>

«አሸባሪው ህወሓት የሚፈጽማቸውን በደሎች ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አይቶ እንዳላየ እያለፈ ነው...!!!» (አቶ ኦባንግ ሜቶ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

«አሸባሪው ህወሓት የሚፈጽማቸውን በደሎች ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አይቶ እንዳላየ እያለፈ ነው…!!!»
 – አቶ ኦባንግ ሜቶ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች

(ኢ ፕ ድ )
ጁንታው በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለው ጭፍጨፋና ግድያ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጆሮ ዳባ ብሎ ማለፉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ አመለከቱ።
አቶ ኦባንግ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፣ አሸባሪው ህወሓት በማይካድራ፣ በአፋር ጋሊኮማ፣ በወሎ እና በሌሎች አካባቢዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። አሁንም እየፈጸመ ቢሆንም የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚባሉ ድርጅቶች ለችግሩ ትኩረት መስጠት አልፈለጉም።
የዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚቆሙት እንደስማቸው ለሰብዓዊ ሳይሆን ለራሳቸው ፍላጎት መሆኑን የገለጹት አቶ ኡባንግ፣ አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ላይ የፈጸመውን ፍጅት አይተው እንደላዩ ማለፋቸው ይህንኑ ሃቅ እንደሚያረጋግጥ ያሳያል ብለዋል። ሰብዓዊ መብት ተከራካሪው አክለውም ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸውም አሸባሪ ቡድኑ የሚፈጽማቸው አረመኔያዊ ድርጊቶች የእነሱ በጎ ፍቃድና አቋም ጭምር ሊኖርበት ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳጫረባቸው ገልጸዋል።
የተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማትና አንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት በማይካድራ፣ በአፋር ጋሊኮማ፣ በወሎ እና በሌሎች አካባቢዎች በንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ግፎችን ከማውገዝ ይልቅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት ችግር ሲፈጥሩ እንደሚስተዋሉ አቶ ኡባንግ ተናግረዋል።
«በመሰረቱ የንጹሃን ዜጎቻችን የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ የራሳችን ኃላፊነት እንጂ የዓለምአቀፍ ጉዳይ አይለም» ያሉት አቶ ኦባንግ፣ ዋናው ቁም ነገር የዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ምላሽና ዝምታ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ የጥፋት ኃይሉን ለማስወገድ የሚያደርጉት ርብርብ ችግሩን ከመሰረቱ ለመንቀል እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
Filed in: Amharic