የተጣለ ማዕቀብ የለም ….!!!
ሲሳይ አጌና
ፕሬዚዳንት ባይደን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለማስቆም መፍትሄ ያሉትን ማዕቀብ እንዲጥሉ ለሃገሪቱ የገንዘብ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ September 17/2021 ትዕዛዝ ሰጥተዋል/ፈርመዋል።
በዚህም ተኩስ አቁም ካልተደረገ ለተፈፀመው ሰቆቃ ተጠያቂ የሆኑ ባለስልጣናትን ለይተው ለወደፊቱ ማዕቀብ እንዲጥሉ ወስነዋል።ማዕቀቡ ዕርዳታ እና ንግድን እንደማይጨምር በጠቅላላ ሕዝቡን የማይመለከት እና የማይነካ መሆኑም ተመልክቷል።
ባይደን የሰጡት ልዩ ትዕዛዝ ወደፊት እየታየ የሚፈፅም ሲሆን፥ዕርዳታንም፥ንግድንም እንደማይመለከት ባላስልጣናት ለ,CNN ገልፀዋል። ይህም ማለት ኢትዮጵያን ጨምሮ 38 ያህል የአፍሪካ ሃገራትን ተጠቃሚ ያደረገውን AGOA መብቷንም አይነካም ማለት ነው።ይህ የኢትዮጵያ ዕድል እንዲሰረዝ የሕውሓት ሎቢስቶች ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው እና የሚመለከታቸው የአሜሪካ ባለስልጣናትም በዚህ ዙሪያ ማስፈራራታቸው ይታወሳል።
አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንደማትጥል፥ ብትጥል እንኳን የኢትዮጵያን መንግስት ከያዘው አቋም እንደማትመልሰው በባይደን አስተዳደር ግንዛቤ መወሰዱን ዋሺንግተን ፖስት አስቀድሞ August 5/2021 የተፃፈውን አንብበናል። አሁንም አዲስ ነገር የለም።
ኢትዮጵያ ድሃ እና አሁንም ከጥገኝነት ያልተላቀቀች ሃገር ብትሆንም፥ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንኳን ቢመጣ ለዚያ ራስን ከማዘጋጀት ውጭ ምርጫ የለም።ማንቁርቱን አንቀህ ትንፋሽ የነሳኽውን የጥፋት ሃይል ልቀቀውና እንዲጠናከር ፍቀድለት ፥ሺህዎችን ብቻ ሳይሆን መቶ ሺህዎችን እንዲፈጅም ሜዳ ስጠው የሚል ጥሪ እና ማሳሰቢያ ለተናጋሪዊ ቀላል ቢሆንም፣ ለሰለባዎቹ ግን አይሰማም!!