>

 ይድረስ ለእግዜር (ዘ ምሳሌ)

ይድረስ ለእግዜር

 


እግዜር ሆይ ስማን

ሕዝቡ እያነባ የራሄልን እንባ
ሁሉ እያለቀሰ ሲወጣ ሲገባ
መንግስት ቁጭ ብሎ ሀገር ከፈረሰ
ሰዎች እረፍት አጥተው መከራው ከባሰ

ልጅ እናት አባቱን ተለይቶ በግፍ
መድረሻ እያሳጡት በየትም  ሰው ሲረግፍ
ህዝቡ እየፈለገ  የእግዜር እውነት ደጃፍ
ጠዋትና ማታ  በደጅ ሰላም ሲያልፍ

ከፈጣሪ ያለ  ስራው  የተሳካ
የሚገስጽ ጠፍቶ ሀገር የሚያስመካ
ስብእና ያለው  በእግዜር  የሚለካ
እጁ ንፁህ የሆነ ሰው ክብርሩ ያልተነካ

በዘር  ጉንጓን ገብቶ ሀገር  ያልሰበከ
ወደጥፋት መንገድ ሰው  ያላሾለከ
ስራው ሚመሰክር ህዝብን  ያላወከ
እንደዚህ ያለ አባት ስራው የተባረከ

ምእመን  ሰብስቦ ተስፋ  የሚሆናቸው
ከአምላክ እንዳይሸሹ መንገድ ሚመራቸው
ጣልቃ  እየገባ  ጠብን የማይዘራው
በዘር ተመርዞ ሰው ከሰው ማይለየው

ቅዱሳን መፅሐፍትን ከጠመጃ የለየ
ፍፁም መንፈሳዊ ከእግዜር ያልተለየ
በከንቱ ውዴሴ በአምላክ ያልታበየ
ፈጣሪ ይባርክ ብሎ ህዝብ ከህዝብ ያለየ

እንደዚህ ያለ አባት  ተቆርቋሪ የዕምነት
በነፍሱ ሚጨክን ቢሆን ሰማእትነት
እባክህ ላክልን  ሕዝብ እንዲኖር በእምነት
መንጋው ሳይበተን አንተ የሞትክለት!

 ዘምሳሌ
Email: zemessalee@gmail.com

Filed in: Amharic