>

የኢትዮጵያዊነት ምስጢሩ ምን ይሆን?  (በታርቆ ክንዴ )

የኢትዮጵያዊነት ምስጢሩ ምን ይሆን? 
በታርቆ ክንዴ 

ደባርቅ፡ መስከረም 05/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው የሚኖሩት እንጂ የማያዩት፤ ኢትዮጵያዊነት ውቅያኖስ ነው ጠልቀው የማይጨርሱት፤
 ኢትዮጵያዊነት ተራራ ነው ገፍተው የማይጥሉት፤ ኢትዮጵያዊነት ነብስ ነው ከራስ ጋር የማይለዩት፤ ኢትዮጵያዊነት መሠረት ነው ፀንተው የሚቆሙበት፤ ኢትዮጵያዊነት ምሰሶ ነው የሚደገፉት፤ ኢትዮጵያዊነት ጣሪያ ነው የሚለብሱት፣ ኢትዮጵያዊነት ጌጥ ነው የሚያጌጡበት፤ ኢትዮጵያዊነት ጋሻ ነው የሚመክቱበት፤ ኢትዮጵያዊነት መከበሪያ ነው የሚከብሩበት፤ ኢትዮጵያዊነት ምርኩዝ ነው የሚደገፉበት፤ ኢትዮጵያዊነት መጠለያ ነው የሚጠለሉበት፤ ኢትዮጵያዊነት ፍስሃ ነው የሚደሰቱበት፤ ኢትዮጵያዊነት መለያ ነው የሚታወቁበት፤ ኢትዮጵያዊነት ዋስትና ነው የሚሻገሩበት። ኢትዮጵያዊነት ቀዳሚነት፣ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት፣ ኢትዮጵያዊነት አፍቃሪነት፣ ኢትዮጵያዊነት ብልህነት፣ ኢትዮጵያዊነት ታታሪነት፣ ኢትዮጵያዊነት መከበሪያ ነው።
ኢትዮጵያን ያሉ ሁሉ በታሪክ ከብረዋል፤ ስማቸውን ከሰማይ በላይ አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያን ያሉ ሁሉ ፈራሽ ገላ ሰጥተው የማትፈርስ ሀገር አቆይተዋል። ኢትዮጵያን ያሉ ሁሉ በአሸናፊነት ዘምረዋል። ኢትዮጵያን ያሉ ሁሉ የበላይ ሆነዋል። ኢትዮጵያን ያሉ የቀደመች፣ የተከበረች፣ የተፈራችና ያልተሸነፈች ሀገር አቆይተዋል። ሀገርን በፅኑ መሠረት ላይ አቁመዋል። ኢትዮጵያዊነት ምስጢሩ ብዙ ነው። ኢትዮጵያዊነት እናዳፍንህ ቢሉት የማይዳፈን፣ እናፍንህ ቢሉት የማይታፈን፣ ልርሳው ቢሉት የማይረሳ ረቂቅ ነው። ለዚያም ነው ጠላቶች ሊያጠፉት ባሰቡ ቁጥር የሚጎላባቸው፤ ሊጥሉት በከጀሉ ቁጥር የሚጥላቸው።
ኢትዮጵያዊነት ካኖራቸው፣ ኢትዮጵያዊነት ከጠራቸው፣ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ከሚስማማቸው ሀገር ወዳድ ሰው ጋር ተገናኝቻለሁ። ምክትል አስር አለቃ ኃይሌ ብርሃኔ ይባላሉ። የተወለዱት በባሌ ክፍለ ሀገር ነው። በኢትዮጵያ ለዛ፣ በኢትዮጵያዊነት መአዛ ነው ያደጉት፤ ስለ ኢትዮጵያ ክብር እየተነገራቸው፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት እየተዘመረላቸው። እድሜያቸው ለቁም ነገር ሲደርስ የኢትዮጵያን ክብር፣ የኢትዮጵያዊነትን ምስጢር ቀርበው ያዩት ዘንድ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ተቀላቀሉ። ጊዜውም በ1970 ነበር። የሚወዷትን ሀገራቸውን በሚወደደው ሠራዊት ውስጥ ሆነው እናት ሀገራቸውን ማገልገል ጀመሩ። ለኢትዮጵያ በዱር አደሩ፤ በበረሃ ኖሩ፤ በምሽግ ከርመዋል፤ ከጠላት ጋር ተፋልመዋል። በታጠቅ አራት የማሰልጠኛ ተቋም ውስጥም በአሰልጣኝነት አገልግለዋል።
