>

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት...!!! (አንዳርጋቸው ጽጌ)

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት…!!!

አንዳርጋቸው ጽጌ
(ክፍል 2)

በሃቅ ላይ የቆመ ሂሳብ ሲወራርድ፣ በታሪክ ማእቀፍ፤
ትንሽ ሃፍረት የሌላቸው ወያኔዎች ምንም ሳይሳቀቁ ከአማራው ጋር የሚያወራርዱትን ሂሳብ ማስላት የሚጀምሩት ከመቶዎች አመታት በፊት የተከሰቱ ታሪኮችን እያጣቀሱ ነው። ስለሆነም እኛም ሳንወድ በግድ ወደ ኋላ ተመልሰን ሂሳቡን በመስራት እስከአለንበት ወቅት መዝገቡን ወቅታዊ ማድረግ ይኖርብናል።
ወያኔዎች አንዱ አማራን የሚከሱት “የኛን ታሪክ ወስዶ የራሱ ታሪክ አደረገው” የሚል ነው። ይህን ክስ ሁለት ቦታ ከፍለው ያቀርቡታል። የመጀመሪያው፣ “የአክሱም ስልጣኔ እና ታሪክ የእኛ ታሪክ ሆኖ ሳለ አማሮች የኛ ታሪክ ነው ብለው ወሰዱት” የሚል ነው። ሌላው ክስ በዋንኛነት ከአጼ ዮሃንስ ንግስና በኋላ በመጣው የታሪክ ዘመን ውስጥ ከተከሰቱ ኩነቶች ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡት ክስ ነው። ሁለቱንም ክሶች “አማሮች ታሪካችንን ወስደው የኛ ነው ስላሉ፣ ታሪካችንን ለማስመለስ ትግራዋይ እንታገል” በሚል ባህላዊ ዘፈን ህዝቡን ሲቀሰቅሱ በቦታው ነበርን። የ1970ው “ታሪህና ወሲዶም፣ ነአ ነአ ኢሎም ንቃለስ ትግራዋይ ንመልስ ቅያና” (ታሪካችንን ወስደው የኛ የኛ ብለው እንታገል ትግራዋይ ታሪካችንን ለማስመለስ) የሚሉ ስንኞች የነበሩትን፣ ከላይ የጠቀስኳቸውን ነጥቦችና “አድዋ፣ ተንቤን፣ ሽሬ እንዳባጉና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ከጣሊያን ጋር የተደረጉ ተጋድሎዎችን አንዳቸውም ሳይቀሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ያልተሳተፉበት፣ አማሮች ከትግሬዎች ቀመተወ የራሳቸው ድል አደረጉት የሚል ክስ የሚያቀርብበትን ዘፈን ዛሬም እናስታውሰዋለን። እነሱ ግን ካሴቱ ሲጠፋ የሚያስታውሰው ሰው የጠፋ መስሏቸው ነበር።  ይህን ካልን እነዚህን ክሶች ተራ በተራ እንያቸው። በቅድሚያ ግን ለሂሳብ ማወራረድ እንዲመች ስል የተወሳሰበውን የኢትዮጵያን ታሪክን እንዳው በደምሳሳው እያቀረብኩት እንደሆነ ይታወቅልኝ።
በማስረጃ የተደገፈው የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚነግረን በስድስተኛው ምእተ አመት መጨረሻ የአክሱም ስርወ መንግስት ስልጣን መዳከም ሲጀመር፣ ስልጣኑን ከአክሱሞች የቀሟቸው፣ እራሳቸው አክሱማውያን እየወረሩና እያስገበሩ፣ እያገቡና እየተዋለዱ የተዋሃዱአቸው አገዎች  እንጂ አማሮች አልነበሩም። (እግረ መንገዴን የአክሱም ስልጣኔ የትግሬዎች ስልጣኔ ለመሆኑ እስካሁን መረጃ የለም። ቋንቋቸው ግእዝ የነበረ ነገስታት ስልጣኔ ነው።)  