>

ማዕቀቡ በስራ ላይ መዋል ጀምሯል...!!! (አፈንዲ ሙተቂ)

ማዕቀቡ በስራ ላይ መዋል ጀምሯል…!!!

አፈንዲ ሙተቂ

*…. የአሜሪካ ከእውነታው ጋር የተጣረሰ ንግግር‼
*…. በመጀመሪያው ምዕራፍ የጦር መሳሪያም ሆነ መለዋወጫ፣ ስልጠናም ሆነ መረጃ ከአሜሪካ በስጦታ እና በገንዘብ አታገኙም ተብላችኋል። በሁለተኛው ምዕራፍ የሚመጣው እቀባ ከዚህ የባሰ እንዳይሆን ያስፈራል።
——-
ይህ መንግሥት 
# አሜሪካ እና አውሮጳ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ለምን እንደሚያስፈራቸው በጭራሽ የገባው አይመስለኝም። አሜሪካም ሆነ አውሮጳ ከኢትዮጵያ የሚያስገቡት ርካሽ ሸቀጥና የሚዘርፉት የተከማቸ ሀብት የለም። እነርሱ በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩበት ምክንያት ከዚህ በጣም ይለያል (መንግሥት ከከፈለኝ በመጽሐፍ ጠርዤ እሰጠዋለሁ። ካልሆነ እርሱ ከሚከፍላቸው ኤክስፐርቶች ጠይቆ ይረዳ። There is no free lunch. ሁሉንም ነገር በነፃ መጻፍ አቁመናል)።
# “ከአሸባሪ ጋር እንዴት እንደራደራለን?” የሚል አመክንዮ ሲቀርብ በጣም እገረማለሁ። የዓለምን ሁኔታ የሚከታተል ግለሰብም ሆነ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ምክንያት አያቀርብም። ለምሳሌ እስራኤል ሐማስን “አሸባሪ” ትለዋለች። ነገር ግን እስራኤልና ሐማስ በተጋጩ ቁጥር የዓለም ሀገሮች “ተደራደሩ” እያሉ በሁለቱም ላይ ጫና ያካሄዳሉ። ሃያ ወይም ሃያ አምስት ቀን ከተጋጩ በኋላ ግብጽ ወይንም ጀርመን ሁለቱንም ወገኖች በማደራደር ጦርነቱ እንዲቆም ያደርጋሉ።
አሁን እየተባለ ያለውም ይህ ነው። “ከፍተኛ ቀውስ፣ እልቂት፣ ውድመት እና የህዝብ መፈናቀል ከመከሰቱ በፊት ተደራደሩ”  ነው የተባለው። መደራደር ማለት የህወሓትን ፍላጎት መቀበል ማለት አይደለም። መደራደር ማለት ሀገርን ከአደጋ መታደግ ማለት ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት “ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተደራደሩ” ነው ያሉት። ይህ መልካም መነሻ ነው። “ህወሓት ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ተቀበሉ” ቢባል ኖሮ ድሉ የህወሓት ይሆን ነበር። ፕሬዚዳንቱ ባስቀመጡት አቅጣጫ የሚጠቀሙት በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑት የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ አርሶ አደሮች ናቸው። የእነርሱ ችግር ተቀረፈ ማለት ሀገር ተጠቃሚ ሆነች ማለት ነው።
—-
ባለፈው ጊዜ ሰማንታ ፓወርን ስላላነጋገራችኋት አውሮጳና አሜሪካ “ጦርነቱ እንዲቆም አትፈልጉም” በማለት ደምድመዋል። አሁንም የተሰጣችሁ አልቲሜተም ከማለቁ በፊት በደንብ አስባችሁበት ጦርነቱን ለማቆም መዘጋጀታችሁን የሚገልጽ ምላሽ ብትሰጡ ይሻላል። ለሀገርና ለህዝብ የሚበጀው እርሱ ነው።
በተያያዘ መረጃ:- የአሜሪካኑ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከእውነታው ጋር የተጣረሰ ንግግር‼
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ “ጠንካራ አገራት ደካሞችን መጫን የለባቸውም” የሚል እምነት አላት ማለታቸው መነጋገሪያ ሆኗል።
አስተዳደራቸው በየአገራት የውስጥ ጉዳይ ገብቼ ልፈትፍት ሲልና ይህንንም በተለያዩ ስልቶች ጫና እያሳደረ ለማስፈፀም በሚጥርበት ወቅት ፕሬዝዳንቱ ለ76ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ነው ይህን ያሉት።
ይህ ንግግርም አሜሪካ እያደረገች ካለው እውነታ ጋር የሚጣረስ ነው በሚል በርካቶች እየተቀባበሉትና እየተቹት ይገኛሉ። ከልዕለ ኃያላን አገራት ጋር ‘በእኔ እበልጥ እኔ’ መካረር ውስጥ መግባታቸው ባይካድም ፕሬዝዳንት ባይደን ግን አገራቸው ሌላ ቀዝቃዛው ጦርነት እንዲነሳ እንደማትፈልግ በንግግራቸው አክለዋል።
አሜሪካ ከትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ትቅደም ነጣይ ፖሊሲ ይልቅ ትብብርን ትሻለችም ነው ያሉት። ዓለም ዐቀፍ ትብብርና አንድነት ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ትብብሩ ለኮሮናቫይረስና ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም በረቀቁ የቴክኖሎጂ ግኝቶች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመመከትም ጭምር እንደሆነ ገልፀዋል። በዚህም ቻይናን ተጠያቂ ሊያደርጉ ሞክረዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በንግግራቸው አሜሪካ “ከእረፍትየለሹ” የአፍጋኒስታን ቆይታ መውጣቷን አስታውሰው አሁን በምትኩ እረፍት የለሽ ያሉትን ዲፕሎማሲ እየጀመሩ ስለመሆኑ አንስተዋል። ስለኮሮናቫይረስ ባደረጉት ንግግርም አገራቸው በዋናነትም ድሃ አገራት የመከላከል፣ የማከምና የመከተብ አቅማቸው እንዲያድግ ሁሉን ዐቀፍ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።
Filed in: Amharic