ምክትል አስር አለቃ ኃይሌ የመንግሥት ሥርዓት ሲቀየር ለሀገር እንዳልዘመቱ፣ ለሕዝብ እንዳልኖሩ በሽብርተኛው ትህነግ የግፍ አገዛዝ የደርግ ወታደሮች በሚል ስም ክብራቸውን ተነጠቁ። ሽብርተኛው ትህነግ በሥልጣን ዘመኑ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና አይደፈሬነት ታላቅ ጀብዱ የፈፀሙ ጀግኖችን አሰቃያቸው። ጨቋኝ፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ የሚል ስም ሰጥቶ በጨለማ ዘመን እንዲኖሩ ፈረደባቸው። ፈሪ ጀግና አይወድምና ለጀግኖች ክብር ነሳቸው።
ሌላው ቀርቶ በካራማራ የተዋደቁትን፣ ሕይወት ሰጥተው፣ ጠላትን ድባቅ መትተው በኢትዮጵያ ሠማይ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን ሠንደቅ በኩራት ያውለበለቡትን ጀግኖች እንደ አለቀ እቃ ጣላቸው። እንደ ዋዛ ገፋቸው። ምክትል አስር አለቃ ኃይሌም የደረሳቸው እጣ ይህ ነበር። ከሠራዊቱ ተበትነው፣ በተወለዱበት ቀዬ ውስጥ አዲስ ሕይወትን ጀመሩ። ትዳር ተያዘ፤ ልጆችም መጡ፤ ታዲያ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችን በትኖ፣ ታላቋን ሀገር ሸንሽኖ፣ ሀገር አሳንሶ ብሔርን አግንኖ ኢትዮጵያን እመራለሁ ያለው ቡድን ልባቸውን ያደማው ጀመር።
የአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ክብር፣ የኢትዮጵያዊነት ምስጢር፣ የኢትዮጵያውያንን ትብብር እና ትሥሥር በወንበዴው ቡድን ሲዳከም አናደዳቸው፤ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ኃያልነት፣ መልካምነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ሲሸረሸር ምክትል አስር አለቃ ሀዘናቸው ከፍ እያለ መጣ።
ኢትዮጵያን አብዝቶ የሚወዳት ፈጣሪ ከፋፋዩን ቡድን አንድ ቀን እንደሚጥለው ፅኑ እምነት ሰንቀው በተስፋ ተቀመጡ። ፈጣሪም አላሳፈራቸውም፣ ምኞታቸውን ተቀበለ፣ ጊዜው ደረሰ። ወንበዴውን ቡድን ከዙፋን ላይ ነቀለ። ከክብር ያወረዳቸው ከሚወዱት የውትድርና ቤት ያስወጣቸው ሽብርተኛው ትህነግ ሲፈራርስ ለማየት በቁ። ምን ይሄ ብቻ ትህነግን ከሚያፈርሱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል አንደኛው እርሳቸው ይሆኑ ዘንድ እድል ሰጣቸው።
በሀገራዊ ጥሪው ከተወለዱበት ባሌ ተነስተው በማይጠብሪ ግንባር ነው ያገኘናቸው። ከሚወዱት ሠራዊት ጋር፣ ለሚወዷት ሀገራቸው የሚጠሉትን ሽብርተኛ እና ወራሪ ትህነግ እየተዋጉ ይገኛሉ። ደስታ ከፊታቸው የማይለዬው ጨዋታቸው ጣፋጭ የሆኑት ምክትል አስር አለቃ ኃይሌ ዳግም ለትግል ስለገቡበት ጉዳይ ጠየቅናቸው “ወያኔ ሲገባ ከሠራዊቱ ተበትኜ ዝም ብዬ ነበር የምኖረው፤ አሁን ሀገሬ ታማለች ብዬ ለሀገር ጥሪ መጥቻለሁ፤ ሁለት ልጆቼም መከላከያዎች ናቸው” ነው ያሉን። ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ መልካምነት፣ አይደፈሬነትና አርቆ አሳቢነት ከልባቸው የሞላ፣ ውስጣቸውን ያረሰረሰ፣ በመንፈሳቸው የነገሰ ነው።
