>
5:16 pm - Tuesday May 24, 8383

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት (ክፍል 1) አንዳርጋቸው ጽጌ

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት (ክፍል 1)

አንዳርጋቸው ጽጌ

 
አንዳንዴ በአንዳንድ አጋጣሚዎች በመናገር ከምናመጣው ጥቅም የምናመጣው ጉዳት ያመዝናል ብለን ስናስብ ዝምታ እንመርጣለን። ግራ ቀኙን እያገላበጠን፣ ይጠቅማል አይጠቅምም እያልን፣ ስለቅርብና እሩቅ ፋይዳው እያሰላሰልን የሆዳችንን በሆዳችን ይዘን እንቀመጣለን። ሆኖም ግን የመታገስ፣ የመቻል፣ የይሉኝይታ ባህላችን እና ባህሪያችን የሚጠቅሙበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ የሚጎዱበት ወቅትም እንዳለ ማወቅ አለብን። በተለይ ባላንጣችን ምንም ለማድረግ የሞራልና የግብረገብ ለከት የሌለው፣ ሃፍረትና ይሉኝታ የማይሰማው ከሆነ ጉዳቱ የበለጠ ያመዝናል።
ወያኔዎች እንዲህ አይነት ባላንጣዎች ናቸው። ሃፍረት፣ ይሉኝይታና ጨዋነት አያውቁም። ቅንነት፣ ሃቀኛነትና ታማኝነት የሚባል ነገር አልዘራባቸውም። ዝም ስላልናቸው ወያኔዎች የሚደጋግሙት ውሸት እውነት ከሚመስልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። እነሱም የገዛ ውሸታቸውን ደጋግመው በመስማት እውነት ነው ብለው ማመን ጀመረዋል። በመሆኑም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይናቸው በጨው ታጥበው ለሚያሰራጩት ቅጥፈት መልስ መስጠት ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የወያኔ መሪዎች ከአማራ ልሂቃን ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን የሚል ነጠላ ዜማ ለቀው ደጋግመው ሲዘፍኑት እያዳመጥን ነው። ከእዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ጥቂት ጥያቄዎችን አንስቼ መልስ መስጠት እፈልጋለሁ። ለመሆኑ ወያኔዎች የአማራ ልሂቃን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ለምንድነው የአማራ ልሂቃንን ከሌሎች የኢትዮጵያ ልሂቃን ለይተው ሂሳብ ማወራረድ የፈለጉት? የአማራ ልሂቃን እውነት ወያኔዎች እንደሚሉት የሚወራረድ ሂሳብ አለባቸው ወይስ ይህ አባባል ወያኔያዊ ይሉንታ ቢስነት የወለደው ቅጥፈት ነው? እውነተኛው የሂሳብ ማወራርድ ስራ በገለልተኛ ሂሳብ አጣሪ ቢሰራ ምን ይመስላል? ማን ይሆን ያልተወራረደ ሂሳብ ያለበት? ይህ ጽሁፍ እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ ምላሽ ለመስጠት በአጭሩ የተዘጋጀ ነው።
