>

"ዘመነ መሣፍንትና ፋሽስት ወያኔ ....!!!!"  (አቻምየለህ ታምሩ)

“ዘመነ መሣፍንትና ፋሽስት ወያኔ ….!!!!”

 አቻምየለህ ታምሩ

ኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰችበትን ቁልቁለት አንዳንድ ሰዎች ከዘመነ መሣፍንት ጋር ያመሳስሉታል። ይኽ ግን ፍጹም የተሳሳተና ዘመነ መሣፍንትን ካለመመርመር የሚሰጥ ግልብ አስተያየት ነው። ዘመነ መሣፍንት በግራኝ ጦርነትና በረይቱማ እና ቦረን ጎሳዎች ወረራዎች ፈርሶ የነበረውን የኢትዮጵያ አውራጃዎች አንድነት እንደገና አንድ ለማድረግና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ለመገንባት የማይሞት ራእይ የነበራቸው የአካባቢ መሣፍንት የተነሡበት የሐሳብ ዘመን ነበር። 
በዘመነ መሳፍንት የአካባቢ መሣፍንት የተደራጁት በቋንቋና በሃይማኖት ሳይወሰኑ በዘመናዊ መንገድ ነበር። ይኽ የዘመነ መሣፍንት ዘመናዊነት መገለጫው በሐሳብ እንጂ እንደ ዛሬው በነገድ ያልነበረው አደረጃጀታቸው ነው። ዛሬ የምንገኘው ከዘመነ መሣፍንት ዘመን በመቶ እጥፎች ወደ ኋላ ሄደን ፋሽስት ወያኔ በእያንዳንዱ የአማራ ቤተሰብ ደረጃ የሽብርና የዘር ማጥፋት ዘመቻ በሚያካሂድበት ዘመን ላይ ነው። ዛሬ የደረስንበት ቁልቁለት የዘመነ መሣፍንቱ ደረጃ ቢኾን ኖሮ በስንት ጣዕሙ በታደልን ነበር።
ባጭሩ ዘመነ መሣፍንት ኢትዮጵያን እንደገና አንድ ለማድረግና ማዕከላዊ መንግሥት ለመመሥረት የየአካባቢው መሣፍንት በቋንቋና በሃይማኖት ሳይወሰኑ በሐሳብ ተደራጅተው ይፎካከሩበት የነበረ ብሩህ ወቅት ነበር። የዘመነ መሣፍንት መኳንንቶችና መሣፍንቶች ራእይ፣ በቋንቋ አጥር የተከፋፈሉ የጎሳ ሀገሮች የመመሥረት ሳይኾን የዐፄ ዐምደ ጽዮንንና የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብን የሁሉም የኾነች ኢትዮጵያን መልሶ ማቋቋም ነበር።
ከአድዋው ራስ ሚካዔል ስሑል እስከ ቋረኛው ካሣ ኃይሉ፤ የዘር ሐረጉን ከሰለሞን ይመዝ ከነበረውና ራሱን ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የማድረግ ሕልም ከነበረው ከከፋው ንጉሥ ጋኪ ሸሮቾ እስከ ሐማሴኑ ደጃዝማች ወልደ ሚካዔል ሰለሞን፤ ከየጁው ራስ ዓሊ አሉላ እስከ ጉራጌው/ስልጤው ሐሰን እንጃሞ ድረስ የነበሩት የአካባቢ መሳፍንት የነበራቸው ሕልም ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመግዛት ነበር።
የጉራጌው/የስልጤው ሐሰን እንጃሞ የሸዋው ንጉሥ መናገሻቸው አንኮበር በነበረበት ወቅት አንኮበር ድረስ ዘምቶ አካባቢውን የመጠቅለልና ራሱን “የሐበሻ ንጉሥ” የማድረግ ሕልም እንደነበረው ብዙ ሰው የሚያውቅ አይመስለኝም። ስለዚህ ታሪክ ወርቁ ንዳ የተባሉ የታሪክ ጸሐፊ “ጀብዱ፣የጉራጌ ባሕልና ታሪክ” በሚል ርዕስ በ1983 ዓ.ም. በሳተሙት የታሪክ መጽሐፍ በስፋት አብራርተዋል። አዛውንት ሐጂ ደርባቸው መሐመድ ገለቱም ምስጋና ይግባቸውና አያታቸው ለትውልድ እንዲተላለፍ ያወረሷቸውን ታሪክ ዋቢ በማድረግ በቅርቡ ባሳተሙት የጉራጌ/ስልጤ ታሪክ መጽሐፋቸው የወርቁ ንዳን ታሪክ ደግፈው ጽፈዋል።
በዘመኑ ጉራጌዎች/ስልጤዎች ዘንድ ሳይቀር ሐሰን እንጃሞ “የሐበሻ ንጉሥ” ለመሆን መነሳትን  በአማርኛ  እንደሚከተለው ገጥመውለት ነበር፤
ሐሰን እንጃሞ የእስላም ንጉሡ፣
ወጥ አይበላም ያለ ድግሡ፣
መገሌን ጃሞ የእንጃሞ ፈረስ፣
ቆርጦ ተነስቷል አልጋውን ሊያፈርስ፣
አዋሽ ተነስቶ አንኮበር ሊደርስ፤
ሐሰን እንጃሞ የአንኮበርን አልጋ አፍርሶ እሱ በመሰየም “የሐበሻ ንጉሥ” የመሆን ሕልሙን ለማሳካትም ብዙ ዘመቻዎች አድርጓል። በመጨረሻም ከሸዋ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ከራስ ጎበና ዳጬ ጋር ፍልሚያ አድርጎ በመሸለፉ ሊጠቀልል ተነስቶ ተጠቅልሏል። በዚህ ወቅትም ጉራጌዎቹ/ ስልጤዎቹ ጀግንነቱን እንዲህ ብለው በግጠም ገልጸውት ነበር፤
ሐሰን እንጃም ደንዳናው ገባር፣
ጎቤን ገጠመው ግንባር ለግንባር፤
ሐሰን እንጃሞ ራስን ጎበናን ግንባር ለግንባር ገጥሞ ከተሸነፈ በኋላ [በዚህ ዋቤን ተሻግሮ በሚገኝ ቦታ በተካሄደ የመጨረሻ ጦርነት መርዕድ ጎበና (ደጃዝማች) የሚባለው የራስ ጎበና ልጅም በጦር ተወግቶ ሞቷል] ካልገዛሁ አገር አፈርሳለሁ ሳይል ራሱን አግልሎ እስከ ሕይዎቱ ፍጻሜው ድረስ በሰላም ኖሮ አልፏል።
ስለዚህ ፋሽስት ወያኔን እያንዳንዱን አማራ የሆነ ፍጥረት ሁሉ በቤተሰብ ደረጃ ለማጥፋት ቤት ለቤት እየተዘዋወረ ፍጅትና ውድመት የሚፈጽምበትን የሽብርና የዘር ማጥፋት ወረራ አገር አንድ አድርገው ለመግዛት የተነሱ ባለራዕዮች ከላይ ታች ይሉበት የነበረውን የዘመነ መሣፍንት ዘመን አንድ አድርጋችሁ የፋሽስት ወያኔን የጦር ወንጀለኛነት አታቃሉት። ዘመነ መሣፍት አይደለም የሽብርና የዘር ማጥፋት ወረራ እያካሄደ ከሚገኘው ከፋሽስት ወያኔ ጋር የቋንቋና የጎሳ ፖለቲካ ከሚካሄዱት፣ በድንቁርና የጎሳ ሀገር ለመመሥረት ከሚራኮቱ ጎሰኞች ጋርም ሊወዳደር ሊወዳደር አይችልም። ዘመኑ ትልቅ ሐሳብና የማይሞት ራእይ የነበራቸው የአካባቢ መሣፍንቶች በቋንቋና በሃይማኖት ሳይወሰኑ ታላቅ የጋራ ሀገር ለመመሥረት ይወዳደሩ የነበሩበት የብርሀን ዘመን እንጂ እንደዛሬው የዘር ማጥፋትና የሽብር ወረራ የሚካሄድበት የጨለማ ዘመን አልነበረም።
በዘመነ መሳፍንት ማዕከላዊ መንግሥትና የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ባይጠናቀቅም እንደዛሬው ሕግና ኅሊና ጨርሶ የጠፋበት፤ አንድን ሕዝብ ለማጥፋት ቅዬው ተወሮ ቤት ለቤት አደን የሚካሄድበት ዘመን አልነበረም። ዘመነ መሣፍንት ሕግና ኅሊና የማይገዛቸው ጎሰኞችና ወሮበሎች የተፈጠሩበት ዘመን አይደለም። በዘመነ መሳፍንት የአካባቢ መኳንንቶች ሁሉ የማይተላለፉት ሕግ፣ የማይሽሩት የአውራጃ ይዞታ፣ የመሬት ባለቤትነት መብት እና የአስተዳደር ወሰን ነበር። ዛሬ ላይ ግን እንደምናየው ፋሽስት ወያኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስና አማራን ለማጥፋት ያሰለጠናቸውን ተከታዮቹን  በሙሉ አሰልፎ የሌሎችን አካባቢ በመውረር በቤተሰብ ደረጃ አንድን ሕዝብ ለማጥፋት የጅምላ ፍጅት፣ ውድመት፣ ዘረፋና ሽብር እያካሄደ ይገኛል። እንዲህ አይነት የጦር ወንጀለኛነት አይደለም በዘመነ መሣፍንት አውሮፓውያን ቅኝ በገዙባቸው አገሮች ሁሉ ተፈጽሞ አያውቅም።
ባጭሩ ፋሽስት ወያኔ በወሎና በጎንደር እየፈጸመው ያለው አይነት ጅምላ ፍጅትና የዘር ማጥፋት፤ ከዚህ የተረፈውን እያንዳንዱን የአማራ ቤተሰብ ደግሞ አደህይቶ እንዲሞቱ ለማድረግ እያካሄደው ያለው ውድመት እንኳን በዘመነ መሣፍንት ዘመን አስከፊ ቅኝ ግዛት በተካሄደባቸው አገራት ሁሉ በቅኝ ገዢዎች አልተፈጸመም። ስለዚህ አይደለም በዘመነ መሣፍንት ዘመን እስከፊ ቅኝ ግዛት በተካሄደባቸው የአለም አገሮች እንኳን ያልተፈጸመ የቤት ለቤት የጅምላ ፍጅት፣ የዘር ማጥፋት፣ ዘረፋና ውድመት በግፍ በወረራቸው አካባቢዎች እየፈጸመ የሚገኘውን ሕወሓት የሚባል የወንጀል ድርጅት ከዘመነ መሣፍንት ጋር እያወዳደራችሁ ፍትሐዊ ባልሆነ ሚዛን እየሰፈራችሁ አለማቀፍ ወንጀለኛውን በጣም ዝቅ ባለ ልኬት በመመዘን ትይዩ ሊሆን ወደማይችልበት ሚዛን አታስቀምጡ። ኢትዮጵያ ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን እንወርዳለን ያሉትን ፋሽስት ወያኔንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለመግዛት ይወጡ ይወርዱ የነበሩትን የዘመነ  መሣፍንት የአካባቢ ገዢዎች ባንድ ረድፍ ወይም ባንድ መደብ ማስቀመጥ ፋሽስት ወያኔን በጣም ከማግዘፍ ውጪ ቁም ነገር የለውም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን ለመውረድ የተማማሉትን ፋሽስት ወያኔዎችን በኢትዮጵያ ይምሉ ከነበሩ የዘመነ መሣፍንት ተዋናዮች ጋር አንድ ረድፍ በማስቀመጥ መመዘንና መተቸት ቀርቶ ማውገዝም እንኳን ቢሆን ከፍተኛ ድንቁርና ነው።
ፋሽስት ወያኔ ስሙ አብሮ መጠራት ያለበት ሚሊዮኖችን በጅምላ ከፈጁት ከሒትለሩ የናዚ ቡድንና ከሙሶሎኒው የፋሽስት ፓርቲ ጋር ነው። የሙሶሎኔው ፋሽስት ፓርቲ ራሱ  ዛሬ ላይ በሕይዎት ቢኖር ኖሮ የመንፈስ ልጁ ፋሽስት ወያኔ የግፍ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በድኆች ላይ እያደረሰ በሚገኘው ጅምላ ፍጅት፣ እልቂትና ውድመት አዝኖ የሚያወግዘው ይመስለኛል።
ናዚዎች ከሁሉም በላይ በእስላምና በአይሁዶች ላይ የነበራቸው ጥላቻ ወደር አልነበረውም። በዚህም የተነሳ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ አይሁድና እስላም ጨፍጭፈዋል። ናዚዎች በእስላምና በአይሁድ ላይ የፈጸሙትን አረመኔያዊ ጭፍጨፋና ውድመት ፋሽስት ወያኔዎች በወረሯቸው የጎንደርና ወሎን አካባቢዎች በሚገኘው የአማራ ሕዝብ ላይ በየዕለቱ እየፈጸሙት ይገኛሉ።
ፋሽስት ወያኔዎች ያላስለቀሱት፤ ሜዳ ላይ ለጅብ ያልበተኑት፤ በየ ኬላውና በየጥሻው የየብስና የባሕር ሲሳይ ያላደረጉት ቤተሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ባይኖርም በግፍ በወረሯቸው የወሎና የጎንደር አካባቢዎች እየፈጽሙ ያሉት የቤት ለቤት የጅምላ ፍጅት፣ የዘር ማጥፋት፣ ዘረፋና ውድመት ግን ከናዚዎች ዘመን በኋላ ተከስቶ አያውቅም።
እነዚህን ጨካኞች ይህንን ሁሉ ግፍ በሰው ዘር ላይ እየፈጸሙ በአደባባይ ንጹሕና አልፎም ተበዳይ መስለው እንዲታዩ ያደረጋቸው ከኛው ከራሳችን በዘረፉት ሀብት የአለምን መስሚያ በገንዘብ ደፍነው ነው። ከዚህ ውጭ በእውነተኛ ሕግ ፊት ፋሽስት ወያኔዎች አለም የሕዝብ ጠላቶች እና የሰላማዊ ሕይወት ጠንቆች እያለ ከሚፈርጃቸው ወሮበላዎች ሁሉ የከፉ አረመኔዎች ናቸው። እነዚህን ኢትዮጵያን ለማፍረስና አማራን ለማጥፋት ሲዖልም ቢሆን ለመውረድ የተማማሉ አረመኔዎች ኢትዮጵያን መልሶ አንድ የማድረግ ሕልም ከነበራቸው የዘመነ መሣፍንት የየአካባቢ ገዢዎች ጋር አንድ አታድርጓቸው።
Filed in: Amharic