የዛጉዬ ስርወ መንግስት የአክሱማውያኑን ስርወ መንግስት ተክቶ እስከ 13ኛው ምእተ አመት መጨረሻ የደረሰ ቢሆንም በመጨረሻ ራሱን የአክሱም ሰርወ መንግስትና ስልጣኔ ወራሽ ነኝ በሚልና ራሱን የአክሱም ስርወ መንግስት አስቀጣይ አድርጎ የሚያይ፣ ዩኩኖ አምላክ የተባለ የሸዋ ንጉስ የዛጉዬን ንጉስ በጦርነት አሸንፎ ነገሰ። በወቅቱ ይህን የንጉሱን ድርጊት ርእዮተአለማዊ ሽፋን በመስጠት በዋንኛነት የተባበሩት የትግራይ የቤተክህነት ልሂቃን እንደሆኑ ይታወቃል። ከዩኩኖ አምላክ ዘመን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ንጉስ ሃይለስላሴ ድረስ የመጡ ነገስታት በሙሉ ራሳቸውን የአክሱም ስልጣኔ እና የአክሱም ስርወ መንግስት ወራሾችና የአክሱምን ገናናነትና ስልጣኔ የራሳቸው የክብርና የኩራት ምንጭ አድርገው ያለፉ ናቸው።
ከዚህ የታሪክ ሃቅ ጋር ተያይዞ ወያኔዎች የሚያቀርቡት ጉደኛ ክስ “አማሮች የአክሱምን ስልጣኔና ታሪክ የራሳቸው አደረጉት” የሚል ነው። ልብ በሉ አማሮች “አራከሱት” አይሉም። “የዚህ ስልጣኔ ባለቤቶች አማሮች ብቻ ናቸው የትግራይ ህዝብ የለበትም ይላሉ” አይልም ክሱ። አማሮች ላይ የቀረበው ክስ “የአክሱምን ስልጣኔ ኢትዮጵያ ለሚባል ሃገር፣ የኩራትና የስልጣኔ ምንጭ አደረጉት” የሚል ነው። “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው” የሚለው ዝነኛውና በድንቁርና የተሞላው የመለስ ዜናዊ አባባል መነሻው ይህ የተንሸዋረረ የታሪክ እይታ ነው። በወቅቱ ለዚህ አባባል “የአንድ ሃገር ህዝብ ታሪክ፣ ያ ሃገር እንደሃገር እስከቀጠለ በዛ ሃገር የሚኖሩ ዜጎችና ህዝቦች ሁሉ ታሪክ ነው።” በማለት የሰጠሁት ምላሽ ወያኔዎች በአማሮች ላይ ለሚያነሱትም ክስ በምላሽነት የሚሰራ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል።
ይህ  እንደተጠበቀ ሆኖ ወያኔዎች የአክሱም ስልጣኔን በተመለከተ በአማራው ላይ የሚያቀርቡት ክስ እጅግ የሚያስገርም ሆኖ እናገኘዋለን። ሁላችንም እንደምናውቀው በአለም ላይ ከታሪክ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጭቅጭቅ፣ በኛ ሃገርም ሳይቀር በተለያዩ አክራሪ ብሄረተኛ የፖለቲካ ልሂቃን የሚነሳ ክስ “ታሪካችንን ተንኳሰሰ፣ እንዲጠፋ ተደረገ፣ በቦታው የእኛ ያልሆነውን ታሪክ ትጫነብን” የሚል ክስ እንጂ ታሪካችንን ወስደው ኮራበት። የራሳቸው የህልውናው መሰረት፣ የኩራታቸውና የክብራቸው ምንጭ አደረጉት” የሚል አይደለም።
እንኳን የአማራ ህዝብ፣ የአለም ህዝብ ጭምር የአክሱምን ስልጣኔ የራሱ አድርጎ ቢኮራበት በወያኔዎች ሊወደድ ሊፈቀር የሚገባው ተግባር እንጂ ሊጠላ የሚገባው ነገር አልነበረም። በጥላቻ ላበደው ወያኔ ግን በአማራው ላይ ጥላቻ ለመፍጠር መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል።
