>

ዘረኝነት ስካር ናት ስንል አላበጀንም? (ደረጄ ከበደ)

ዘረኝነት ስካር ናት ስንል አላበጀንም?

ደረጄ ከበደ

*….. “ጥንብ ናት” አሉ እኚያ የሃይማኖት መምህር? ዘረኝነት እንዲያው ስምም የላት። ተዋርዳ ታዋርዳለች። “ለሃገር ፍቅር” እያነቡ የዘፈኑም ሆነ የዘመሩ አንድ በአንድ ከሚዛን ወድቀው አየን። ተከስክሰው።  ፍቅርም እንደ ቁንጅና በራስ ትፈታ ይሆን እንዴ? ትርጉሟ ተምታታብን።
ዘረኝነት እንደ አልኮል መጠጥ ሲጠጧት አትታወቅም። እየሞቀች፥ እያሟሟቀች ትማጋለች። ቆሽትና ጉርጅ ሥር ገብታ ሲትወሸቅ ግን እንዳመለጠች ኮሶ ትል ባት ላይ ተለጥፋ በአደባባይ ጀግናውን ታዋርዳለች እንጂ እንቆቆ አይሞክራትም።
“ደጁ” ‘ከአድማስ ወዲያ ያለች ምድር’ እያለ ያዜመላትን ምድር ከሰሞኑ ፅሁፎቹ ብንፈልጋት ፈፅሞ እናገኛት ይሆን? የመሰለን ይህች ምድር የአማራውም፥ የኦሮሞውም፥ የጉሙዙም፥ የትግራዋዩም ናት። ከደረጀ ሃሳብ “መች ተለየች?” የተባለችው ግን እርሷ ናት ለማለት አያሰደፍርም።
ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም ሃገር የመከላከያ ሠራዊት አላት። ይህ የሃገር መከላከያ ሠራዊት በወደር የለሽ ዘረኝነት በጦፉ ወያኔዎች “የደርግ ሠራዊት” ተብሎ በዓይናችን ፊት በደምና አጥንቱ በጠበቃት ሃገር ዳቦ ለማኝ እንዲሆን ተደርጓል። በጦሩ መደምሰስ ብቻ የኢትዮጵያን አንድነት ማጥፋት እንደማይቻላቸው ያወቁት የወያኔ መሪዎች በህዝብ መካከል የጥላቻ እንክርዳድ በስፋት ዘሩ።
ህዝቡ ግን “አወቅን” ከሚሉ እጅግ ይሻላልና መርዛቸውን እንቢ እያለ የመጨረሻ የክፋት ካርዳቸውን እንደ ያዙ እንዲያፈገፍጉ አደረገ። የህዝቡን ቁጭት አሁንም በመከላከያው ለመወጣት ብለው “የአቢይ ሠራዊት” ያሉትን የሰሜን ዕዝ በውድቅት ሌሊት አረዱት።
ይህም እንደማይበቃ ስለሚያውቁ የህዝብ ለህዝብ እልቂት እንዲከሰት “የሂሳብ ማወራረድ” ዘመቻ ታውጆ የሚችለውንም፥ አቅም አልባውንም በነቂስ ነድተው አፋርና አማራ ክልል ገቡ። ዘረኝነት የጠለቀው ሰው ከፊቱ ሲያጣ እንስሣ ጨፈጨፈ። እጅግ የበረታበትም ትምህርት ቤትና ሀኪም ቤት ቦጫጨቀ። ፈፅሞ እንደ ውጋ የጨለጣትም እንደ ማይካድራ፥ ጋሊኮማ፥ ጭና ወዘተ ዓይነት ሰውን ከሰው ደረጃ ወደ ሰይጣንነት የሚያወርድ ተግባር ፈፀመ።
ዘማሪ ዶ/ር ደረጀ ከበደ ከፅዋው ፉት ሲያደርግ አስጠንቅቀን ነበር።  “ለተገፉት መጮህ” የሚል ፅዋ ፊቱ አስቀምጦ አንድ፥ ሁለት ሲል መብቱም፥ የክርስቲያን ግዴታውም ነው ስንል አንዷን መጠጥ የሙጥኝ ካለ ግን በአደባባይ እንደምትደፋው አስጠንቅቀን ነበር። የፈራነው አልቀረ።
መርጦ መላፍ፥ ከመለኪያ ወደ ብልቃጥ፥ እያለም ጠርሙስ ማውረድ፥ ሰሞኑን ደግሞ ከባንኮኒ ንቅንቅ ሳይሉ በላይ በላዩ ማንቆርቆር ሆኖ ቀጭ። እና በእጅ አዙር የተጣባ ዘረኝነት ያስለፍልፍ ገብቷል። “በሃገር ወዳዷ” የደረጀ አንደበት የሃገር መከላከያ ሠራዊታችን “ከአብይ ሠራዊት” ጭራሽ ወርዶ የብርሃኑ ጁላ፥ የባጫ ደበሌ ሠራዊት ሆኗል። የዘረኝነት ኮሶ መጣባት ብቻ ሳይሆን ያለ ቀድዶ ጥገና በማይሞከር የሆድ ጉርጅ መወሸቁን አመላካች ነው። ነገ የደረጀ አንደበት “አማራው በኦሮሞው ላይ የሚያወርራደው ሂሳብ አለ” ብላ እንደሚታዜም ሳስብ በሁለቱ ዓይኖቼ እንባ ግጥም ይላል።
ወዳጆቼ፥ ክፉ ጊዜ ውስጥ ገብተናል። ጀግና ጦር ሜዳ ብቻ እያለቀ ያለ አይምሰላችሁ። እቤቱ ቁጭ ብሎ፥ ሳይነካ ያበደ ብዙ ሆኗል። በለሆሳስ ጀምሮ እንደ ዘማሪ ደረጀ፥ በፈረንጆቹ አባባል “እግሩን በገዛ ጥይቱ” ክፉኛ ያቆሰለ ቤቱ ይቁጠረው። አጥብቀን ካልተጠየፍን እስከምንጠፋፋ ሊያሰክረን የሚችል የሚያስነውር ጉሽ በምድሪቱ ተደፍቷል። ማንንም አይምርም። ሳይጠጣ በአንቡላው ሽታ የሰከረ እንኳ እጅግ ብዙ ነው። ጌታ አምላክ ይሰውረን!
እግዚአብሔር አምላክ ዘረኝነትን የምንጠየፍበት አቅም ይስጠን። ከተስማማችሁ አሜን በሉ።
Filed in: Amharic