>

ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አሊ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ (ባልደራስ)

ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አሊ የተጻፈ

ግልጽ ደብዳቤ
 
ጉዳዩ፡- በባልደራስ አመራሮች ላይ እየደረሰ ያለውን መንግስታዊ በደልን በተመለከተ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ 

ይሄንን ደብዳቤ በምጽፍሎት ወቅት እርሶ ለአሜሪካው ፕሬዝደንት በጻፉበት ሳምንት ውስጥ መሆኑ ግጥምጥሞሽ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ላይ የደረሰው የፍትህ መጎደልና እኔ በምሰጠው አመራር ላይ ሸውራራ አመለካከት የአሜሪካ መንግስት ይዞብኛል የሚል መነሻ ይዘው በመሆኑ ፤ እኔም በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ላይ የሚደርሰው ኢፍትሃዊ የሆነ መንግስታዊ በደል አስመልክቶ ፤ እርስዎ የሚመሩት መንግስት የሚወስደው እርምጃን ማውገዝ አግባብ ይሆናል ብዬ በማሳቤ ልጽፍሎት ተነስቻለሁኝ ።
    ይህ ወደ እርስዎ የተላከው ደብዳቤ ግልጽ እንዲሆን የተደረገው ፤ ለታሪክ እና  ለኢትዮጵያውያን ጥያቄችን በአግባቡ እንዲረዱ በመሻት ጭምር ነው።
    ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራችን በዚህ ወቅት ያለችበትን ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ መከራ ለምን ተጫናት ብዬ ልጠይቅዎት አልሞክርም፤ምላሽ እየተሰጠ ያለበትንም ሁኔታ በዚህ ደብዳቤ ለምን ይሄ ሆነ በማለት ልተችዎ አልፈልግም፤የሚፈጽሙት የመረጡትን መንገድ በመሆኑ ወደፊት በዚሁ ጉዳይ እመለስበታለሁ።
   ሆኖም ስለፍትህ መጎደል ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ. ባይደን የጻፉላቸውን ደብዳቤ ሀሳብ ካየሁት በኃላ ግንዛቤ ይኖሮት እንደሆነ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ላይ የሚደርሰውን ኢፍትሃዊ ድርጊት ላስታውሶት በመውደዴ ፣ እንዲሁም ከመጪው መንግስት ምስረታዎ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ በአደባባይ የሚያነሷቸውን የሽንገላ ቃላቶች አስታክኬ በፓርቲያችን አመራር ላይ የደረሰ ኢፍትሃዊ ተግባር እና የእርስዎ መንግስት በደል እንዲያስቆሙ ልጠይቆ ነው፡፡
     ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያውቁት የፍትህ ሀ..ሁ.. ከሆነው ውስጥ የመጀመሪያው ” የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል” እንደሚባል እርስዎም የሚያውቁት ይመስለኛል ፤ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር የሆኑት የሰላማዊ እና የሰብአዊ መብት ተማጓቹ አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ የፓርቲያችን አመራሮቻችን በእስራት ላለፉት 15 ወራት ምስክር በግልጽ አላሰይም፣  አሳይ በሚል ክርክር ብቻ ንጹኃ ኖች በስቃይ ላይ ይገኛሉ፡፡
    ትላንት በህውሃት አመራር ዘመን የመናገርና የመጻፍ ነጻነቱ ተገፎ ከ10 ዓመት በላይ በእስራት ዕድሜውን ያሳለፈው፤እንዲሁም እመጫት ሆና በህውሃትም ይሁን አሁን ከምታጠባበት ተጎትታ ለእሰራት ተዳርጋ  ትላንትም ዛሬም መከራዎን የምታየው አስቴር ስዩም የመሰሉ ፍትህ እንፈልጋለን የሚሉ ንጹሃንን ያለፍትህ መንገላታታቸው በእጅጉ ያሳዝነኛል ፣ በንጽኃን ላይ እየደረሰ ያለው በደል ሁሌም ያስቆጨኛል ። ከትላንትና የቀጠለው ሕጋዊ ሽፍን እያላበሱ ተቀናቃኝን ማንገላታት ማብቂያው እንዴትና መቼ ይሆን እያልኩ እጠይቃለሁ ?!
