>

ታሪክን ወደኋላ “..ለእኔ በዚህ ዓለም ላይ ከኢትዮጵያ የሚበልጥብኝ ነገር የለም...!!!”  (ይልማ ደሬሣ) 

ታሪክን ወደኋላ

“..ለእኔ በዚህ ዓለም ላይ ከኢትዮጵያ የሚበልጥብኝ ነገር የለም…!!!” 
ለይልማ ደሬሣ 

ክቡር አቶ ይልማ ደሬሣ…..ታላላቆቼ ክቡር ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስና ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ የገለጻችሁልኝ አስተያየት በአዕምሮዬ ስለተቀረጸ፤ ለሥራዬ መልካም ድጋፍ ሆኖ እንደሚረዳኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እዚህ ላላችሁት ለታላላቆቼና ለጓደኞቼ በአጭሩ ለማረጋገጥ የምፈልገው፤
“………ለእኔ ለይልማ ደሬሣ በዚህ ዓለም ከኢትዮጵያ የሚበልጥብኝ ነገር የለም…….”፡፡ ስለዚህ ለተላኩበት ለአሜሪካ ለሚያዳምጡኝ የአገሬን ችግር በተቻለኝ ዘርዝሬ አስረዳለሁ፡፡ ለሚከራከሩኝም በተቻለኝ ጠንክሬ እሟገታለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ክቡር ጸሐፊ ትዕዛዘ አስተያየት ሲሰጡ፤ ሥራ ሳይጀመር ብዙ የሚናገር ብዙ አይሠራም” ብለዋል፡፡ ስለዚህ እኔም ጥቂት የምናገርና ብዙ የምሠራ ሆኜ ለመገመት እንድችል፤ ንግግሬን ማሳጠር እወዳለሁ፡፡ ለሰጣችሁኝ ጥልቀት ላለው ምክርና ለገለጻችሁልኝ የጋለ መልካም ምኞት ከልብ የሆነ ምስጋናዬን እያቀረብኩ በሰላም ይግጠመን ብዬ እሰናበታችኋለሁ፡፡
ይህንን የተናገሩት ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ ሃገራቸውን ከእንግሊዝ ሞግዚትነት ለማላቀቅ ይቻል ዘንድ ወደ አሜሪካ መልዕክት ይዘው እንዲሄዱ ኃላፊነት የተሰጣቸው በሽኝት መርሃግብር ቀን ላይ ነበር።
ክቡር አቶ ይልማ ደሬሳ [ በአሜሪካን — ዋሸንግተን ዲሲ ] 
የክቡር አቶ ይልማ ደሬሣ የአሜሪካ የሚሲዮን ግብ ምንና ምን መሆኑ እንደተገለጸው፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዋና መልዕክተኛ ዋሽንግተን እንደደረሱ፤ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የተላከውን ልዩ መልዕክት ለአሜሪካው መሪ ለፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ለማቅረብ ቀጠሮ ጠየቁ፡፡ የስቴት ዴፓርትመንት፤ (ማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር) እና የዋይት ሐውስ ቤተመንግሥት ኃላፊዎች ከተወያዩበት በኋላ፤ የተሻለው መንገድ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት እ.ኤ.አ ሐምሌ 7 ቀን 1943 ዓ.ም የዓለም የእርሻና የምግብ ጉባኤ የመልዕክተኞች መሪዎች የሆኑትን የሬሴፕሽን ግብዣ በማድረግ ስለሚቀበሉ! በዕለቱ ክቡር አቶ ይልማ ደሬሣን የንጉሠ ነገሥቱን ልዩ መልዕክት ለማቅረብ እንዲችሉ ተወሰነ፡፡
በመሠረቱ አቶ ይልማ ዴሬሣ የያዙት ዋናው መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በእንግሊዞች ወታደራዊ አስተዳደር የደረሰባትን ችግር በተቻለ ያህል ለአሜሪካው መሪ በቃል ለማስረዳትና በሜሞራንደም (ማስታወሻ) ያዘጋጁትንም ጽሑፍ አያይዞ በእጅ – ለመስጠት ነው። በተጨማሪም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለወዳጃቸው ለፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ፈርመው የላኩትን የመታሰቢያ ፎቶግራፍ ለማቅረብ አቶ ይልማ ተዘጋጅተዋል፡፡ ነገር ግን የዋይት ሐውስ ፕሮቶኮል ሹም