>

ውድ ወንድሜ አቻምየለህ ታምሩ፤ አወ ልክ ነህ ያማራ ኃይል መዝመት ያለበት ወደ ወሎ ሳይሆን ወደ ዐራት ኪሎ ነው ( መስፍን አረጋ)

ውድ ወንድሜ አቻምየለህ ታምሩ፤ አወ ልክ ነህ ያማራ ኃይል መዝመት ያለበት ወደ ወሎ ሳይሆን ወደ ዐራት ኪሎ ነው

 

መስፍን አረጋ


ወያኔ የኢትዮጵያ ችግር ዋናው ምንጭ የነበረው፣ ፈላጭ ቆራጭ በነበረበት በ 27 ዓመቱ የመከራ ዘመን እንጅ ባሁኑ ጊዜ አይደለም፡፡  እደግመዋለሁ ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ችግር ዋናው ምንጭ ወያኔ አይደለም፡፡  ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ችግር ዋናው ምንጭ የወያኔን ዘረኛ ሕገመንግሥት እንዳለ በማሰቀጠል፣ የትግሬን የበላይነት በኦሮሞ የበላይነት የተካው፣ ጎጠኛው፣ ሸፍጠኛውና ዐምባገነኑ ዐብይ አሕመድ ዓሊ ነው፡፡  

እርግጥ ነው፣ ወያኔ ለኢትዮጵያ ትልቅ ችግር ስለሆነ፣ ይህ እኩይ ድርጅት እዛው እተፈጠረበት ደደቢት ላይ መቸም እንዳይነሳ ተደርጎ ለኻቹ ካልተቀበረ በስተቀር፣ አገራችን ኢትዮጵያ ከአጋም እንደተጠጋ ቁልቋል ዕድሜ ልኳን ስታለቅስ ትኖራለች፣ ለዚያውም ዕድሜ ከሰጣት፡፡  ነገር ግን፣ ወያኔ የኢትዮጵያ ትልቅ ችግር ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ዋና ችግር መሆኑ ግን ከዐራት ኪሉ በተባረረበት ዕለት አክትሟል፡፡  በተለይም ደግሞ ያማራ ኃይሎች ቅራቅር ላይ ድባቅ መትተውት ጣረሞት ውስጥ ከከተቱት በኋላ፣ ከትልቅ ችግርነት ወደ ኢምንት ችግርነት ወርዶ ነበር፡፡  

ዐብይ አሕመድ ግን ለወያኔ ‹‹የጽሞና ጊዜ›› በመስጠት በፍጥነት እንዲያንሠራራና የአማራን ሕዝብ ያለ ምንም ተጠያቂነት እንዲዘርፍና እንዲጨፈጭፍ ማመቻቸት ብቻ ሳይህን፣ ማድረግ የሚችለውን እገዛ ሁሉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ አደረገለት፡፡  ወያኔ በፍጥነት እንዲያንሠራራ ባደረገበት እቅዱ፣ ያማራ ኃይሎች ከጀርባ እየተመቱ እንዲዳከሙ መፈጸም የሚችለውን ደባ ሁሉ ፈጸመ፡፡  የአማራን ምድር ከከባድ መሣርያወች ጋር ለወያኔ እያስረከበ በሄደበት እቅዱ፣ የአማራ ኃይሎችን ግን ለሸኔ ያስታጠቀውን ድራጉኖቭ (dragunov) እንኳን እንዳይታጠቁ፣ ታንክን በዱላ እንዲጋፈጡ ፈረደባቸው፡፡  በመቶወች የሚቆጠሩ የወያኔ የጭነት መኪኖች በኮንቮይ መልክ እየተግተለተሉ ወያኔወችን አማራ ምድር ላይ እያራገፉ፣ ካማራ ምድር የዘረፉትን እየጫኑ ወደ መቀሌ በመውሰድ በጠራራ ፀሐይ ሲመላለሱ፣ የአማራ ሕዝብ በሚከፍለው ታክስ የተገነባው፣ በዐብይ አሕመድ ጠቅላይ አዛዥነት የሚታዘዘው፣ በይልማ መርዳሳ የሚመራው ዓየር ኃይል ዓይቶ እንዳላየ ዝም አላቸው፡፡  

ባጠቃላይ ለመናገር በአፋር ምድር ላይ የትም እንዳይንቀሳቀስ ያደረገውን ወያኔን፣ በአማራ ምድር ላይ መረን በመልቀቅ፣ የአማራን ሕዝብ በወያኔ አስጨፈጨፈው፡፡    ለወያኔ ሲሆን በጥያራ አጭቆ ገንዘብ ባስቸኳይ እንዳልላከ፣ ለአማራ ሲሆን ግን ቅንጣት ድጎማ በመንሳት ከወያኔ ጭፍጨፋ የተረፈውን የአማራ ሕዝብ በሰው ሰራሽ ጠኔ ፈጀው፡፡  የአማራ ሕዝብ እንደ ቅጠል የሚረግፍበትን ጦርነት፣ በዓለማችን ታይቶ የማይታወቅ ድል እያለ በአማራ መከራ ላይ ተሳለቀ፡፡  በአማራ ሕዝብ ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እስኪፈጸም ድረስ ሥራየ ብሎ እየጠበቀ፣ በነገታው አዳባባይ ወጥቶ አበባ በመትከል፣ ወይም ደግሞ በፌስቡክና በትዊተር ስለ አበባ ውበት በመደስኮር የአማራን ሞት ከዝንብ ሞት እንደማይቆጥረው በግልጽ አሳየ፡፡  የአማራን ሕዝብ ክፉኛ እያቆሰለ፣ ማቁሰሉ ብቻ ስለማያረካው በቁስሉ ላይ እንጨት መስደዱን ቀጠለ፡፡  ለመሆኑ፣ ይህን ያህል የመረረ ጥላቻ ምክኒያቱ ምንድን ነው? 

