>
5:13 pm - Saturday April 19, 2279

የመስቀል በዓል እንጨት ተደምሮ እሳት ተቀጣጥሎ ለምን ይከበራል? (ቢንያም ዘ ወይንዬ)

ቅዱስ መስቀል ፍቅር ነው

የመስቀል በዓል እንጨት ተደምሮ እሳት ተቀጣጥሎ ለምን ይከበራል?
ቢንያም ዘ ወይንዬ

 
ለመስቀሉ መገኘት የሮሙ ንጉስ ቆስጠንጢኖስ እና የንግስት ዕሌኔ ሚና ምን ነበር? ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጣ?
ዕሌኒና ተርቢኖስ የሚባሉ ሁለት ደጋግ ክርስቲያኖች ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ተርቢኖስና ዕሌኒ ኑሮአቸው ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት በመሆኑ ለብዙ ሰዎች እንደ ምሳሌ ሆነውይኖሩ ነበር፡፡ ተርቢኖስ ነጋዴ ነበር፡፡ከዕለታትአንድቀን ራቅ ወዳለ ሀገር በመርከብለንግድ ሄደ፡፡ ዕሌኒም ባለቤቷ ተርቢኖስ ለንግድ ወጥቶ እስኪመለስ ስለባሏ ከመጸለይና ከማሰብ በቀር ከግቢዋ አትወጣም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ተርቢኖስ ለንግድ ሄዶ ብዙ ዓመታትን ቆይቶ ከጓደኞቹ ጋር ወደሀገሩ ሲመለስ ከነጋዴዎች አንዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሽፍታና ከማዕበል ከልዩ ልዩ አደጋ ተርፈን በሰላም ተመልሰን ግን ሚስቶቻችን ሌላ ሳይወዱ ሳይለምዱ እናገኛቸው ይሆን? ብሎጠየቀ፡፡ ተርቢኖስ ግን “እንኳን በሰላም አደረሰን እንጂ ሚስቴን በዚህ አልጠረጥራትም” ብሎ ሲመልስ ሌላው ጓደኛው “ያንተሚስት ከማን ትበልጣለችና ነው አሁን ሄጄ ከሚስትህ ጋር ለምዳኝ ወዳኝ ወድጃት ብመጣስ ምን ይቅጣህ?” አለው፡፡
ተርቢኖስም በሚስቱ እሌኒ ተማምኖና ይህንን ብታደርግ ይህን ያህል ዓመት የለፋሁበት ሀብት ከነትርፉ ውሰድ አንተም ብታደርግ እንዲሁ ሀብትህ ከነትርፉ ለእኔ ይሁን ተባብለው ተወራረዱ፡፡ከዚያም መርከቡ ወደብ ከመድረሱ በፊት ነጋዴው ወደ ዕሌኒ ቤት ደረሰና በሩን አንኳኩቶሠራተኛይቱን ዕሌኒን ማነጋገር እፈልጋለሁና ንገሪልኝ ብሎ ጠየቃት፡፡ እሷም እያፈረችየተላከችውን ለዕሌኒ ነገረቻት ዕሌኒም ተቆጥታ ከመች ወዲህ ነው እንግዳ የማነጋግረው ብላ አሳፈረቻት፡፡
ሠራተኛይቱም ለነጋዴው መልሱን ስትነግረው ነጋዴው እንደማይሆንለት ከተረዳበኋላ ሌላ ተንኮል አቀደና ለሠራተኛይቱ ባልና ሚስቱ ብቻ የሚያውቁትን አንድ ነገር ብቻብትሰጪኝ ብዙ ገንዘብ ወርቅ እሰጥሻለሁ ብሎ ወርቅ ሰጣት፡፡ ሠራተኛይቱም ሁለቱ ብቻ የሚያውቁትን የእመቤቴ ሀብል አለ ያንን እመጣልሀለሁ መጀመርያ አንተ በከተማው ውስጥ እየዞርህነጋዴዎችን መጡ የብስ ረገጡ እያልክ አስወራ ከዚያም ተመልሰህ እንድትመጣ ብላ ሰደደችው፡፡ነጋዴውም እንደተመከረው የነጋዴዎቹን መምጣት በከተማይቱ እንዳወራ የነጋዴዎቹ ቤተሰቦችነጋዴዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ፡፡ የዕሌኒም ሰራተኛ እመቤቴ ነጋዴዎች መጡተብሎ ይወራልና፡፡ ባለቤትዎ በሰላም ስለመጡ ይዘገጃጁ ገላዎን ይታጠቡ ብላ መከረቻት፡፡ዕሌኒም ገላዋን ስትታጠብ ያንገቷን ሐብል ቁጭ ካደረገችበት ቦታ ሠራተኛይቱ አንስታ ለነጋዴውበተቃጠሩበት ዕለት ሰጣች፡፡ ነጋዴውም ለሠራተኛይቱ የውለታዋን ብዙ ገንዘብ ሰጥቶአት ደስእያለው ወደ ጓደኞቹ ሄደ፡፡ ለተርቢኖስ ሚስትህን ለምጃት ወድጃት መጣሁ አለው ተርቢኖስምውሸት ነው ለዚህ ምን ምልክት አለህ ብሎ ጠየቀው፡፡ ተንኮለኛውም ነጋዴ ያንን ሐብል አውጥቶይህ ሐብል የሚስትህ አይደለምን ብሎ ሰጠው ተርቢኖስም ደነገጠ የሚናገረውን አጣ፡፡በውርርዱምመሰረት ሀብቱን ሁሉ አስረከበና ባዶ እጁን ወደቤቱ እያዘነ እየተቆጨ ሔደ፡፡
