>

እነርሱ ሽብርተኛ ያሉትን "ዳኤሽ" ፣ "ሰይጣን"  ሲሉ ትክክል፤  እኛ ስንለው ወንጀል .... ? (ዮሀንስ መኮንን)

እነርሱ  ሽብርተኛ ያሉትን “ዳኤሽ” ፣ “ሰይጣን”  ሲሉ ትክክል፤  እኛ ስንለው ወንጀል …. ?
ዮሀንስ መኮንን

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሰሞኑን በአንድ መድረክ ላይ ህወሓትን “እንደ ሰይጣን የመጨረሻ ፍጥረት መሆን አለባቸው” ብሎ በመጥራቱ እና “ህወሓቶች ከነ አስተሳሰባቸው መደምሰስ አለባቸው” ብሎ መናገሩ አሶሽየትድ ፕሬስ እና ቢቢሲን የመሰሉ  የምዕራባውያን “ቢጫ ጋዜጠኞች” ትኩስ አጀንዳ ከመሆን አልፎ ሳማንታ ፓወርን የመሰሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት መግለጫ የሚሰጡበት ርእሰ ጉዳይ ሆኗል።
[ምዕራባውያኑ ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ አጀንዳዎችን በማራገብ ከአውዳቸው ውጪ በመተርጎም የሌለ ሙቀት በመፍጠር የሚታወቁ ሚዲያዎችን “ቢጫ ሚዲያ” እያሉ ይጠሯቸዋል። በእኛ ሀገር “አድምቄ” እንደምንለው ዓይነት መሆኑ ነው።]
ምዕራባውያን አልቃኢዳን፣ አይ ኤስ አይ ኤስን፣ አልሸባብን እና ቦኮ ሀራምን “አሸባሪ” ብለው ሲፈርጁ የሌሎች ሀገሮችን ፈቃድ ጠይቀው አልነበረም። በእነኚሁ ቡድኖች ላይ ከአፍጋኒስታን እስከ ሶማሊያ፤ ከሊቢያ እስከ የመን በምድር እና በሰማይ የጥይት አረር ያዘነቡባቸው ከምድረ ገጽ ሊያጠፏቸው አይደለም እንዴ? እነርሱ አሸባሪዎች ላይ ከወሰዱት ዘመቻ ይልቅ ዳንኤል ስለ አሸባሪዎቹ የተናገረው ዛቻ ምነው ጮኾ ተሰማ? ያው እነርሱ double standard የሚሉት የተዛነፈ ሚዛናቸው ጠባይ መሆኑ ነው።
ምዕራባውያኑ ISIS ን ሲጠሩ “Daesh” የሚለውን መጠሪያ ይሰጧቸዋል። በአረብኛ “ዳኤሽ” ማለት ከእግር በታች መርገጥ፣ ከትብያ መቀላቀል፣ መደምሰስ ማለት ነው። እነርሱ አሸባሪ ያሉትን ቡድን ረግጦ ከትብያ ቀላቅሎ ይደምሰስ የሚል ስም ሲሰጡት ትክክል ከሆነ ዳንኤል “ህወሓት መደምሰስ አለባት” ሲል ምን የሚያስጮኽ አዲስ ነገር ተገኘ? ሰውየው ነገር የሚገንንበት “ደመ መራር” ካልሆነ በስተቀር!
በዲሴምበር 2015 ፈረንሳይ ቡድኑን “ከአሁን በኋላ ISIS ሳይሆን “Daesh” ማለት አለብን” በማለት ያቀረበችውን ጥሪ የተቀበለችው እንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትሯ ዴቪድ ካሜሮን በፓርላማ ተገኝተው ሲናገሩ “እውነቱን ለመናገር ይህ ሰይጣን የሞት ፈረስ እውነተኛ የእስልምና ተወካይ አይደለም” ብለው ነበር።
[“Frankly, this evil death cult is neither a true representation of Islam, nor is it a state,” UK Prime Minister David Cameron told Parliament in December 2015 when announcing that his government would be joining France in calling the group “Daesh” rather than “Isil”]
የአሜሪካ የጸረ ሽብር ስፔሺያሊስት የሆኑት ጃሬት ብራችማን ደግሞ የአልቃይዳ ሰው ስለነበሩት አቡ ያህያ ሪፖርት ሲያቀርቡ “እነኚህን ድመቶች እያንጋጋ የሚነዳ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
ምዕራባውያን እና “ቢጫ ጋዜጠኞቻቸው” ሽብርተኛ ብለው የፈረጁትን ግለሰብ ወይንም ቡድን ሲያሻቸው “ሰይጣን” ሲፈልጉ “ድመት” ወይም “አይጥ” ብለው ሲጠሩ ጠያቂም ተቆጪም የለባቸውም። እኛ ግን በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን የሚያርድ፣ መንደራቸውን የሚያቃጥል፣ አስገድዶ የሚደፍር እና የሚዘርፍን ቡድን “እንደ ሰይጣን የመጨረሻ ፍጥረት መሆን አለባቸው” ብላችሁ መጥራታችሁ አሳስቦናል” የሚል የመግለጫ ጋጋታ ያዘንቡብናል።
ህወሓታውያን  “ኢትዮጵያን ሲኦልም ቢሆን ወርደን እንደመስሳታለን” ሲሉ ዝም ያሉት አሜሪካ እና አጃቢዎቿ “ህወሓት የተባለው አሸባሪ ቡድን መደምሰስ አለበት” ሲባል ግን ጆሮአቸው ይቆማል!
ህወሓት ከምድረ ገጽ የደመሰሳቸው የማይካድራ፣ የአጋምሳ፣ የጋሊኮማ፣ የጭና፣ የጨጨሆ፣ የራያ እና የቆቦ ሰማእታት በግፍ የፈሰሰው ደምን ዐይተው እንዳላዩ፤ ጩኸታቸውንም ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው እያለፉት ምዕራባውያን ይህንን ሁሉ ግፍ የፈጸመውን አሸባሪ የህወሓት ቡድን “መደምሰስ አለበት” ለሚለው የዳንኤል ንግግር መግለጫ ማውጣታቸው አንካሳ ሚዛናቸውን ከማሳየት ያለፈ እንጥፍጣፊ የሞራል ወዝ የለውም።
ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር በፖለቲካ አመለካከቱም ሆነ አሠላለፉ አንስማማ ይሆናል። በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ህወሓት ላይ ባለው አቋም ግን አንለያይም። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ዜጎች እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የተሰለፉት የህወሓትን አሸባሪነት እና ሰይጣናዊ ሀገር የማፍረስ ተልእኮ በግልጽ ስለሚረዱት ነው። ምዕራባውያኑ ዘንግተውት ከሆነ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር ተጠራርተው እየተመሙ ያሉት ህወሓትን ለመደምሰስ መሆኑን እናስታውሳቸዋለን።
Filed in: Amharic