1) የአማራ ገዥ መደብ፣ የአማራ ልሂቃን
ለአማራ ህዝብ ሆነ ለሌላውም ኢትዮጵያዊ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነጥብ አለ። ወያኔ የአማራ ገዥ መደብ ወይም ልሂቅ ሲል የአማራ ህዝብ ማለቱ ነው። ይህን በምን ታውቃለህ ለምትሉኝ? መልሴ እነሆ።
በ1970 አ.ም በትግራይ ምድር ወያኔ ነጻ መሬት በሚል ስም በሰጣቸው አካባቢዎች ለአንድ አመት ያህል ቆያቻለሁ። ብዙውን ጊዜ ያሳለፍኩት አዲ ፍታዎ በምትባል የአድዋ አውራጃ መንደር ውስጥ ነበር ። የወያኔ መሪዎችና የወያኔ ካድሬዎች ከእኔና ከሌሎች በቦታው ከነበርን ጥቂት ግለሰቦች ጋር ሲያወሩ የአማራ ገዥ መደብ የሚል ቃል ይጠቀሙ ነበር። የትግራይን ህዝብ በስፋት ሰብስበው በዲስኩርና በዘፈን ቅሰቀሳ ሲያደርጉ ግን ገዥ መደብ የሚለውን ቃል ትተው የትግራዋይ ጠላት አማራ( አምሃራይ) እንደሆነ ነበር ሲያስተምሩና ሲቀሰቅሱ ውለው የሚያድሩት። እኛም ይህን ጉዳይ አንስተን፣ “እንዴት አንድ ህዝብ የሌላ ህዝብ ጠላት አድርጋችሁ ታስተምራላቹህ?” የሚል ተቃውሞ በተደጋጋሚ አቅርበናል። የወያኔ መሪዎችም በተደጋጋሚ “የካድሬዎች ስህተት ነው” ከማለት አልፈው የትግራይ ህዝብ የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲጠላ የመቀስቀስ ስራቸውን አቁመው አያውቁም።
ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ አንዳንድ ትልልቆቹ የድርጅቱ መሪዎችና በርካታ ተራ ካድሬዎችና የሰራዊት አባላት ድርጅታቸው ይህን የአማራ ጥላቻ ትርክት ለትግራይ ህዝብ ሲያስተምር እንደነበር፣ ከዛም አልፈው ድርጊቱ ትክክል አንዳልነበር  ምስክርነታቸውን የሰጡበት ጉዳይ ነው።  በመሆኑም ወያኔዎች የአማራ ገዥ መደብ ሲሉ የአማራ ህዝብ ማለታቸው እንደነበር ሁሉ፣ ዛሬም ለሚድያ ፍጆታ የአማራ ልሂቃን ይበሉ እንጂ ሂሳብ የማወራረድ ፋላጎት ያላቸው ከመላው የአማራ ህዝብ ጋር ነው።
ወያኔዎች በ27 አመት የግፍ አገዛዝ ዘመናቸውና ከዛም ቀጥለው በመጡትና ባለፉት 3 አመታት ሂሳብ ሲያወራርዱ  የነበረው ወደፊት እንደማሳየው እዳ ከሌለበት የአማራ ሊሂቅ ጋር ብቻ ሳይሆን በመስኪኑና ደሃው የአማራ ህዝብ ላይ ነው። እንዳውም ልሂቁን በቀላሉ እዳ ማስከፈል የሚችሉበት እድል ስላልነበራቸው፣ የተወሰነውም በሎሌነት የገባላቸው ስለነበር፣ የጭካኔና የግፍ በትራቸው ሲያርፍ የነበረው በምስኪኑ ሰፊው የአማራ ህዝብ ላይ ነበር።  ስለዚህም አማራን በልሂቅና ልሂቅ ባልሆነ ክፍሎች ለመከፋፈል ወያኔዎች ሊያጃጅሉን ሲሞክሩ መልሳችን “ሞኛችሁን ፈልጉ” መሆን ያለበት።
2) ወያኔ የአማራን ህዝብ ለምን  ከሌላው ህዝብ ለይቶ ሂሳብ ማወራረድ እፈልጋለሁ ይላል?