ቀጥሎ ደግሞ ወያኔዎች በአማራው ላይ ክስ ወደሚያቀርቡበት የቅርብ ዘመን ታሪክ እንምጣ።
ዘመነ መሳፍንት እንዲያበቃ እና ኢትዮጵያ በአንድ ማእከላዊ መንግስት ስር እንድትተዳደር መሳፍንቶችን በማስገበር እርምጃ የወሰዱትን ንጉሰ ነገስት ቴዎድሮስን ከተኩት የአጼ ዮሃንስ ዘመነ መንግስት እንነሳ። ጉልበት ያለው፣ ተቀናቃኞቹን አሸንፎ ንጉስ መሆን በሚቻልበት ሃገር አጼ ዮሃንስም እንደ አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን በጉልበት ንጉሰ ነገስት እንዳደረጉ ይታወቃል። የአጼ ዮሃንስ ጉልበት ግን የኢትዮጵያ መሳፍንት እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት ፍልሚያ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የመጀመሪያው ሃገራቸውን በውጭ ወራሪዎች እንድትወረር ከእንግሊዞች ጋር ተመሳጥረው በአጼ ቴዎድሮስ አስከሬን ልዋጭ ከእንግሊዞች ባገኙት ዘመናዊ መሳሪያና እንግሊዞች ባሰለጠኗቸው ተዋጊዎች ከመጣ ጉልበት የተገኘ ንግስና እንደሆነ የታወቀ ነው።
አጼ ዮሃንስም እንደ ቴዎድሮስ “የአክሱም ነገስታት ዝርያ ነኝ። የስርወ መንግስቱ ወራሽ ነኝ”  አሉ። እንደ ምኒሊክ አይነቶችም በወቅቱ ንጉሰ ነገስት የመሆን ህልም የነበራቸው የሸዋ ንጉስ የአጼውን ጉልበት አይተው ገበሩላቸው።  ንጉስ ምኒሊክ ድንጋይ ተሸከመው ለአጼ ዮሃንስ በመገበራቸው ያኮረፈ፣ ቂም የያዘ አማራ አለ? የለም።
አጼ ዮሃንስ ለእንግሊዞች አድረው በቴዎድሮስ ላይ አሲረው መሳሪያ ቢቀበሉም መልሰው በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስትነታቸው ከቱርኮች፣ ከግብጾች፣ ከጣሊያኖች ጋር ተዋግተው በማሸነፋቸው የአማራ ህዝብ እንደራሱ ጀግና አድርጎ ከማየት ውጭ ያደረገው ነገር የለም። አጼ ዮሃንስ “የነገስታቱ ከተማ ጎንደር ተደፈረ ቤተክርስቲያን በደረቡሾች ነደደ” ተብሎ ሲነገራቸው ወደ ምጽዋ ጀመረውት የነበረውን ጉዟቸውን ገትተውና ገስግሰው መተማ ላይ ደርቡሾችን ገጥመው በመሰዋታቸው ፤ንጉሱ በአማራ ህዝብ ላይ የወሰዷቸው በጭካኔ የተሞሉ እርምጃዎች እንዳሉ ሆነው፤ የአማራ ህዝብ  ህልፈታቸውን በቁጭት ሲያየው የኖረ መሆኑን ማንም የማይክደው ሃቅ ነው።
“የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ
አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዩሃንስ”
በማለት የተቀኘላቸው አማራው አልነበረም?
ስልጣን ከዮሃንስ ወደ ምኒሊክ የሄደው፤ ከቴዎድሮስ በኋላ ስልጣን ወደ አጼ ዮሃንስ በሄደበት ተመሳሳይ ሂደት ነው። ቴዎድሮስ በእንግሊዞች ተገደሉ። ዮሃንስም በመሃዲስቶች ተገደሉ። ዮሃንስ በቴዎድሮስ ቦታ ራሳቸውን መተካት የቻሉት በጉልበት ባላንጣዎቻቸውን አስገብረው ነበር። ጉልበቱ በሃገር ክህደት የተገኘ ቢሆንም!