አቶ ይልማ ዴሬሣ ፕሬዚዳንቱን እንዲያነጋግሩ የፈቀደላቸው ጊዜ፤ ከሰባት ደቂቃዎች የማይበልጥ ስለሆነ በዚች ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ዋና ዋና ችግሮች አሟልቶ ለማስረዳት ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መልዕክተኛ እጅግ የከበደ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሎንዶን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ( School Of Economics ) የተመረቁትና ጣዕም ያለው እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆኑት ይልማ ዴሬሣ፤ አቀራረባቸውና የሚገልጹት ሐሳብ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልትን ስለማረከ የፕሮቶኮል ሹሙ የገደበላቸው የሰባት ደቂቃዎች ጊዜ ቢያልፍም፤ የኢትዮጵያ መልዕክተኛ አገራቸው የደረሰባትን በደል ዘርዝረው ለማስረዳት እንዲችሉ በፕሬቪዳንቱ ፈቃድ ጊዜ ተጨመረላቸው፡፡
አቶ ይልማ ደሬሣ ኢትዮጵያ የነፃነት አጋሮቿ ሆነው የመጡት እንግሊዞች፤ ዘወር ብለው ምን ያህል በደል እንዳደረሱባትና ሕዝቦቿን ለማስተዳደር መብቷን ነፍገው ምን ያህል እንዳስቸገሯት፤ አድማጭን በሚስቡና የርኅራሄነት ሰሜት በሚቀሰቅሱ ቃላቶች ለአሜሪካው መሪ ካስረዱ በኋላ ንግግራቸውን ሲፈፅሙ፤
“…..ክቡር ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያና በታላቁ ገዥዬ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስም ሆኜ ያቀረብኳቸውን ሐሳቦች፤ ለዚች ለምታሳዝንና ከባድ ችግር ላይ ለወደቀች አገሬ አንዳንድ እርምጃዎች ለማድረግ እንዲያስችልዎ በማሰብ፤ ልዩ ሜሞራንደም ስለአዘጋጀሁ ፤ እንዲቀበሉኝ ከፍ ባለ ትሕትና እለምናለሁ … ” በሚል ቃል ማስታወሻቸውን አቀረቡ፡፡”
ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት በጣም ተደሰቱ ፤ ይልማ ደሬሣ የት አገር እንደተማሩና በምን ሙያ እንደተመረቁ ጠይቆ ከተረዳ በኋላ ፤ የሚከተለውን ተናገሩ:-
……..“ እናንተ ኢትዮጵያውያኖች አገራችሁ ኢትዮጵያ ያላትን የተከበረ ጥንታዊ ታሪክና ባሕል የማንፀባረቅ ተሰጥዎ ያላችሁ ናችሁ። እኔ የዩናይትድ ስቴትስ መሪ ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ የንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴን መልዕክተኛ ስቀበል ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ዐስር ዓመት ከሚሆን ጊዜ በፊት የንጉሥ አማች የነበሩትን ራስ ደስታ ዳምጠውን በዋይት ሐውስ ተቀብዬ ሳነጋግር በእኝህ ትልቅ ሰው ላይ ያየሁትን ኢትዮጵያዊ ባሕልና ጨዋነት እርጋታና አስተዋይነት ሁልጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ ምን ይሆናል? እኝህን የመሰሉ ታላቅ ሰው በክፉዎቹ ፋሽስቶች እጅ በሚያሣቅቅ ሁኔታ መገደላቸውን ዘግይቼ ስሰማ እጅግ አዘንኩ፡፡ ይህንንም መሪር ሐዘኔን ለወዳጄ ለቀዳማዊ ኃይለሥሳሴ ጽፌላቸዋለሁ፡፡ አንተም ከንጉሠ ነገሥቱ የተላከልኝን መልዕክት ደህና አድርገህ) በማስረዳትህ ብቻ ሳይሆን ሐሳቡንም በጽሑፍ ማስታወሻ ስላቀረብክልኝ በጣም አመሰግናለሁ። ከነገርክኝ እንደተረዳሁት አንተ እዚህ በዋሽንግተን በምትቆይበት ጊዜ! ሊፈጸሙ የሚችሉትን ጉዳዮች እንድታውቀው ይደረጋል …” ብሎ ክቡር አቶ ይልማ አሰናበታቸው፡፡
Filed in: Amharic