ወያኔ በ27 አመት የግፍና የዘረፋ  የአገዛዝ ዘመኑ ሰቆቃ የፈጸመው በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ነው። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም። አፋሩ፣ ሱማሌው፣ ኦሮሞው፣ ሲዳማው፣ ወላይታው፣ በጥቅሉ ደቡቡ፣ ጋምቤላው፣ ቤንሻንጉሉ፣ አማራውና ሌላውም በወያኔ አገዛዝ በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ተመድቦ ተዋርዶ፣ ተረግጦ ተገዝቷል። እስከ አጥንቱ ተግጧል። በድህነት ተቆራምዶ፣ ሰማይ ተደፍቶበት ኖሯል። ግፍ መከራ ሲበዛበት የተሻለ ህይወት ፍለጋ በገፍ ተሰዷል። ካሰበበት ሳይደርስ በረሃና ባህር በልቶት የትም ቀርቷል። የትም የቀረው ዜጋ ቁጥሩ ስንት እንደሆነ ቤቱና ወላጆቹ ያውቁታል። ይህን አሰቃቂ ጉድ የረሱ ወያኔዎች ብቻ ናቸው። እነሱ በዳዮች ናቸውና። የበዳዮች የማስታወስ ችሎታ ደግሞ ደካማ ነውና።
ዛሬ ደግሞ ወያኔዎች አይናቸውን በጨው ታጥበው እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ሲገዙት የነበረውን ከአማራ ክልል ውጭ ያለውን ህዝብ “ከአንተ ጋር ጠብ የለንም ጠባችን ከአማራው ጋር ነው” እያሉት ነው። ይህን የሚሉት፣ አማራውን አጥፍተን አዲስ አበባ ብንደርስ ከአንተ ጋር ጠብ ስለሌለን ምንም አናደርግህም የሚል መልእክት በማስተላለፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ በአማራና በአፋር ክልል የጀመረውን ጥቃት የኔ ጥቃት አይደለም ብሎ የዳር ተመልካች እንዲሆን በማሰብ ነው።
ወያኔዎች እራሳቸውን ብቻ ብልጥ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ደደብ አድርጎ የሚያይ በሽተኛ ህሊና አላቸው። የእነሱ ብልጣብልጥ ስትራተጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ተራ በተራ እየከፋፈሉና እያስገበሩ፣ ቢቻል ከቀድሞ የዘረፋና የጭቆና ዙፋናቸው ላይ መመለስ፣ ካልሆነም ኢትዮጵያን በማፍረስ ሃገሪቱን የህዝቧ ሲኦል እንድትሆን ማድረግ ነው። ይህን ተልእኮ ለማሳካት ምስኪኑን የትግራይን ህዝብ ለስቃይና ለእልቂት እየዳረጉት ነው። ኢትዮጵያ ሲኦል ስትሆን ደግሞ ለወያኔዎች የምትመች ገነት የሆነች ትግራይ የምትባል ሃገር የመፍጠር ጅላ ጅል ህልም ይዘው ነው።
ሌላው ወያኔ አማራውን በጠላትነት የፈረጀበትን ምክንያት እንድሚከተለው አቀርበዋለሁ። የአማራ ክልል ህዝብ “ወያኔ ያነጣጠረው በኔ ላይ ብቻ ነው” በሚል አመክኖ እራሱን ከሌላው የሀገሪቱ ህዝብ ነጥሎ ትግሉን የወያኔዎችና የአማራ ህዝብ እንዲያደርገው በማሰብ ነው። እዚህ ላይም ወያኔዎች የረሱት ሌላ ሃቅ አለ። የአማራ ህዝብ የራሱን ሽንፈት የኢትዮጵያ ህዝብ ሽንፈት እንደሆነ የሚረዳ፣ ወያኔ ዳግመኛ የባርነት ስርአቱን በኦሮሞው፣ በሶማሌው፣ በደቡቡ፣ በጋምቤላው ወዘተ ላይ መጫን የሚችለው በአማራ ህዝብ አስከሬን ላይ ተረማምዶ እንደሆነ የሚያውቅ ህዝብ ነው። ሰለዚህም ነው የአማራ ህዝብ በየግንባሩ በዘመተበት ቦታ ሁሉ ከወያኔ ጋር የሚደረገውን ትግል የአማራ ህልውናን ብቻ የማስጠበቅ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ህልውና የማስጠበቅ እንደሆነ አጥብቆ የሚናገረው። ስለዚህም ነው ከወያኔ ጋር የሚደረገው ወቅታዊ ትግል “በአማራና በአፋር ክልል ይደረግ እንጂ በነዚህ ክልሎች ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በሁሉም ህዝብ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው” የሚለው። ለእዚህም ነው ሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ ወያኔ በአማራና በአፋር ህዘብ ላይ የከፈተውን ጥቃት በሁሉም የሃገሪቱ ህዝብና በኢትዮጵያ ላይ የተደረገ ጥቃት አድርጎ የተመለከተው። ቀፎ እንደተነካበት ንብ በጋራ የተቆጣው።