    ወደ ፍርድ አደባባይ እየተመላለሱ ፍትህ አጥተው ቤተሰቦቻቸው፣ጓደኞቻቸው፣ የትግል አጋሮቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው እያዘኑ፤  በእርስዎ መንግስት የፊጥኝ የታሰረችው ፍትሕ ንጹሃንን ምን ያህል እያንገላታች እንደሆነ እየመሰከሩ ያሉት የእርሶ መንግስት ስራ መሆኑን ባሰብኩ ግዜ ታላቁ መጽሃፍ ‹በሰው አይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ከማውጣት በፊት በአንተ አይን ወስጥ ያለውን ግንድ አውጣ›  የሚለውን ላስታውሶ በመፈለጌ ነው፡፡
    ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መንግስትዎ አቶ ታዲዎስ ታንቱ አይነት አዛውንት ላይ የሚሰራውን ግፍ ሳልቆጥረው ቀርቼ አይደለም፤ምርጫውን በተመለከተ የተደረገውን ማጭበርበር ፤ ሌሎች በሀገራችን ውስጥ ፍትህን ለማሳጣት የሚያደርገውን ሂደት ለምስክርነትና ለምሳሌነት አይበቃም ከሚልም አይደለም፤ይልቁኑ እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን መጀመሪያ ክፉ ጠላት ሀይማኖትና አገር ሊያጠፋ ሲመጣብን መጀመሪያ ጠላታችንን መከላከልና መመከት እንዳለብን ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወሰድነውን ትምህርት ጠንቅቀን በማወቃችን ሆኖ እንጂ !!
    ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ያስታውሱ እንደሆን የመልካም ዕድል ምሽት ባማረ ሁኔታ ባሰሩት መናፈሻ በተዘጋጀ የዕራት ግብዣ ተገኝተው ህዝብ ድርጅቶን ካልመረጠ በሰላም ስልጣን እንደሚያስረክቡ፤ከተመረጡ ግን ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ የተናገሩትን ከምርጫውም በኃላ እርሶም ሆኑ ብዙዎቹ የፓርቲዎ አመራሮች ስልጣን ለተቃዋሚዎች እንዳገኙት የህዝብ ድምጽ እንደሚያጋሩ የተናገሩትን ባሰብኩ ቁጥር ‹‹ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ››እንድል የሚያደርግ ተግባር ከሚመሩት መንግስቶ ከዕለት ዕለት የማይሻሻል መልኩ የሚታይ በመሆኑ ነው፡፡
   ለተቃዋሚዎች ስልጣን ማጋራት ያስፈለገው የአብዛኛው ህዝብ ድምጽ እንዳይባክን ለማድረግና የህዝቡ ድምጽ እንዲሰማ፤ እንዲሁም ብዙ ምስቅልቅሎሽ ያለባትን ሀገራችን የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩንም በማቻቻል ከድህነት እንድትወጣ ፣ ልማቷን ለማፋጠን፣ሰላሟን ለማስፈንና ከውስጥም ከውጭም የተጋረጠብንን መከራ ተባብረን ለመመከት እንድንችል ነው፡፡ በአንጻሩም ለተቃዋሚዎች ስልጣን ማጋራት ከዚህ ምስኪንና ደሃ የኢትዮጵያ ህዝብ ላብ ላይ ተወስዶ ባለስልጣኖችዎ የሚኖሩትን የቅንጦት ህይወት ለመጋራት በፍጽም እንዳልሆነ ይሰማኛል፡፡
    ከእውነት ለኢትዮጵያ ማገልገል እና መስራት እንደ መታደል የሚቆጠር በመሆኑ ኩራት ነበር፡፡ ይሁንና መንግስትዎ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የያዙት የበቀል በትር ከላይ ያነሳሁትን እንኳን ሊመልስ ይቅርና ፍትህ ለመጠየቅ እርስዎና ድርጅትዎ ምን አይነት የሞራል መሰረት ይኖሮታል እንድል ያደርገኛል፡፡
     ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የበቀል በትርዎ በዶ/ር በቃሉ አጥናፉ የፓርቲያችን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ የነበሩ የኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩንቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ከሚሰሩበት ከምርምር ዳይሬክተርነታቸው በማንሳት፤ ስርዓትዎ ኢፍትሃዊ መሆኑን በገሃድ ያሳዩበት ነው፡፡ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ እጅግ ታታሪ እና ሀገር ወዳድ በነጻነት የሚሰማውን ሀሳብ የሚይዝ በጉብዝናው ዛሬ የደረሰበት ደረጃ የደረሰ ሀገሩን ለማገልገል ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ነው፡፡ ለባልደራስ በህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት እንዲሁም ፓርቲው ከሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን በተለይ ምርጫውን ተከትሎ የተዘጋጁ ቅድመ እና ድህረ ምርጫ ጥናቶች ሳይንሳዊ እንዲሆን አድርጎ ያዘጋጀ፤ ለወደፊትም የሀገራችን ፍታሃዊ እና ነጻ ምርጫ በጥናት ላይ የተመሰረት ለማድረግ መሰረት የጣለ ደፋር፣ጀግና የፓርቲያችንና የሀገራችን አለኝታ መሪ ላይ መንግስትዎ ያሳረፈውን የበቀል በትር ከኢፍታዊነት ባሻገር ለተቃዋሚዎች ስልጣን አጋራለሁ የሚሉት ከዚህ ቀደም ለተቃዋሚዎች በህወሃት የሚመራው ኢህአዴግ ገንዘብ የሚሰጣቸው ቀለብተኛ ተቃዋሚዎች እርሶዎም እንደ ያኔ መሰል ፓርቲዎችን ስልጣን ለማጋራት አስበው ከሆነ ይብላኝላቸው እንጋራለን ብለው ለሚጠብቁት።  እኛስ ለዶር በቃሉ አጥናፉ አይነት ታታሪ ሰው በችሎታው ማገልገል የሚቻልበት የምርምር እና የትምህርት ተቋም ሀገራችን ሊኖራት አለመቻሉ በጣም ያሳዝናል፡፡ ስልጣኑንማ አሽከርነት ነው ብለን በአፍንጫችን ይውጣ ብለን እንጸየፈዋለን፡፡
    ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ካለፉት 3 ዓመት ስህተቶችዎ የተማሩ መስሎኝ ነበር! በካድሬ እና በተረኝነት መንፈስ የተሞላ የመንግስት መዋቅር አገራችንን ወዴት ሊወስዳት እንደሚችል መከላከያው ላይ የነበረበት ሁኔታ፤ የውጭ ግንኙነት መስሪያ ቤታችን እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ዋንኛ ማሳያዎች ሊሆንዎት በተገባ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ በተለያዩ ክፍለ አለማት በዲፕሎማሲ ስራ ላይ የነበሩ አምባሳደሮችና ሰራተኞች ወደሀገር እንዲመለሱ ያደረጉት በነሱ ምትክ ለስራው ሳይሆን ለእርሶ ታዛዥ በሆኑ ለመተካት መሆን የለበትም፡፡ ሆኖም በዶ/ር በቃሉ አጥናፉ የተተኩትን ስናስብ ሀገራችን መከራዎ ገና ብዙ፤ወደፊትም የሚቀጥል ልጆቿም ለነጻነትና ለእኩልነት ትግል ወገባቸውን ማጥበቅ እንዳለባቸው ያስገነዝበናል፡፡
     እንደ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ አይነት ታጋይ እርሶና አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ብዙዎቹ ጓደኞችዎ ከህወሃት ጋር አብራችሁ የኢትዮጵያ ህዝብን ቁምስቅሉን በምታሳዩበት ወቅት፤ ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት በቅንጦት አማርጣችሁ እንድትማሩ ስልጣንና ሁሉ ነገር በተመቻቸላችሁ ግዜ፤ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ህወሃትን በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ግንባሩን ሳያጥፍ፤እዩኝ እዩኝ ሳይል ሲታገል የነበረ ሀገር ወዳድ ጀግና ነው፡፡ በዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ላይ መንግስትዎ ያደረሰው ከሌሎች ብዙ የስርዓትዎ ኢፍትሃዊነት አንጻር ሲታይ ተስፋ የምንቆርጥበት ሳይሆን ልንታገለው የወጣንለት ዓላማ ትክክለኝነት ማሳያ ነው፡፡
     ትላንት እነእስክንድር የከተማችንን ቅርስ የማጥፋት ዘመቻ፣መሬት ወረራ፣የኮንዶሚንየም ዝርፊያና የመሳሰሉት ኢፍትሃዊ ድርጊቶች በማጋለጣቸው ከደረሰባቸው ገፈት አንጻር ሲታይም ትንሹ ቢሆንም፤ለታላቋ ሀገር አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ላሳያቸው ኢፍትሃዊነት ከጻፉት ደብዳቤ አንጻር አይተው ምላሽ ቢሰጡ አሊያም ክቡርነትዎ እንዳሉት ኢትዮጵያ ሁሌም ለነጻነት በምታደርገው ትግል ብቻዋን እንደሆነችው ሁሉ፤እኛም ለነጻነታችን የምናደርገው ትግል ሁሉም ዜጎች በሃገራቸው እኩል እሰከሚታዩ ድረስ የማንንም ይሁንታ ሳያስፈልገን ጠንክረን እየታገልን እንደምንቀጥል ልገልጽልዎ እፈልጋለሁ፡፡
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
ጌታነህ ባልቻ በሻህ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንት
Filed in: Amharic