖ ነበር። ለዚህም የባልደራስ አመራሮችን ችሎታና ትጋት አለማድነቅ ንፉግነት ነው። እስክንድር የፓርቲውን መወለድ መንገድ ላይ ማወጁንና መንቀሳቀስን ትቶ በፍርድቤት መብቴን ላስከብር ቢል ኖሮ፤ አሁን በምናየው ፍርድቤት ዕውን መብቱ እንደማይከበር ለአፍታ አልዘነጋም። ይህ በቅፅበት የተወሰነ ግን ፍፁም ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑ የሚያሳየው የእስክንድርን ፍጥነትና ባለስል አእምሮን መሆኑን ብቻ ነው። አለበለዚያማ እስክንድር በዛሬዋ ኢትዮጵያ መብቱን በገሃድ የተገፈፈ ግለሰብ ነው!
እስክንድር እኮ ተለይቶ የቴሌቪዥን ጣቢያ በገንዘቡ ማቋቋም አልተፈቀደለትም፤ እስክንድር እኮ ተለይቶ የፓርቲውን መግለጫ በሆቴሎች ውስጥ ገንዘቡን ከፍሎ ማካሄድ አልተፈቀደለትም፤ እስክንድር በራሱ ቢሮ ውስጥ መግለጫ መስጠት አልተፈቀደለትም፤ እስክንድር ለተቸገሩ ወገኖች የሚችለውን ርዳታ እንዳይሰጥ የተከለከለ ነው። በግል ህይወቱ ላይ የሚደረግበትን ጫና የማወቅ ዕድሉ የለኝም እንጂ ብዙ የሚያስብል እንደሚሆን አልጠራጠርም። ነገር ግን ይህ ሁሉ ያገጠጠ የመብት ረገጣ በእስክንድርና ጓደኞቹ ላይ ሲካሄድ “ኧረ ይህም በዛ” የሚሉ የሀገሪቱ “ኤሊቶች” አልታዩም።
ይልቁንስ የየዕለት መሰናክሎቹን በስል አዕምሮውና ቁርጠኝነት የሚያልፈውን እስክንድርንና ባልደራስን ለማንኳሰስ ብዙ የኳተኑት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን “ተቃዋሚ” የሚባሉ ግለሰቦችም ነበሩ። ማሰብ በሚችሉበት መጠን ወይም ማሰብ በተፈቀደላቸው ልክ ያህል ለእስክንድር ከ”እብድ” እስከ “የፖለቲካ መደዴ” የሚል ስያሜ ለመስጠት ዳድተዋል። ሰውየው ግን ለሀገርና ለወገን አርቆ አሳቢነቱንና የአስተሳሰብ አድማሱን በድፍረትና በሰላማዊ መንገድ ለአዲስ አበባ፤ አሜሪካና አውሮፓ ኤሊቶች በመድረክ አቀረበ፤ አሳሳቢነቱንም አሳሰበም። እየዋለ እያደረ ይህ ርምጃ ሀገር ውስጥ ያሉ አድርባዮችና ሸፍጠኞችን በራሳቸው እንዲያፍሩና ድውይ እንደሆኑ እንዲያምኑ ማድረጉን ግን ማንም አይክደውም። ለማደርም ይሁን ማሰብ ተስኖአቸው እንደሆነ ባይታወቅም ተስፋቸውን በግለሰብ ላይ ያደረጉትን ሁሉ ቢያንስ የረባ አለመስራታቸውን ፤  ከዚያም ላቅ ካለ ደግሞ የ“ሕዝባዊነታቸውን” መጠን ሕዝብ እንደተረዳውና ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው ወለል ብሎ ታያቸው። በአንፃሩ ግን ይህ ሕዝባዊ ርምጃ የእስክንድርን ታሪክ የሚኩልና የሚያሸበረቅ ሆነ። የእስክንድር ቁመና የመግዘፉ አንዱ ምክንያት በሥራው ምክኛት ከጨመረው ቁመት ሌላ የእኒህ “ማሰብና ለእውነት መቆም ለምኔዎች” ቁመት እየጫጨ በመሄዱ የተነሳም በሚጨመር ርቀት ምክንያትም ጭምር ነው።