ዐብይ አህመድ የጭቆናን ምንነት በቅጡ ሊረዳ በማይችልበት ለጋ እድሜው “ያማራ ጨቋኞችን” ለመታገል ጫካ ገብቶ የወያኔን ጡት እየጠባ ባማራ ጥላቻ ተመርዞና ተሰቅዞ ያደገ፣ አማራን በማጥፋት አማራዊ ናት የሚላትን ጦቢያን አፈራርሶ በሷ መቃብር ላይ የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) ለመመሥረት ቆርጦ የተነሳ፣ በዚያ ላይ ደግሞ በማንነቱ ምክኒያት በሥርሰደድ (chronic) የስነልቦና በሽታ የሚሰቃይ ኦነጋዊ አውሬ ነው፡፡  የዚህ እኩይ ግለሰብ የአማራ ጥላቻ፣ ከወያኔ የአማራ ጥላቻ እጅግ ቢብስ እንጅ አያንስም፡፡  ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ ወይም ደግሞ ከለማበት የተጋባበት እንዲሉ፡፡

መለስ ዜናዊ (ከክቡር ከበደ ሚካኤል ተረትና ምሳሌ ላይ ያነበበውን የቄሳር ካሊጉላን ንግግር በመቅዳት) የአማራ ሕዝብ አንገት አንድ ቢሆን ኖሮ፣ ቀንጥሸው እገላገል ነበር ማለቱ ይነገርለታል፡፡  የመለስ አድናቂ የሆነው ዐብይ አሕመድ ግን የአማራን አንገት በመቀንጠስ ብቻ ሳይሆን ደሙንም በመጠጣት የሚረካ አይመስልም፡፡  ዐብይ አሕመድ የስልጣን ጥመኛ ቢሆንም፣ የስልጣን ጥሙ ግን ከአማራ ጥላቸው ስለማይበልጥበት፣ አማራ ተጠናክሮ ከሚያይ ይልቅ ወያኔ አዲሳባን ተቆጣጥሮ በስቅላት ቢቀጣው ይመርጣል፡፡  

ወያኔና ኦነጋውያን ጠባቸው የስልጣን እንጅ የአማራ ጥላቻን በተመለከተ የልብ ወዳጆች ናቸው፡፡  ስለዚህም የኦነጋውያን እቅድ ወያኔ የኦነግን የበላይነት አሚን ብሎ ተቀብሎ አማራን ሰቅዞ የሚይዝ ጎጠኛ ሎሌ እንዲሆን እንጅ እንዲጠፋ አይደለም፡፡  በሌላ አባባል ኦነጋውያን ለወያኔ ያዘጋጁለት ሚና፣ አማራን ፋታ በሚነሳ ደረጃ ጠንካራ ሆኖ ለኦነግ አሳሳቢ በማይሆን ደረጃ ደካማ እንዲሆን ነው፡፡  ስለዚህም ወያኔን ታማኝ ሎሌው ለማድረግ ያሰበውን ዐብይ አሕመድን ጠቅላይ የጦር አዛዥ አድርገህ፣ የአማራን ኃይል ወያኔን እንዲያጠፋ ማዝመት ማለት፣ ናዚን ለማጥፋት የዘመተውን የራሺያን ጦር ሂትለር ይምራው ማለት ነው፡፡  ዋናውን የወያኔ ደቀ መዝሙር ዐብይ አሕመድን ዐራት ኪሉ አስቀምጠህ፣ ወያኔን ለመዋጋት ወደ ወሎ መዝመት ትርፉ አላስፈላጊ መስዋዕትነትን መክፈል ብቻ ነው፡፡      

ባሁኑ ወቅት የአማራ ሕዝብ ትልቁ ጠላት ዐብይ አሕመድ እንጅ ወያኔ አይደለም፡፡  ወያኔ ማለት በዐብይ አሕመድ ላይ የተጫነ ዳውላ ማለት ስለሆነ፣ አህያው ከተወገደ ዳውላው የትም አይደርስም፡፡  ዓይኑን በጨው አጥቦ የሚዋሸው፣ ትናንት የተናገረውን ዛሬ የሚቃረነው፣ በማንነቱ ምክኒያት በሥርሰደድ (chronic) የስነልቦና በሽታ የሚሰቃየው ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ ከስልጣን ተወግዶ ብቁ፣ ቅን እና አገር ወዳድ በሆነ መሪ ከተተካ፣ የወያኔና የሸኔ ዕድሜ ከሳምንታት አያልፍም፡፡  አቶ ልደቱ አያሌው ሊወቀስ የሚችለው ወያኔን ባለማውገዙ እንጅ፣ ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ዋና በሽታ በሽተኛው ዐብይ አሕመድ ነው በማለቱ ምንም አልተሳሳተም፡፡  

