>
5:21 pm - Tuesday July 21, 7125

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን  አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን  አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ

ማዕቀቡ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደርና የህወሓት አባላትን ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።

በዚህም ዕቀባ ግጭቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁሙን የተከላከሉ በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።

ይሄንንም ትዕዛዝ በዋነኝነት የሚያስፈጽመው የአሜሪካ ግምጃ ቤት (ትሬዠሪ) ሲሆን የውጭ ጉዳይ መሥሪያቤቱም ተባባሪ ይሆናል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የቀጠለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከፍተኛ የሆነ የሕዝቦችን ስቃይ አስከትሏል እንዲሁም የኢትዮጵያን አንድነትም አደጋ ላይ ጥሏል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

በዚህ ጦርነት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ በከፍተኛ ችጋር ተመትተዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል፣ ታግደዋል እንዲሁም ወከባ ደርሶባቸዋል። “የምሰማው የጅምላ ግድያ፣ መድፈር እና ሕዝብን ለማሸበር የሚደረጉ ወሲባዊ ጥቃቶች ሪፖርቶች አስደንግጠውኛል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው።

በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና የህወሓት ኃይሎች በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል።

በጭካኔ የተሞሉ ግድያዎች፣ መድፈርና ወሲብ ጥቃቶች በሰፊው ተፈጽመዋል ያለው መግለጫው በተባበሩት መንግሥታት መሰረት፤ በሠሜን ኢትዮጵያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ታዳጊዎች በደረሰባቸው ወሲባዊና ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ህይወታቸውን እንደገና ለመገንባት የህክምና፣ የአእምሮ ጤና፣ የሥነ-ልቦና እና የሕግ አገልግሎቶች ያስፈልጋቸዋል።

“ዛሬ የፈረምኩት ትዕዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን የሚያራዝሙ፣ ሰብዓዊ ተደራሽነትን የሚያደናቅፉ እንዲሁም የተኩስ አቁሙን የከለከሉ ወይም ተባባሪ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ አዲስ ማዕቀብ ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን።

በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በኤርትራ መንግሥት፣ በአማራ ክልላዊ መንግሥትና በህወሓት አባላትና ሌሎችም ጦርነቱን ለማስቀጠል እየገፋፉ ባሉ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መንግሥታቸው ለግምጃ ቤቱ አስፈላጊውን ሥልጣን መሰጡትንም መግለጫው አትቷል።

አሜሪካ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመደገፍ እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ትስስር ለማጠናከር አሁንም ቁርጠኛ ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እነዚህ ማዕቀቦች በኢትዮጵያ ወይም በኤርትራ ሕዝቦች ላይ ያተኮሩ እንዳልሆኑም አሳስበዋል።

“ማዕቀቦቹ ያተኮሩት በጦርነቱ ሰብዓዊ ቀውስን በፈጠሩ ግለሰቦች ወይም አካላት ላይ ነው። ከማንኛውም አገር በበለጠ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ እና የልማት ዕርዳታ እንሰጣለን። በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማቅረብ ከአጋሮቻችን ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

እነዚህ ማዕቀቦች በሚጣሉበት ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያም ሆነ በቀጠናው ላይ ያልታሰበ ተፅዕኖ ለማቃለል እርምጃዎችን ትወስዳለች ተብሏል።

ማዕቀቡ ላልተጣለባው ግለሰቦች ገንዘብ መላክ፣ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እና የረጅም ጊዜ የእርዳታ መርሃ ግብሮች እና መሠረታዊ የሰውን ፍላጎቶች የሚመለከቱ የንግድ እንቅስቃሴዎች ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ መላው የአፍሪካ ቀንድ ክልል መግባታቸውን ሕጋዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ እንደምትጥርም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ የመከላከያ (ወታደራዊ) ንግዶች ላይ ገደቦችን የጣለች ሲሆን በግጭቱ ውስጥ ላሉ ማናቸውም ወገኖች የጦር መሳሪያ ፍሰትን ለማስቆም እና በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ሌሎች አገራትም ይህንኑ እንዲተገብሩ ጠይቃለች።

ሆኖም በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች ድርጊት የአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ለመጣሉ የሚወስን ይሆናል ተብሏል።

በግጭቱ አፈታት ላይ መሻሻል ከሌለ አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል የተዘጋጀች ሲሆን ነገር ግን መሻሻሎች ካሉ አገራቸው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ከዚህ ጦርነት የምታገግምበትን መንገድ፣ ከፍተኛ እዳዋን ለማቅለል እና ምጣኔ ሀብቷንም ለማነቃቃት አገራቸው እንደምትሰራም ፕሬዚዳንቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

አስተዳደራቸው በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ የመበት ጥሰቶች እንዲቆሙ እና ለተቸገሩ ሰዎች ሰብዓዊ ተደራሽነት እንዲደረግ ግፊት ማድረጉን እንደሚቀጥል አፅንኦት ሰጥተዋል።