ሌላው ወያኔ የአማራን ህዝብ ለይቶ ለማጥቃት የወሰነበት ምክንያት የሚከተለው ነው። ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመዘርጋት የሞከረውን ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ስርአት በወያኔ የአገዛዝ ዘመን አምሮ የተቃወመው አማራ በመሆኑ ነው። ወያኔ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፍሎ፣ ህዝቡ በዘር ጥርጣሬና ፍጥጫ ውስጥ እንዲወድቅ አቅዶ የሰራ ድርጅት ነው። የእቅዱ አላማ የወያኔን የዘረፋና የጭቆና አገዛዝ ዘላለማዊ ማድረግ ይቻላል የሚል ነበር። “እርስ በርሱ የሚጠራጠር ህዝብ በጋራ በወያኔ ላይ ማመጽ አይችልም” ከሚል ስሌት የተሰራ እቅድ ነው። በእነዛ ዘመናትም ወያኔ የአማራን ህዝብ በጠላትነት መፈረጅ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ህዝቦች የአማራን ህዝብ በጠላትነት እና በጥርጣሬ እንዲያዩ ያላደረገው ጥረት አልነበረም። የአማራ ህዝብም መስፈሪያ የማይገኝለት ዋጋ እንዲከፍል ተደርጓል። በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንደ ቅጠል ረግፏል፣ መፈናቀል፣ መዘረፍና መሰደድ የአማራ ህዝብ እጣ ሆኖ ቀጥሏል።  ይህም ሆኖ በወያኔ የዘላለማዊ የስልጣን ባለቤትነት ህልሙ ፊት ደንቃራ ሆኖ ያገኘው የአማራን ህዝብ ነው።
በመጨረሻም የወያኔን የግፍ አገዛዝ እድሜ ያሳጠረው፣ ፋኖ እና ቄሮ ተናበው በወያኔ ላይ ማመጻቸው እንደሆነ ይታወቃል። “የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው” የሚለው፣ የወያኔን ከፋፋይ የዘር ግርግዳ ያፈረሰው፣ የወያኔን የግፍና የዘረፋ የአገዛዝ ዘመን ማብቃቱን ያበሰረው መፈክር ባለቤት የሆነው አማራው ስለሆነ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ አማራና ኦሮሞው በጋራ አሲረዋል። ወያኔ ሳያስበው፣ አማራው የራሱ እጩ የሆነውን አቶ ደመቀ መኮንን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩነት አውጥቶ፣ ድምጹን በሙሉ ኦሆዴድ ላቀረበው እጩ ለዶ/ር አብይ ሰጥቷል። ይህን በማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ የወያኔን እድሜ ሊያስቀጥል የሚችል የወያኔ ተላላኪ የሆነ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስልጣን እንዳይዝ አድርጓል።
ወያኔዎች ተላላኪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከላይ አስቀምጠን ሃገር እየዘረፍን ህዝብ እየረገጥን ዝንተአለም እንኖራለን  ብለው የነደፉትን ትልም መና በማስቀረት አማራ ትልቅ ሚና ነበረው። ወያኔዎች ዘላለማዊ ነው ብለው ተኩራርተው ከተቀመጥንበት ዙፋን እንዲፈነግሉ ያደረጋቸው ዋንኛ ባላንጣ “አማራ ነው” ብለው የሚያምኑ መሆናቸውን በአደባባይ ተናግረዋል። “የፈነገለን አማራ ነው” የሚል ቂም መቋጠራቸው የአደባባይ ሃቅ ነው። ይህን ቂም አጼ ዮሃንስ ሲሞቱ ለትግራይ ይገባው የነበረውን ንግስና አማሮች ቀምተው ለአጼ ሚኒሊክ አደረጉት ከሚለው የቆየ ቂም ጋር አዋህደው ወያኔዎች ለአማራ ያላቸውን ጥላቻ ማጠናከሪያ አድርገውታል።
እንግዲህ ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎችም በአደባባይ ወያኔዎች ያልነገሩን  ምክንያቶች በአንድ ላይ ተደምረው ነው የሰሞኑ የወያኔ ነጠላ ዜማ “ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን” የሚል የሆነው። በሚቀጥለው ዝግጅቴ በክፍል 2 እውነት በሃቅ ላይ የተመሰረተ የሂሳብ ማወራረድ ስራ ብንሰራ ማን በእዳ ብዛት ተቀብሮ እንደሚቀር የሚያሳይ ዝርዝር ዘገባ አቀርባለሁ። የጀመሩት ወያኔዎች ስለሆኑ ለመጨረሱ የምናፍርበት ምክንያት አይኖረም። እስከዛው በቸር እንገናኝ።
Filed in: Amharic