አጼ ምኒሊክም፣ አጼ ዮሃንስን መተካት የቻሉት ጉልበታቸው ከባላንጣዎቻቸው በላይ በመሆኑና ባላንጣዎቻቸውም እንዲገብሩላቸው በማድረጋቸው ነው። ምኒሊክ ድንጋይ ተሸክመው ዮሃንስ እግር ስር እንደወደቁ  ሁሉ በኋላ ደግሞ የምኒሊክ እጣ የገጠማቸው የትግራዩ ራስ መንገሻ ዮሃንስ ድንጋይ ተሸክመው ምኒሊክ እግር ስር ወድቀው የምኒሊክን ንጉሰ ነገስትነት ተቀብለዋል። ይህ አሰራር በነገስታቱ ዘመን ይሰራበት የነበረ ነው። ለሃይለኛ መንበርከክ ለንጉስ ምኒሊክ ሲሆን የሚሰራበት ለራስ መንገሻ ሲሆን  የማይሰራበት ምክንያት አይኖርም።
አጼ ዮሃንስ ስልጣን ከአክሱማውያን እጅ ከወጣ ከሺ አመት በኋላ የመጡ ብቸኛው ከትግራይ የተነሱ የኢትዮጵያ ንጉስ ናቸው። የነገሱትም ለ17 ብቻ አመታት ነው። ከአጼ ዮሃንስ በፊትም ሆነ በኋላ ንጉሰ ነገስትነት ከሸዋው ንጉስ ዩኩኖ አምላክና ከአክሱም ነገስታት ጋር “የዘር ግንድ አለን” በሚሉ ነገስታት ተይዞ የቆየ ነው።
እነዚህ ነገስታት የአንድ ዘር የደም ጥራት ያልነበራቸው ከተለያዩ ዘሮች ጋብቻና መቀላቀል የተገኙ ናቸው። ከአጼ ዮሃንስ ሞት በኋላ የዮሃንስ ልጅ መንገስ ሲገባው፣ አማሮች ስልጣናችንን ያለአግባብ ቀምተው ምኒሊክን አነገሱ ለሚለው የወያኔ ክስ ዮሃንስ የማን ልጅ ሆኖ ነው የነገሰው? በመወለድ ከሆነ የቀድሞ ንጉሰነገስት ቴዎድሮስ ሲሞቱ ልጃቸው ወይም የቅርብ ዘመዳቸው መንገስ አልነበረበትም ወይ ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል።
በተለይ የአጼ ቴዎድሮስ ህጻን ልጅ፣ ልኡል አለማየሁ በእንግሊዞች ተይዞ፣ የሺ አመታት እድሜ ከነበራቸው የኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶች ጋር በምርኮ ስም ወደ ሃገረ እንግሊዝ ሲወሰድ፣ አጼ ዮሃንስ እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ እንዴት ተደርጎ አላሉም። እንዲያውም መንገድ መሪና አስተባባሪ በመሆን የተባበሩት አጼ ዮሃንስ አልነበሩም ወይ?  ይህን አስነዋሪ ድርጊት ንጉሱ የፈጸሙት ለስልጣን ብለው አልነበረም ወይ?  ለነዚህ ጥያቄዎች  ወያኔዎች ምን መልስ ይኖራቸው ይሆን?
አጼ ቴዎድሮስም ቢሆኑ ባላንጣቸውን በሃይል አስገብረው ነገሱ እንጂ ንጉሰነገስት ከነበሩ አባታቸው ስልጣን በውርስ አላገኙም። በመሆኑም ይህን ጉዳይ ወስደው ወያኔዎች በአማራ ላይ ክስ ማቅረብ አይችሉም። ሆኖም ግን አንዱ ወያኔ በአማራ ላይ የጥላቻ ዘመቻ የሚያካሂደው “አማራው ስልጣን ያለአግባብ ከትግራይ እንድትወጣ አድርጓል” የሚል ነው። የንግስና ስልጣን በጉልበት በሚወሰንበት ዘመን የተከናወኑ ኩነቶችን አንስቶ በህዝብ ላይ የጥላቻ መቀሰቀሻ ማድረግ አሳፋሪ የሚሆነውም ለዚህ ነው።
ሌላው የታሪክ ሃቅ ፍጹማዊ የሆነ ወያኔያዊ ይሉኝታ ቢስነት የተጠናወተው ነው። አድዋ ላይ በጣሊያኖች ላይ የተገኘው ድል አጼ ምኒሊክ  ከመላው ኢትዮጵያ ባሰባሰቡት ተዋጊ ሰራዊት የተገኘ ድል ነው። ሃቁ ራስ መንገሻ ዮሃንስ አድዋ ላይ በራሳቸው አቅም አነስተኛ ቁጥር የነበረውን የጣሊያን ሰራዊት መመከት አቅቷቸው፣ ጣሊያን አድዋን አልፎ መቀሌን ተቆጣጥሮ የትግራዩ ገዥ መቀመጫ አጥተው በሚንከራተቱበት ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ ተሰባስቦ የመጣው ጦር የትግራይን መሳፍንት፣ መኳንንትና ህዝብ ከመጨረሻው የነጭ ተገዥነትና ውርደት ያዳነ መሆኑ ነው። ወያኔዎች ይህን የአድዋን የጦርነት ሃቅ ክደው ድሉ “የኛ ብቻ ነው” እያሉን ነው። ይህን ለትግራይ ህዝብ ሲያስተምሩ በጆሯችን ሰምተናል። ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ዘፈን ስንኞች ይህንኑ ነበር የሚሉት።
በመጨረሻም ራስ መንገሻ በጣልያን አማካኝነት ለደረሰባቸው ውርደት ከጣሊያን ጋር ተሰልፈው የነበሩ ኤርትራውያን ናቸው በማለት፣ አጼ ምኒሊክ ለነጩ ወራሪ ለጣሊያን ሳይቀር ያሳዩትን ከአሸናፊነት የመጣ ሰብአዊነት ኤርትራውያኑ እንዲነፈጋቸው አድርገዋል። ራስ መንገሻ የምርኮኞቹ ኤርትራውያን ወታደሮችን አንድ እጅና እግር ካልተቆረጠ ሞቼ እገኛለሁ በማለት ምኒሊክ የጭካኔ ውሳኔ እንዲወስኑና የኢትዮጵያም የጀግንነትና የድል ታሪክ በራስ መንገሻ ግፊት ጥቁር ጥላሸት እንዲቀባ ሆኗል። እውን ወያኔ እንደሚለው “ አድዋን አማሮች ቀምተው “የእኛ እኛ” ብለው የሰረቁት ታሪክ ነው? ወይስ ያለ ምኒሊክ ሰራዊት የትግራይ እጣ ምን ይሆን እንደነበር ወያኔዎች አጥተውት?” በዳግማዊ ምኒሊክ የተመራው ከመላው ኢትዮጵያ የዘመተው ተዋጊ ድል ባያደርግ ኖሮ የትግራይ ህዝብ እጣ የጣሊያን ባሪያ ከመሆን አያመልጥም ነበር። ሃቁ ይህ እና ይህ ብቻ ነው።
በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ (ማይጨው ጦርነት) ወቅትም የሆነውን እንመልከት። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ያስታጠቃቸውን በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ይዞ ደጅአዝማች ሃይለስላሴ ጉግሳ ከጣሊያን ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ለመውጋት ገና ጦርነቱ ሳይጀመር ወደ ኤርትራ አልሸሸም እንዴ? የራስ ካሳ ጦር ተንቤን አቢ አዲ ላይ ሲዋጋ፣ የራስ እምሩ ጦር ሽሬ እንዳባጉና ላይ ሲዋጋ፣ ወጣቱ አብቹና ወንድሞቹ ከሰላሌ ዘምተው፣ አብቹ ወንድሞቹን ትግራይ ምድር ላይ ሲገብር፣ እነደጃች መሸሻ የከንባታውን ጦር እየመሩ በጀግንነት ተዋግተው በትግራይ ምድር ሲሰው፣ ትግራይ ውስጥ የወያኔ ቅድመ አያቶችና አያቶች በዛን ወቅት ምን ይሰሩ ነበር?
