>

የመስከረም 24 ፖለቲካ...!!! (ወንድወሰን ተክሉ)

የመስከረም 24 ፖለቲካ…!!!

ወንድወሰን ተክሉ

 

« የቀድሞው ጠ/ም አቶ ኋይለማሪያም ደሳለኝ ከእነሙሉ ድክመትና ችግሮቻቸው ከብልጽግናው ዶ/ር አቢይ ሙሉ በሙሉ ይሻላሉ። ዶ/ር አቢይ በሶስቱ ዓመት አገዛዛቸው ኢትዮጲያን ለመምራትና በተለይም ከተዘፈቅንበት ችግር ለማውጣት የሚያስችል ብቃትና አቅም የሌላቸው መሆናቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል። » 
 ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው 
 
     
 
*….አቢይ አህመድ ከኋይለማሪያም ደሳለኝ የባሰ ደካማና ብቃት የለሽ ከሆነ ለምንድነው በመሪነት ለመቀጠል ሲሰናዳ በዝምታ ልናይ የቻልነው ???
 
**
 
፨   ከዚህ ከአቶ ልደቱ አያሌው ሀሳብና እይታ ጋር አንዳችም ችግር የለብኝም። የህወሃት መጠቀሚያ ፑፔት እያልን ክፉኛ ስናብጠለጥላቸው ስንተቻቸውና ስንቃወማቸው የነበሩት አቶ ኋይለማሪያም ደሳለኝ በጠ/ም/ነት  ስድስት ዓመት አገዛዛቸው ኢትዮጲያ ዛሬ በአቢይ ዘመን እያየች ያለውን አሰቃቂ እልቂት ያላሳዩ ከመሆናቸውም በላይ ህዝባዊው አመጽ ተቀጣጥሎ በተፋፋመበት ወቅት ለሀገሪቱ ህልውና የእኔ ከስልጣን መነሳት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለት የአዛዣቸውን ህወሃት ትእዛዝ  በመጣስ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው በመልቀቅ ለለውጥ ትልቁን ሚና የተጫወቱ ናቸው።
፨ በሶስቱ የአቢይ ዘመን ያመረትነው ምንድነው ???
ከእልቂት መከራ የእርሰበርስ ጦርነት ብሄርና እምነት ተኮር አሰቃቂ ጭፍጨፋና የሀገራችን ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ  እያንሰራራ የነበረው ኢኮኖሚያችን መንኮታኮት፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነታችን በሱዳን ተደፍሮ መወረርና ኢትዮጲያ በሻእቢያው ኢሳያስ ቀጥተኛ ትእዛዝ ስር ወድቃ መጫወቻ መሆንና የምእራባዊያን ሀገራት በሙሉ ያገለሏት ሀገር ከመሆን  በስተቀር ምን ያየነው የተሻለ ሁኔታ አለ?? ይህንን የተሻለ ሁኔታን ሊፈጥር የሚችል አመራር ያልታየ በመሆኑ አቶ ልደቱ እንዳለው ኋለማሪያም ደሳለኝ ከእነ ሙሉ ድክመቱ ከአቢይ  አህመድ ሙሉ በሙሉ የተሻለ መሪ መሆኑ ላይ አንዳችም ቅዋሜ እንደሌለኝ ሁሉ አብዛኛው ኡትዮጲያዊ እይታ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።
፨ለመሆኑ ኢትዮጲያ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት IDP ከ3.6ሚሊዮን በላይ በመያዝ ከዓለም ከሲሪያ ሊቢያ የመንና ኢራቃ በልጣ በአንደኝነት ደረጃ ላይ የተገኘቺው በዚሁ በአቢይ መሃይማዊ አገዛዝ ምክንያት መሆኑን እንዘነጋለንን???
፨ ለመሆኑ ዛሬ በጎንደር በወሎ በአፋርና ብሎም በትግራይ እየተካሄደ ባለው አሰቃቂ የእርሰበርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀን በመቶሺህ የሚቆጠር ወጣትና ብሎም አጠቃላይ የአማራ የአፋርና የትግራይ ህዝብ በጦርነቱ ጥይትና በርሃብ እንዲረግፍ እየተደረገ ያለው በአቢይ መሀይማዊ የፖለቲካ ፖሊሲና ውሳኔ ምክንያት እንደሆነስ እንዘነጋለንን?? ወይንስ ሁሉንም ችግርና ትርምስምሱን ለአንዷ ወያኔ በማሸከም «ጁንታው ነው» እያልን አቢይን ብቁ መሪ በማድረግ እንመለከታለን???
እናም እነዚህን ሁኔታዎችን በስክነት ስንመለከትና ብሎም ስንመረምር እውነታው አቶ ኋይለማሪያም ደሳለኝ ከአቢይ አህመድ በእጅጉ በልጦና ተሽሎ ያለበትን ሁኔታ ነው ቁልጭ ብሎ የምናየው።
የኢትዮጲያ ሁኔታ ግን ከአቶ ኋይለማሪያምም ሆነ ከአቢይ አህመድ የተሻለና የበለጠ አመራርን የሚጠይቅና የሚፈልግ ሁኔታ ላይ ያለ በመሆኑ የአቢይ በስልጣን ላይ መቀመጥ ማለት ይህንን ሀገራዊን ችግር ሳንፈታ በላይ በላዩ እየጨምርን ወደ ሁለንተናዊ መፍረስ ደረጃ ላይ መድረስ ማለት ስለሆነ ኋይለማሪያምን ያልፈለገቺው ኢትዮጲያ አቢይንም በመቶ እጥፍ የማትፈልግ ሀገር መሆናን ነው የምናየው።
ሌላው አስደናቂው ልዩነት የአቶ ኋይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣን ነጻ ያልሆነና በህወሃት ቀጥተኛ  ትእዛዝና ቁጥጥር ስር የነበሩበት መሆኑና በአንጻሩም አቢይ አህመድ ግን ስልጣኑን በፍጹም ነጻነትና ብሎም አይደለም ኋይለማሪያም እራሱ መለስ እንኴን ባልተጠቀመበት ሁኔታ  አቢይ ስልጣኑን ገደብ ባለፈ ሁኔታ ያለአንዳች ሞጋችና ተገዳዳሪ ብቻውን እንዳሻው የማዘዝና የማናዘዝን ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው ሆኖ መገኘቱና በዚህ ያልተገደበ የስልጣን ነጻነት ተጠቅሞ እየሰራ ያለው ሁኔታን ስንመለከት ከአቶ ኋይለማሪያም ደሳለኝ መቶ ግዜ በችሎታና በብቃት ያነሰ ሆኖ እንድናየው ያደርገናል።  ምናልባት አቶ ደሳለኝ ኋይለማሪያም አቢይ የሚጫወትበትን ነጻ ስልጣን ቢያገኙ ኖሮ በስድስቱ ዓመት ቆይታቸው የተሻለ ይሰሩ ነበር ብሎ መገመት ያስችለናል።
የሆነው ሆኖ ብቃት የለሹ ናርስሲስትና ፋሺስት አቢይ አህመድ መስከረም 24 መንግስት እመሰርታለሁ ብሎ ሽርጉድ ከጀመረ ሰነባብታል። ይህ በአቢይ የሚመሰረተው መንግስት ተብዬ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዳለ በአቢይ አመራር የሚቀጥል ከሆነ አቢይ የኢትዮጲያ የመጨረሻ ጠቅላይ ምኒስትር ይሆናል በማለት አቶ ልደቱ አያሌው ብልጽግና አዲስ መሪ ይመርጥ ሲል ይናገራል።
ይህም የአቶ ልደቱ ሀሳብ ትክክል ሆኖ -ማለትም የብልጽግና በአቢይ አመራር ስር ገዢ  ፓርቲ መሆን ማለት የሀገራችንን ሁኔታ ተባብሶ እንድትፈርስ የመስማማት ያህል ነው መባሉ ትክክል ሆኖ በአጠቃላይ የብልጽግና በአቢይ ስር መመራትም ሆነ በአዲስ መሪ መመራት በሀገሪቱ ችግር ላይ መፍትሄ ለማፍለቂ በቂ አይሆንም ብዬ አምናለሁ።
ይህ ማለት እኛ ኢትዮጲያዊያን ህገወጡን ብልጽግናን መሰከረም 24 እመሰርታለሁ የሚለውን መንግስት መቀበል አይገባንም ብቻ ሳይሆን በዝምታ ማየት አይገባንም ማለት ይሆናል። የሀገራችንን ችግር ብልጽግና ያባብሰዋል እንጂ አያሻሽለውም ብለን ስናምን ከብልጽግና ውጪ ያሉ አማራጮችን -ሁሉን ያካተተ የሽግግር መንግስት አይነት አማራጭ እንድንመለከት ያስፈልገናል ማለት ነው።
የሁሉን አቀፍ የሽግግርን መንግስት ወሳኝነት አቶ ልደቱን ጨምሮ ጥቂት እማይባሉ ፖለቲከኞች አስተጋብተውት ገዢ ሀሳብ መሆን ያልቻለ ቢሆንም ያለን ፍቱን መድሃኒት ማፍለቂያው መንገድ ግን በደንባራው ብልጽግና ብቻ ሀገሪቷን የሚገዛበትን ሁኔታ ከመቀበል የሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ምስረታን መጠየቅና መቀበልን ይጠይቃል።
የአቢይ አህመድ መራሹን የብልጽግናን ፓርቲ በመጪው መስከረም 24 ሊመሰርት ለቀደው መንግስት ብቁ ያለመሆን እስቲ በአቢይ አመራር ያሳለፍናቸውን ሶስት ተኩል ዓመታትን በዝርዝር እንፈትሽ። የአቢይ አመራር ያስከተለውን ሀገራዊ ጥቅምና ጉዳት፣ ሀገራዊ በርከትና መርገምትን ጎን ለጎን በማስቀመጥ እንመዝነውና በሚያመዝነው ላይ ውሳኔያችንን እናስቀምጥ። ያኔ የአቢይ አመራር ምን ያህል ጠቃሚ አስፈላጊነቱና ምን ያህል አፍራሽ አደገኛነቱ ቁልጭ ብሎ ይታየናልና በዝም ብሎ ጭፍንተኝነት አቢይ ይቀጥል ወይም አቢይ ይነሳ ከሚል በብዥታ የተሞላ ውሳኔ መታቀብ ይቻለናል።
፨   (አቶ ልደቱ አያሌው «ብልጽግና ሆይ ለአዲሱ አመት እጅህ ከምን» በሚል አርእስት ስር በመስከረም 24መንግስት ምስረታ ዙሪያ ባስተላለፈው መል እክቱ ላይ «በየመስከረሙ24 ፖለቲካ» አርእስት ስር በዝርዝር የምመጣበት መሆኑን ለመግለጽ  እወዳለሁ)
Filed in: Amharic