ባለቤቷንበናፍቆትና በታማኝነት ስትጠብቅ የከረመችው ዕሌኒ በተርቢኖስ ያልተለመደ ሀዘንና ብስጭት ግራተጋብታ ወንድሜ ምን ሆነሀል? ለወትሮው እንኳን ይህን ያህል ዘመን ተለያይተን ቀርቶ ለጥቂትቀናት ተለያይተን እንኳ ለጥቂት ቀናት ተለያይተን ስንገናኝ እንነፋፈቃለን፡፡ አሁን ግን ከመጣህበትጊዜ ጀምሮ አዝነህ አይሀለሁ ብላ ጠየቀችው፡፡ ተርቢኖስም ብዙ የደከምኩበትና የለፋሁበት ሀብትንብረቴ እንዳለ ማዕበል አጠፋብኝ እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን አላት፡፡ እሌኒም የተማረች ናትናእግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን እንዳለ ኢዮብን አስበውአንተ እንኳን በሰላም መጣህ እንጂ ሀብቱ ውሎ አድሮ ይመጣል፡፡ እያለች አጽናናችው፡፡ተርቢኖስም እንግዲህ በተከበርኩበት ሀገር ተዋርጄ፣ በሰጠሁበት ሀገር ለምኜ ለመኖር አልችልምናወደሌላ ወደማያውቁኝ ሀገር እሔዳለሁ አንቺ ግን ሁሉ ይወድሻል ያከብርሻል ከወደድሸው ጋር ኑሪአላት፡፡ ዕሌኒም በደስታ ጊዜ አብሬህ እንደሆንኩ በችግርም ጊዜ ልለይህም የኔንና ያንተን አንድነትችግር አይፈታውም ከአንተ ተለይቼ ወዴት እቀራለሁ ወደምትሄድበት አብሬህ እሄዳለሁ ብላተነሳች፡፡
ሁለቱም ቤታቸውን ጥለው ሲሄዱ በመንገድ ላይ ተርቢኖስ በልቡናው ይዞት የነበረውን ምሥጢር አወጣው “ዕሌኒ ስወድሽ የጠላሽኝ ሳምንሽ የከዳሽኝ ምን አድርጌሽ ነው?” ብሎ ጠየቃት፡፡ ዕሌኒምእኔ አንተን አልጠላሁም አልከዳሁምም ይህንን ሐሳብ እንዴት አሰብህ ብትለው ከኪሱ አውጥቶሐብሉን አሳያትና የሆነውን ሁሉ ነገራት፡፡ ዕሌኒም ያልጠበቀችው ነገር ስለተፈጸመ አዝና የሆነውንእውነተኛ ታሪክ በሙሉ ነገረችው፡፡
ተርቢኖስ ግን አላመናትም፡፡ ከባህር ዳር በደረሱ ጊዜ በቁመቷልክ ሳጥን አሠርቶ ዕሌኒን በውስጡ አስገባትና ብታደርጊውም ባታደርጊውም እንደሥራሽ ሥራሽያውጣሽ ብሎ ወደ ባህሩ ወረወራት፡፡ ዕሌኒ ያለችበት ሳጥን በፈቃደ እግዚአብሔር እየተንሳፈፈከወደብ ደረሰ በዚያ ወደብ አካባቢ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር የነበረው ኮስታንዲዮስ /ቁንስጣ/የተባለው ንጉሥ ነበርና ሳጥኑን አይቶ አውጥቶ እንዲከፍቱት ወታደሮችን አዘዘ፡፡ ሳጥኑንአውጥተውም ሲከፍቱት እጅግ የተዋበች ሴት ሆና አገኟት ንጉሡም ዕሌኒን ወስዶ ሚስቱአደረጋት፡፡ ኮስታንዲዮስ /ቁንስጣ/ የመክስምያኖስ ቄሳር ሆኖ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር ነበር፡፡ንግስት ዕሌኒም በ272ዓ.ም ታላቁ ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱየአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንደሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ ባለሟሎችና ህዝቡ ተስማምተው የ18ዓመቱን ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ 25 ቀን 316 ዓ.ም በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያአነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሰራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ ነበር፡፡
ንግሥት ዕሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉየተሻለ ነበር፡፡ በተለይም በ312ዓ.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት ምታ ነጋሪት ክተትሠራዊት ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ በራዕይ በሰማይ ላይ “በዚህ መስቀል /ምልክት/ ጠላትህን ድልታደርጋለህ” የሚል መስቀልና ጽሑፍ ስላየ ለሠራዊቱ የመስቀል ምልክት በመሳሪያቸው እናበሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም በቲቤር ወንዝ ድልድይ ላይጠላቱን ድል ነስቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዥሆነ፡፡
