>

ጦርነትን ከሰው ልጅ ልብ ለማረቅ የተሳናቸው...??? (አሰፋ ሀይሉ)

ጦርነትን ከሰው ልጅ ልብ ለማረቅ የተሳናቸው…???

አሰፋ ሀይሉ

የክርስትናም፣ የአይሁድም፣ የእስልምናም ቀደምት አማኒዎች የሆኑ ሕዝቦች፣ ከጥንት እስከዛሬ በጦርነት እሳት እየተለበለቡ ነው የኖሩት! ከተፈጥሮ መቅሰፍት በላይ ሰው በፈጠረው ጦርነት እየታመሱ ዘመናትን የዘለቁ ህዝቦች ናቸው።
የቀደመው የአይሁድ እምነት ተከታይ የሆኑት ህዝበ እስራኤሎች በመጨረሻ በዓለሙ ተበትነው እስኪቀሩ ድረስ በብሉይ ኪዳናት በስፋት እንደተዘከረው ዘመናቸውን ሁሉ የባጁት በዙሪያቸው ካሉ ሕዝቦች ጋር የማያቋርጥ ጦርነትን በማካሄድ ነው።
የክርስትናው ዓለምም ሕዝቦች ታሪክ በደንብ የሚታወቅና በማስረጃዎችም የተደገፈ የፍጅትና ያልተቋረጠ የጦርነት ታሪክ ነው።
የእስልምናውም ዓለም ደግሞ ሲጀመር ጀምሮ በመሳደድና በማሳደድ ተግባሮች የተሞላ፣ እስከዛሬም ጦርነትና ኃይል ያልተለየው የፍጅትና የውድመት ታሪክ ያለው ነው።
በክርስትያኑ ዓለምና በእስላሙ ዓለም መካከል የተካሄዱት የመስቀል ጦርነቶች፣ እና የአይሁድ እምነት ወራሾች ተጨምረውበት፣ ዛሬም ድረስ አንዱ ከሌላው ጋር እያበረ ሌላውን እየወጋና እያስወጋ እስከዛሬም የእነዚህ አውራ ሐይማኖቶች ተከታዮች የጦርነት ታሪክ እንደቀጠለ ነው።
እምነት ነው ወይ ሕዝቦቹን የሚያፋጀው? ቢሆን ኖሮ ክርስትያንና ክርስትያን ሕዝቦች ከዘመን ዘመን እርስበርስ እየተጋደሉ አይዘልቁም ነበር።
ጉዳዩ የእምነት ቢሆን የእስልምናው ዓለም እርስ በእርሱ ተከፋፍሎ እየተባላና እየተናከሰ ዘመናትን አይሻገርም ነበር።
ይህ ሁሉ የየህዝቦቹ መጠፋፋት የእምነት ጉዳይ ቢሆን ኖሮ የክርስትናው ዓለም በእምነት ከሚቀርበው ከእስልምናው ዓለም ጋር አብሮ በአይሁዱ ላይ በተነሳ ነበር።
እና በኃይል በማመንና፣ በፈጣሪ በማመን መካከል የሆነ ግንኙነት አለ ወይ? የሰው ልጅ ጭራሽ እምነት ሲኖረው ነው ወይ የመጨረሻው የክረት ደረጃ ላይ ደርሶ የሚጠፋፋው? የምስራቃዊ ቀደምት ቤተዕምነት አማኞች ለምን ከክርስትናው ይልቅ እስልምናው ቀልባቸውን ማረከው?
የእነዚህ ሶስት ቤተእምነቶች ተከታዮች ኮሙኒዝም የሰዎችን እምነት አጥፍቶ የዓለምን ሕዝብ ካጠፋፋ የበለጠ የጥፋት ታሪክ አላቸው? ቤተ እምነቶች (በተለይም አይሁድ፣ ክርስትናና፣ እስልምና) ረዥሙ ጉዟቸው ሲገመገም፣ ለሰው ልጅ ሠላምና መፋቀር ያበረከቱት አስተዋፅዖ ይበልጣል? ወይስ የሰውን ልጅ ቆስቁሰው፣ ጀንጅነው፣ እሳት አስጨብጠው ያጫረሱበት እኩይ ጎናቸው ያይላል?
ለመሆኑ ሐይማኖቶች ባይኖሩ የሰልጅ አሁን ከተላበሰው በላይ አውሬነትን ይላበስ ነበር? ዓለም እነዚህን ሶስት ቤተእምነቶችበማግኘቷ የበለጠ ሠልጥናለች? ወይስ የበለጠ ሠይጥናለች?
እነዚህ እምነቶች ያለ ጠላት (ያለ ሠይጣን) እና ያለ ውጊያ ራሳቸውን ችለው መኖር የሚያስችል ሰብዕና አላቸው ለሠሆኑ? ወይስ የሸይጣንና የፈጣሪን የማያቋርጥ ፍልሚያ አርፎ ለተቀመጠው ለሰው ልጅ በመስበክ፣ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ጦራቸውን ያለመታከት እየነቀነቁ ሊዘልቁ ነው ያሰቡት?
የሰው ልጅስ በእነዚህና በሌሎችም ቤተ ዕምነቶች ለዘመናት ሁሉ የፈጣሪን ፅድቅ ሥራ ሲሰበክ ኖሮ፣ ምግባሩ እየተቀደሰና ወደ ፅድቅ እየተጠጋ መጣ? ወይስ ይበልጥ እየረከሰና ክፋቱ እየባሰበት ሄደ?
የሰው ልጅ ከሐይማኖት እየራቀ፣ በሐይማኖት እየተንገፈገፈ መጣ? ወይስ ይበልጥ ወደ ሐይማኖትና መንፈሳዊነት እየተሳበ ሄደ? እነዚህ ሶስት ቀደምት ቤተእምነቶች የወደፊቷን ዓለም ያይዋታል? ከዓለም ፍፃሜ በፊት ግብዓታቸው ይፈፀማል? ወይስ ከነቁመናቸው ፀንተው የዓለምን ፍፃሜ ይሻገራሉ?
“እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር –
እነዚህ ሶስቱ ፀንተው ይኖራሉ፣
ፍቅር ግን –
ይበልጣል ከሁሉ።”
ሳስበው የወደፊቱ የሰው ልጅ ሐይማኖት ፍቅር ይመስለኛል! የምን ፍቅር? ጥያቄው አያልቅም!
ከሁሉ የሚበልጠውን ፍቅርን ይስጠን!
ኢትዮጵያ ፍፃሜ በሌለው ፍቅር ፀንታ ትኑር!
Filed in: Amharic