በመጨረሻም ወንድማዊ ምክር፡፡  አንተ አቻምየለህ ታምሩ አገርህን በምትወዳት መጠን አቶ ልደቱ አያሌውም እንደመሚወዳት ማመንና መቀበል አለብህ፡፡  አያሌ ምሁር ነን ባዮች የኢትዮጵያን ችግር አይተው እንዳላዩ በመሆን ዐብይ አሕመድን በማወደስ ላይ በተጠመዱበት ሰዓት፣ አቶ ልደቱ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ ይሆናል የሚለውን ሐሳቡን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን ፈጅቶ በጽሑፍ በማቅረቡ ሊወደስ እንጅ ሊወቀስ አይገባውም፡፡  አቶ ልደቱን ያቀረበውን ሐሳብ በጨዋነት መቃወም ስትችል፣ ወይም ደግሞ አቶ አንዳርጋቸውን ባንድ ወቅት እንደጠየከው እንክራከርበት ማለት ስትችል፣ ቅራቅንቦ ነው ማለት አግባብ አይደለም፡፡  ያቶ ልደቱን ሥራ ድሪቶ ለማለት የተሸቀዳደምከው፣ የሰሜን ጠል ፖለቲካ የሚያራምዱት አንዳርጋቸው ጽጌና መሰሎቹ፣ በሐሳብ እጅግ በሚበልጣቸው በአቶ ልደቱ ላይ የከፈቱት መጠነ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሰለባ ሁነህ እንዳይሆን ራስህን በራስ ልትመረምር ይገባል፡፡  

በተጨማሪ ደግሞ አንተ የታሪክ ሰው ስለሆንክ፣ የበለጠው ትኩረትህ ባለፈው ላይ ሊሆን እንደሚችልና፣ አቶ ልደቱ ግን ፖለቲከኛ ስለሆነ የበለጠ ትኩረቱ ባሁኑና በመጭው ላይ ሊሆን እንደሚችል መርሳት የለብህም፡፡  እንዲሁም ያለፈውን መረጃ የማበራየት ችሎታህ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ያበራየኸውን መረጃ ዘንድበህ (extrapolate) የወደፊቱን የመገስለት (በስሌት የመገመት፣ guesstimate) ችሎታህ ግን እንደማበራየት ችሎታህ ከፍተኛ ላይሆንና በዚህ ላይ ጥቂት መሥራት ሊኖርብህ ይችላል (መሥራት ካለብህና ከፈለክ ደግሞ ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደምትራቀቅበት አልጠራጠርም)፡፡    

ከሁሉም በላይ ግን አማራ ሕዝብ ዐብይ ጠላት የሆነው መተተኘው ዐብይ አሕመድ፣ አንተ ራስህ የከፈትክለትን ቀዳዳ ተጠቅሞ በመተቱ ሊያኮላሽህና የአማራን ሕዝብ ትግል በአጅጉ ሊያዳክመው እንደሚችል አትዘንጋ፡፡  ባሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን ለማዳን በሚደረገው ወሳኝ ትግል ላይ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ጉምቱ ሰወቻችን፣ ዐብይ አሕመድ ሲጠራቸው ወዴት፣ ሲልካቸው ዐቤት የሚሉ የዐብይ አሕመድ አምላኪወች የሆኑት፣ እነሱ ራሳቸው በከፈቱለት ቀዳዳ ተሽቆጥቁጦ ከገባ በኋላ፣ በተካነበት አፍዝ አደንግዙ ለሱ ጅራታችውን የሚቆሉ፣ እሱን ቀና ብለው የማያዩ ሽቁጥቁጦች ስላደረጋቸው ነው፡፡  እነማንን እያልኩ እንደሆነ አንተው ራስህ ስለምታውቅ ስም መጥራት አያስፈልግም፡፡   ያብይ አሕመድ መተት በነሱ ይብቃ፡፡    

ስለዚህም ወድ ወንድሜ አቶ አቻምየለህ ታምሩ፡፡  የሞት ሽረት ትግል እያደረግን ስለሆንና፣ አንተም አቶ ልደቱም አጅጉን ስለምታስፈልጉን፣ በልደቱ ላይ ያለህን ቅሬት አደባባይ ላይ ከማውጣት ተቆጥበህ አንተም እንደ ልደቱ በትልቁ ጠላታችን በዐብይ አሕመድ ላይ አትኩር፣ ዐብይ አሕመድ ከተወገደ ወያኔ ባጭር ጊዜ ውስጥ ይወገዳልና፡፡   የአማራ ኃይል መዝመት ያለበት ወደ ወሎ ሳይሆን ወደ አራት ኪሎ ነው፡፡    

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic