>

ያልተዘመረላቸው ጸረ ፋሽስት ጀግና!   (አቻምየለህ ታምሩ)

ያልተዘመረላቸው ጸረ ፋሽስት ጀግና!  

አቻምየለህ ታምሩ

 

ታላቋ ድምጻዊ  እጅጋየሁ ሽባባው [ጂጂ] «እማማ ኢትዮጵያ» በሚለው ዘፈኗ ብዙ ለስሜት ቅርብ የሆኑ ሀሳቦችን  ታነሳለች። ጂጂ በስንኞቿ  የራሷን ኢትዮጵያ  በዘፈኗ ገንብታ ዘመናችንን ጥለን ወደኋላ እንድንጓዝ ታስገድደናለች። ዐፄ ቴዎድሮስ ወደተነሱበት  የተረሳ  ህልማቸው ሄዳ፤
 
ኃይለኛ አርበኛ አርበኛ ላይ፣
ልውጣ መቅደላ ልበል ዋይ ዋይ፣
ምነው ቢነሳ መይሳው ካሳ፣
አልወድም ጎበዝ ጀግና ሲረሳ፤
 
ትላለች። ጂጂ በዚህ ዘፈኗ   አንድ መሪ ወይንም ሐሳብ ያለው ጀግና ሐሳቡ ሲተው፣ ተከታይ ሳይኖረው፣ ሲረሳ አልወድም ማለቷ ይመስለኛል። እኔም ምንም እንኳ የምንኖረው በብዙ ችግር ውስጥ ሆነን  ቢሆንም  ያለፉ  ጀግኖች  ሲረሱ አልወድምና ከአምስቱ አመት የጸረ ፋሽስት ጥሊያን ተጋድሎ ጋር ስማቸው ሊነሳ ስለሚገባለው አንድ  ወጣት ጀግና ላወሳ ወደድሁ። 
 
እኒህ ጀግና የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጦር ትምህርት ቤት የሆነው የሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ምሩቅ ነበሩ። ከሆለታ  ገነት በፊት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው እውቀትን ቀስመዋል። በሆለታ ገነት ቆይታቸው አስፈላጊውን የመኮንንነት ትምህርት ከጨረሱ በኋላ  ሌተናት ኮሎኔል ሆነዋል። በሆለታ በነበራቸው ብቃት  የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት  ጦር  ሁለተኛው ሪጅመት አዛዥ ለመሆን በቅተዋል።  
 
ፋሽስት ጥሊያን ኢትዮጵያን ሲወር የሻለቃ ጦር በመያዝ  ጣርማ በር ላይ የተደረገውን የመጨረሻ ተጋድሎ መርተዋል። ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ጦር ሰፈር ወደ ምዕራብ ሲዛወር ወደ ነቀምት አምርተው የጥቁር አንበሳ ጦር ሲቋቋም የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ሆነው ተመርጠዋል። በጠቅላይ አዛዥነታቸው በርካታ ኦፕሬሽኖችን መርተዋል። በነቀምት ቦንያ ሲያንዣብቡ የነበሩ ሶስት የጠላት አውሮፕላኖችን ያወደሙበትና ጠላትን ሙሉ በሙሉ የዶግ አመድ ያደረጉበት ኦፕሬሽን ዋናው ነው። 
 
ከጊዜ በኋላ ነቀምትን እንዲለቁ ሲገደዱ ወደ ጎሬ በመሄድ ከራስ እምሩ ጋር የተወሰነ ቢቆዩም፤ እነ ራስ እምሩ እጅ ሲሰጡ እጅ አልሰጥም በማለት ተጋድሎውን በመቀጠል ጅማን ነጻ ለማውጣት ወደ ጎጀብ አምርተዋል። ጎጀብ ሲደርሱ  በሽሽት ላይ የነበሩ አዛውንቶች፣ ሕጻናትና ሴቶች  ከለላ ጠይቀዋቸው አብረው ተቀላቅለው  በጉዞ ላይ እንዳሉ  የጠላት ጦር ከቧቸው «ሕጻናትና ሽማግሌ አላስፈጅም»  በማለት  ለመማረክ ተገደዋል። ከዚያ በኋላ  መጀመሪያ ጅማ፣ በኋላም  አዲስ አበባ ታስረው ቆይተው በግራዚያኒ ላይ የግድያ ሙከራ በተደረገ ወቅት  እኒህን ጀግና በአውሮፕላን በመጫን ሶስቱን የፋሽስት አውሮፕላኖች የዶግ አመድ ባደረጉበት  ቦንያ ላይ ከአውሮፕላን በመወርወር ጭካኔያቸውን ተወጥተውባቸዋል። 
 
ይህንን ሁሉ ጀብዱ የፈጸሙት ኢትዮጵያዊ ጀግና  በግፍ ሲገደሉ እድሜያቸው ሀያ አንድ አመት ከዘጠኝ  ወር ነበር። ስማቸው ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ይባላል። ልብ በሉ! ሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ያንን ሁሉ ታሪክ የሰሩት የ21 አመት ልጅ ሆነው  ነው።  ከወረራው በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በገነት ጦር ትምህርት ቤት ውስጥ መታሰቢያ አቁመውላቸው ነበር።  ለእናት አገራቸው መተኪያ የሌለው መስዕዋትነት የከፈሉት  የነ በላይ ኃይለ አብ መታሰቢያ የሚገኝበት ታሪካዊው  የሆለታ ገነት የጦር  ትምህርት ቤት  ኢትዮጵያን ለማፍረስና የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት በታገለው በወያኔው ሐየሎም አርአያ ስም ይጠራል። 
 
ጀግናው ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ የተወለዱት በ1908 ዓ.ም. ሲሆን  ትውልዳቸው ከመረብ ማዶ ከባህረ ነጋሽ ነው።  እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዛችን ብለው ሊወጓት ጫካ ቢገቡና ቢያደሟትም እነ ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ ግን ለእናት አገራቸው ኢትዮጵያ የሞት ጽዋን ተቀብለዋል።   ክብር ለጀግናው ኢትዮጵያዊ  ሰማዕት ለሌተናት ኮሎኔል በላይ ኃይለ አብ!
Filed in: Amharic