ኢትጵያዊነት ሙሉነት፣ ኢትዮጵያዊነት ኃያልነት፣ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት የሚለው ይገዛቸዋል። “ወጣቱ መከላከያ ሠራዊቱን መቀላቀል አለበት፤ ከመከላከያ በላይ ለሀገር ምንም ነገር የለምና” የእሳቸው ፅኑ አመለካከት ነው። የመከላከያ ሠራዊትን መለዮ ማድረግ ለኢትዮጵያ፣ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን ኖሮ መሞት ለእርሳቸው ክብር ነው። “እኔ ልጆቼን ወደ ጦር ሜዳ ልኬ ቤት ውስጥ አልቀመጥም ብዬ ነው የመጣሁት። መከላከያና የኢትዮጵያን ባንዲራ ሳይ እውነት ነው የምልህ እንባዬ ይመጣል። አለቅሳለሁ። መለዮውን መልበስ ትልቅነት ነው። ክብር ያለው ነገር ነውና ሕዝባችን በተለይም ወጣቱ ራሱን በሱስ ከሚደብቅና የፌስቡክ አርበኛ ከሚሆን የሀገሩን ዳር ድንበር ቢያስጠብቅ ነው የሚሻለው። ሀገር ከሌለ በባዕድ ሀገር ውስጥ መንከራተት ይመጣል። ሀገር ከኖረች ሁሉም ነገር ይኖራል” ነው ያሉን።
ሽብርተኛው ትህነግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የተከፉት ያህል፣ ሲሞት ደስ ብሏቸዋል። “ወያኔ በሴራ ነው የበተነን። እኔ የወያኔ ሤራ ከሽፎ ሲፈርስ በማየቴ እድለኛ ነኝ። እኛን ስለሚፈራንና ኢትዮጵያዊነት ውስጣችን እንዳለ ስለተገነዘበ አፈረሰን። የእርሱን መቃብር ማየት እጅግ በጣም ነው ያስደሰተኝ። ለዚህ በመብቃቴም እድለኛ ነኝ” ብለዋል። ስንቶችን ኢትዮጵያዊነት የሚለው ስም ብቻ ልባቸውን በደስታ እያቀለጣቸው፣ እያኮራቸው፣ ከፍ እያደረጋቸው፣ በአንድነት እየሰበሰባቸው ሳለ ሽብርተኛው ትህነግ ግፍ እንደፈፀመባቸው እርሳቸው ምስክር ናቸው።
ምክትል አስር አለቃው እንዳሉት የኢትዮጵያ የበላይነት መገንባት አለበት፤ ኢትዮጵያውያን አንድነት ፈጥረው የሚለያይን ነገር መታገል አለባቸው፤ ድንቅ በረከት የተሰጣትን ሀገር ተጠቅመን ብርቅ ሀገር ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ አለብን ብለውናል። ለኢትዮጵያ ሲሉ መሞት በረከት እንደሆነ ሚያምኑ ብዙ ጀግኖች አሉ።
ለኢትዮጵያ ራሳቸውን የሰጡና የሚሰጡ ሞልተዋል፤ ኢትዮጵያዊነት ክብር ነውና፤ አንተም ተነስ ለኢትዮጵያ ዝመት፤ ለነፃነት ክተት፤ ረሃቡ፣ ጥሙ፣ እርዛቱ ሁሉ የመጡት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በሚጠሉት ምክንያት ነው። የችግሩን ስር ሳትነቅል ቅጠሉን ብቻ እያረገፍክ መኖርን አትመኝ። የረገፈው ቅጠል ጊዜ አይቶ ይለመልማል፣ ይህ እንዳይሆን ሥሩን ነቅለህ ለመጣል ዛሬውኑ ተነስ። ወገኖችህ ለዘላለም ከመከራ የሚወጡት ለመከራ የዳረጋቸው ለዘላለም ሲያልፍ ብቻ ነው። ለዘላለም እንዲያልፍላቸው ከፈለክ የኢትዮጵያን ጠላቶች ለዘላለም አጥፋቸው።
ያን ጊዜ ወገኖችህም አንተም የመጨረሻውን ሳቅ ትስቃላችሁ። የመከራውን ካባ ከላያችሁ ላይ አውልቃችሁ ትጥላላችሁ። ይህ ይመጣ ዘንድ በምትችለው ሁሉ ለመታገል ተነስ።
Filed in: Amharic