በእነ እስክንድር ላይ የደረሰው በደል ከላይ የገለፅኩት ብቻ አይደለም። ለጊዜው ተሞክሮ ሳይሳካ የቀረ ቢሆንም የባልደራስ አመራሮች ሰብዓዊ መብታቸው በሕገ ወጥ መንገድ አንዲታገድ የተሞከረው አስተዛዛቢ መከራ አንዱ ነው። በምርጫው ሰሞን የታሰሩት የባልደራስ አመራሮች ገና እንኳን ሳይከሰሱ “በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች የመምረጥ መመረጥ መብታቸው እንዲከበርላቸው የኢትዮጵያ ሕግ አይፈቅድም” እና ለምርጫ ተወዳዳሪነት አይመዘገቡም በሚል ሆን ተብሎ በተፈጠረ ሕዝብን አሳሳች ምክንያት ሳቢያ “በሕግ ባለሙያዋ” በብርቱካን ሚደቅሳ አማካኝነት በመገናኛ ብዙኃን ዘመቻ ማካሄድ በእነ እስክንድር ላይ ሊወሰድ የተሞከረው የመብት ቁርጠኝነትና ገፈፋን ርቀት የሚያሳይ ነው[በነገራችን ላይ ብርቱካን መጀመርያ የኢትዮጵያ ሕግ አይፈቅድም ካለች በኋላ በሚቀጠለው ቀን ደግሞ በሕግ ጥበቃ ስላሉ አይመችም በሚል ነው ብላ የሰው መብት የመጣስና ሕግ ብቻዋን የማውጣት መብት ያላት ሆና የቀረበችበት አሳፍሪ አካሄድ በጣም ሰቅጣጭ ነበር]።
በአዲስ አበባና በታዋቂው የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሕግን የተማረችና ዳኛ ሆና ያገለገለች ሰው እጅግ መሰረታዊ የሆነውን “ክፍርድ በፊት በህግ ፊት ነፃ ሆኖ የመታየትን መብት” ለመካድ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የታገለችበት ሁኔታ እስክንድር በሀገር ቤት ኤሊቶች የተካደበትና ይህንም ለማድረግ ኤሊቶች የሄዱበት አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በተለይ ይህ ጉዳይ ለእስክንድር እጅግ የተለየ መገረም እንደሚፈጥርበት ይሰማኛል። የራሱ የርሱን ስህተትንም ፊት ለፊት ያሳየዋል ብዬ አምናለሁ። ይህን ያልኩበትን ምክንያት ከታች ልግለፅ።
ባልደራስ እንደ ድንቅ አሰላሳይ ፓርቲ ለሀገር ይበጃል ብሎ ካቀረባቸው ሀሳቦቹ አንዱ በዚህ በተጠናቀቀው ዓመት መጀመርያ ላይ የመንግሥት የሥራ ዘመን ሲጠናቀቅ ወደ ተሻለና አስተማማኝ ሰላማዊ የሽግግር መንገድ ለመሄድ “የባለሙያዎች የባላደራ መንግሥት” ቢቋቋም የተሻለ ነው ሲል ያቀረበው ሀሳብ ነበር። ሀሳቡ እንደተሰማ እንደተለመደው በእስክንድር ሀሳብና ድርጊት ላይ ጨሰ፤ አቧራው ጨሰ ተባለ። ሰውየው እንደተለመደው በርጋታና በድፍረት ሀሳቡን ለማስረዳት በተለያዩ ሚዲያዎች ይቀርብ ጀመር። እኔ ከተከታተልኳቸውና በዚህ ጉዳይ ላይ እስክንድር መልስ ከሰጠባቸው ቃለመጠይቆቹ አንዱ “አንዳፍታ” በሚባል የዩቱብ መገናኛ ብዙኃን ላይ የነበረው ቆይታ ነበር። በእኔ አስተያየት ጠያቂው የብልፅግና አፍቃሪ ይመስላል።