ጣሊያን ያሰለፋቸው ኤርትራውያን ጣሊያን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ በመቃወም በተለይ በደቡብ ግንባር መሳሪያቸውን እየያዙ ጣሊያንን እየከዱ ከኢትዮጵያዊያን አርበኞች ጎን ተሰልፈው ጣሊያንን ሲዋጉ የወያኔ አያቶች በሰሜን ግንባር ከክህደት በስተቀር ምን ፈየዱ? በሰሜኑ ግንባር የወያኔ ቀደምቶች ከጣሊያን በከፋ መልኩ ኢትዮጵያዊ ወገናቸውን እየገደሉ መሳሪያውን፣ ስንቁን አልገፈፉም?
ለመሆኑ በጣሊያን ወረራ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ የተካሄደው የአምስት አመት የአርበኝነት ታሪክ ሲወሳ፣ በትግራይ ምድር የበቀሉ የሁለት አርበኞች ስም መጥራት ይቻል ይሆን?  ይህን  የትግራይ መሳፍንቶች የክህደት ታሪክ አማራው አራገበው? ይህን የክህደት ታሪክ እየቆሰቆሰ፣ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ወንድሞቹ ላይ ቂም እንዲቋጥር ተጠቀመበት? ወይስ ይህ “የውሰጣችን ገመና ነው” ብሎ ሸፍኖ ሸፋፍኖ ቀበረው?
ወያኔዎች “የአማራ” የሚሏቸው ተከታታይ መንግስታት በእነዚህ የወያኔ አያቶችና አባቶች ሸፍጥ፣ ቂም ይዘው የትግራይን መሳፍንትና መኳንንት በኋላም የትግራይን ልሂቃን ከሃብት፣ ከስልጣን፣ ከሹመት አገለሏቸው? አላገለሏቸውም። በአጼ ሃይለስላሴ መንግስት ውስጥ ከነበሩ 40 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ውስጥ 11 ከመቶ የሚሆኑት ትግርኛ ተናጋሪዎች የነበሩ መሆኑን እዚህ ላይ እናስታውሰው። ከዚህ ጉዳይ ጋር በወያኔ ዘመን የሆነውን በተመለከተ በቦታው እንመለስበታለን።
ከትልልቅ ስልጣን ባለቤትነት ውጭስ ቢሆን የትግራይ ተወላጆች በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰው፣ አርሰው፣ ነግደው፣ በሲቪልና በወታደራዊ ተቋማት ተቀጥረው መስራትና መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቸው ወያኔዎች “የአማራ” በማለት የሚከሱት የኢትዮጵያ መንግስት አልነበረም? የአማራ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች፣ ከትግራይ የሚፈልሰውን ወገኑን እንደራሱ ወስዶ፤ ሰርቶ የሚኖርበትን ትዳርና ቤተሰብ የሚመሰርትበትን ሁኔታ ሲያመቻች እንደኖረ ይታወቃል። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከትግራይ ተሳደው፣ መጠጊያቸውን የአማራ ህዝብ ያደረጉ ለትልቅ ሃብትና ክብር የበቁ ታሪክ የሚያውቃቸው በርካታ ግለሰቦች አሉ። በግልባጩስ ብንመለከተው፤ በየትኛው ዘመን ነው አማራው፣ ወደ ትግራይ ሄዶ መሬት ወስጄ ልረስ፣ ሱቅ ከፍቼ ልነግድ፣ በግልና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ልቀጠር ያለው? ለመሆኑ በትግራይ ምድር ለአማራ ህዝብ የተዋለ ውለታ በታሪክ ተፈልጎ ይገኝ ይሆን? ይህን ቆየት ካለው ታሪካችን ጋር የተሳሰረ ጉዳይ በእዚሁ እንቋጨው። በክፍል ሶስት ቀረብ ወዳሉት ዘመናት በመምጣት ሂሳብ የማወራረዱን ስራ እንቀጥላለን።
Filed in: Amharic