አሜሪካ ከአጋሮች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሁሉም ወገኖች ግጭቶችን እንዲያቆሙ፣ ያልተገደበ የሰብአዊ ተደራሽነትን እንዲፈቅዱ እና እንዲያመቻቹ፣ ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ወደ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቧም ተገልጿል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እና የግጭቱን ፖለቲካዊ እልባት ለማምጣት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ በነሐሴ ወር ለድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት በሰጡት አስተያየት “ሁሉም ወገኖች አንድ ቀላል እውነት መገንዘብ አለባቸው ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ የለም” ያሉትን ጠቅሰው ወደ ድርድር መምጣት አለባቸው ብለዋል ጆ ባይደን።

አሜሪካ ይህ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቆርጣ መነሳቷንም አስታውሰው የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆ የሚያደርጉትን የሽምግል ጥረቶችና ሌሎችንም ሙሉ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ከተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ከአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጋር የተስማማሙት ለዚህ ቀውስ ምንም አይነት ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለው ነው ብለዋል።

“ከመላው አፍሪካ እና ከመላው ዓለም የመጡ መሪዎች ጋር ጥሪ የማደርገው የግጭቱ ተሳታፊዎች ወታደራዊ ዘመቻቸውን ገታ አድርገው ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ ተደራሽነትን እንዲፈቅዱ እንዲሁም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር እንዲመጡ ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ያሳሰቡ ሲሆን “የተለየ መንገድ መምረጥ ይቻላል ነገር ግን መሪዎች እሱን ለመከተል መምረጥ አለባቸው” ብለዋል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ግጭቱ ካልቆመና መሻሻሎች ካልታዩ፤ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደምትወስድ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።

ባለፈው ወር የአሜሪካ ጠቅላይ ግምጃ ቤት በኤርትራ ጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ ላይ ዕቀባ መጣሉ የሚታወስ ነው።

ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ በአሜሪካ ውስጥ ባላቸው ንብረትና ገንዘብ ላይ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ዕቀባ የተጣለ ሲሆን ለሚመለከተው የአገሪቱ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣንም ስለግለሰቡ ሪፖርት እንደሚደረግም ተመልክቷል።

ከሦስት ወራት በፊት፣ ግንቦት 15/2013 ዓ.ም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ካለው ግጭት ጋር እየተፈፀሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጥቃቶች አገራቸው በተደጋጋሚ ስጋቷን ብታሰማም ትርጉም ያለው ምላሽ ባለመኖሩ አገራቸው የጉዞ እቀባ መጣሏን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

በዚህም በኢትዮጵያና በኤርትራ የቀድሞ እና የአሁን ባለስልጣናት፣ ወታደራዊ እና ደኅንነት ኃላፊዎች እንዲሁም የአማራ ክልል መደበኛና ኢ-መደበኛ የጸጥታ አባላትና ግለሰቦች፣ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ባደናቀፉ የህወሓት አባላት ላይ የቪዛ እቀባ አሜሪካ ጥላለች።

ይህ በግጭቱ ላይ እጃቸው ያለበት ወይም ተባባሪ የሆኑትን የሚመለከት ሲሆን እንዲሁም የቅርብ ቤተሰቦቻቸውም ጭምር እቀባው ተግባራዊ ሊሆንባቸው ይችላል ተብሏል።

ከጉዞ እቀባው በተጨማሪ አሜሪካ የምታደርገውን የምጣኔ ሀብትና የደኅንነት እገዛ እንዲቋረጡና ግጭቱ ካልቆመና መሻሻሎች ካልታዩ፤ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደምትወስድም አስጠንቅቃ ሌሎችም አገራት የአሜሪካን ፈለግ እንዲከተሉ ጥሪ አድርጋለች።

ከዚህም በተጨማሪ ‘ዲፌንስ ትሬድ ኮንትሮል ፖሊሲ’ ተግባራዊ እንደምታደርግም ገልጻ ነበር።

ይህ እርምጃ በሕዝብ ላይ ጥፋት የሚፈፀምበት የቴክኖሎጂ ግብአት ላይ ከሚደረግ ቁጥጥር ጋር የተያያዘ ሲሆን ሰፋ ያለ ይዘት ያለው ይህ ፖሊሲ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን ጨምሮ፣ ሶፍትዌሮች፣ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ቁሳቁሶችና ረቀቅ ያሉ ወታደራዊ ቴክኖሎጂን ያካትታል።

ባይደን ዛሬ የፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝን በተመለከተ አፈጻጸሙንና ዝርዝሩ አብሮ ይፋ ተደርጓል። ውሳኔውን በተመለከተ ዕቀባው ከሚመለከታቸው ወገኖች እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

Filed in: Amharic