>
5:16 pm - Monday May 24, 7030

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የዘንድሮውን የጀርመን አፍሪካ ሽልማት አሸነፉ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የዘንድሮውን የጀርመን አፍሪካ ሽልማት አሸነፉ

.


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የዘንድሮው የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽ (DAS) ሽልማት አሸናፊ ሆኑ፡፡
ሽልማቱ ስም ካላቸው የጀርመን ሽልማቶች ቀዳሚው ሲሆን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዶ/ር ዳንኤልን የሽልማቱ አሸናፊ አድርጎ መምረጡን ፋውንዴሽኑ አስታውቋል፡፡
ዶ/ር ዳንኤል ለሽልማቱ ታጭተው ከነበሩ 30 ሰዎች መካከል ቀዳሚ ሆነው ነው ከፍተኛውን ሽልማት ያገኙት፡፡
24 አባላት ያሉት ገለልተኛው የዳኞች ጉባዔም ዶ/ር ዳንኤልን አሸናፊ አድርጎ በሙሉ ድምጽ መርጧል፡፡
ኮሚሽነር ዳንኤል በመጪው ህዳር በሚዘጋጅ ይፋዊ ስነ ስርዓት ሽልማቱን የሚቀበሉ ይሆናል፡፡
ሶማሊያዊቷ የሰላም አቀንቃኝ ኢልዋድ ኢልማን የባለፈው ዓመት የሽልማቱ አሸናፊ ነበረች፡፡
ዶ/ር ዳንኤል ሽልማቱን ያገኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
ዳንኤል ገና የ23 ዓመት ወጣት ሳሉ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ጥብቅና መቆም መጀመራቸውን ያስታወቀው ፋውንዴሽኑ ሴት የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያዎች ማህበርን ጨምሮ ከበርካታ ሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ጋር መስራታቸውን ይገልጻል፡፡
የሲቪል ማህበረሰቡን በመወከል የ1997ቱን ምርጫ ለመታዘብ ችለው እንደነበርም ነው ፋውንዴሽን ሽልማቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ያስቀመጠው፡፡
ሆኖም ዶ/ር ዳንኤል በወቅቱ በምርጫው የተስተዋሉ ግድፈቶችን አስመለክተው ያደርጓቸው በነበሩ ገለጻዎች ሳቢያ ለአራት ዓመታት እስር ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከዚያም ወዲህ የ‘ሂውማን ራይትስ ወች’ እና የ‘አምነስቲ ኢንተርናሽናል’ ከፍተኛ አመራር በመሆን አገልግለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተሾሙበት ከ2011 ዓ/ም ጀምሮም አዋጆች እንዲሻሻሉ እና ተቋማዊ ለውጦች እንዲመጡ ከሌሎች የኮሚሽኑ ባልደረቦች ጋር በመሆን ብዙ ሰርተዋል፡
Filed in: Amharic