ስለዚህም የእስክንድርን ሀሳብ ስሜታዊ በሆነ መንገድ ሲሞግት “ባልደራስ የባለሙያዎች ባላደራ የሚል ሀሳብ የሚያቀርበው፤ ኧረ ለመሆኑ ሁሉም ወገን የሚስማማባቸው የሚከበሩ ባለሙያዎች ከየት ይመጣሉ ብሎ ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀርባል [ጥያቄው ቃል በቃል የቀረበ ሳይሆን የጠያቂውን ሙሉ ሀሳቡን የያዘ መሆኑን ተረዱልኝ]። እስክንድር አቀርቅሮ የሆነ ነገር ማስታወሻ ላይ ይፅፍና ወደጠያቂው ዘወር ብሎ “አሁን የማሳይህን በድምፅ ሳይሆን ለራስህ ግንዛቤ በሆድህ አንብበውና ለምሳሌ እነዚህ ግለሰቦች ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ እንደባለሙያ የሚቀበሉዋቸውና የሚተማመኑባቸው እንደሚሆኑና እንደማይሆኑ የራስህን ግምት ውሰድ” ብሎ ካስጠነቀቀው በኋላ የፃፋቸውን ስሞች ያሳየዋል። ጋዜጠኛው ፈገግ እያለ “ልክ ነው” ሲል ተስማማ። እኒህ እስክንድር በልቦናው ለሙያቸውና ለሕዝብ ታማኝ ይሆናሉ ብሎ የፃፋቸው ስሞች ብርቱካን ሚደቅሳና ዳንኤል በቀለ እንደነበሩ በተመሳሳይ መንገድ ሌላ ሚዲያ ላይ በግልፅ ተናግሮ ነበር። እናም እስክንድር እንዲህ በግልፅ ዓይን ያወጣ ግፍና በደል ሲደርስበት ለሙያቸውና ለሕዝብ መብት ታማኝ ናቸው የሚላቸው ባለሙያዎች በሚወስዱት አቋም ምን ይል ይሆን? እላለሁ።
በባልደራስ አመራሮች ላይ ከክስ ምስረታ ሂደት ጀምሮ እስከ የፍርድ ቤት ዉሎአቸውና ኑሯቸው ላይ የሚደረገውን አሳፋሪ አካሄድ የሚገነዘብ “ኤሊት” በሙሉ “ይህም በዛ” ብሎ የእኒህን ዜጎች ፍትህ የማግኘት መብትን የመጠየቅ ኃላፊነት አለመውሰድ የሚፈጥረው ነገር ቢኖር ከሚጠዘጥዝ ኅሊና ጋር መኖርን ብቻ ነው። ቤተሰቦቻቸው ባገጠጠ ኢፍትሐዊነት በሰቀቀን እንዲኖሩ መፍቀድ ራሱን የቻለ ሌላ ግፍ ነው። ወደ አሥራ ስምንት ወራት የሚጠጋ ጊዜ ንፁሓንን በግፍ አስሮ ታሳሪዎችንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ማሰቃየት የሚፈጥረው የራስን ቁመና እያሳነሰ የታሳሪዎችን ታሪክ ማድመቅ ብቻ ነው። በዳኝነት ነፃነት ስም በፍርድ ሂደት ጣልቃ አንገባም የሚል መርህ የሚሰራው፤ ከሚጠበቀው እጅግ በጣም የወረዳ አሳፋሪ የሕግ ሂደት በሚታይበት ጊዜ መሆን የለበትም። ስለባልደራስ አመራሮች የግፍ እስር ለመጠየቅ የካቢኔ አባል ሚኒስትሮችም ኃላፊነት አለባቸው።
ፍትሕ ለባልደራስ የሕሊና እስረኞች!
የባልደራስ የሕሊና እስረኞች ቤተሰቦች ስቃይ ይብቃ!
ንፁኃንን በመበደል ማትረፍ የሚቻለው የሚጠዘጥዝ ሕሊና ብቻ ነው!! 
Filed in: Amharic