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡ ንግሥት እሌኒምበተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327ዓ.ም ወደኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳመስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337ዓ.ም ተጠመቀ፡፡ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡ እንደደረሰችም ስለከብረ መስቀል መረመረች ጠየቀች፡፡ ቦታውን የሚያስረዳት አላገኘችም፡፡ የአይሁድ ወገን እንቢቢሉም በኋላ ግን ባደረገችው ጥረት አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመለከታት አስቆፍሪውብሎ ነገራት ኪራኮስም ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ እውነተኛው ተራራ ይህ ነው ብሎ ማሳየትባለመቻሉ ከሦስቱ ተራሮች አንዱ ነው ስላላት አይሁድ ተራሮቹን ይቆፍሩ ዘንድ አዘዘቻቸው፡፡የጌታችን ቅዱስ መስቀል ከጌታ ሞት እያመነ በተቸገሩ ግዜ ማንም እንዳያገኘው የኢየሩሳሌም ነዋሪሁሉ የእቤቱን ቆሻሻ የከበረ መስቀል ባለበት ቦታ እንዲጥል አይሁድ አዝዘው ስለነበር ከሁለት መቶዓመት በላይ ጥራጊ ስለጣሉበት ታላቅ ተራራ ሆነ፡፡
ዕሌኒ ተራሮቹን ለማስቆፈር ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ ለመለየት ደመራ አስደምራ ብዙእጣንም በመጨመርና በማቃጠል ከአኢየሩሳሌም ወጣብለውያሉትንኮረብቶች አሳያት፡፡ የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍናበመስገድ መስቀሉ ያለበትን ትክክለኛ ስፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ሰገደ ጢስ” ጢሱሰገደ ብሎታል፡፡ ከዚያም መስከረም 16 ቀን ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህልከተቆፈረ በኋላ መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችንየተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ተቸገሩ፡፡ የሞተ ሰው አምጥተው በሁለቱ መስቀሎች ላይበተራ ቢያስቀምጡት አልተነሣም፡፡ በመጨረሻ በአንዱ መስቀል ላይ ቢያስቀምጡት ያን ጊዜየሞተው ሰው ተነሣ፡፡ በዚህም የጌታን መስቀል ለዩት፡፡ ዕሌኒም የጌታ መስቀል እንደሆነ አወቃሰገደችለት፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘትበሰሙ ግዜ መብራት አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ አደረጉ፡፡ በዚህምምክንያት ይህ ታላቅ የድኅነት ምልክት የሆነው መስቀል የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ደመራበመደመር በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡
በመስቀል ደመራ በዓል ትዕይንት
ንግሥትዕሌኒ መስከረም 16 ቀን 320ዓ.ምበዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተመቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው ይህመስቀልም ከዚያ ዕለት ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩተአምራት እየሰራ ሙት እያነሳ ዕውር እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ፡፡ ይህንንም ከኃያላን ነገሥታትመካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው፡፡ በዚህ ጊዜ የአየሩሳሌምምዕመናን የድሉን ዜና ሰምተው ስለነበር የአንድ ቀን መንገድ ያህል ሄደው በመቀበል ካህናቱበዝማሬና በቸብቸቦ ወንዱ በሆታ ሴቱ በእልልታ ሆ! እያሉና ችቦ አብርተው ተቀብለዋቸዋል፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ለመስቀል ችቦ እያበሩ በዓሉን በሆታ በእልልታበስብሐተ እግዚአብሔር የምታከብረው ይህንን ታሪካዊ ትውፊት በመከተል ነው፡፡ ብዙየቤተክርስቲያን አባቶች እንደሚሉት ንጉሡ ሕርቃል ይህንን ታላቅ ድል ለማግኘትና የጌታን ቅዱስመስቀል ከአሕዛብ /ከፋርሶች/ እጅ ለማስመለስ የቻለው በዚያን ጊዜ አብያተ ክርስቲያንናት ሁሉለአንድ ሳምንት /አንድ ሱባዔ/ ባደረጉት ጾም ጸሎት ነው፡፡ ይህንንም ለማስታወስና ጌታንለማመስገን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያንበየዓመቱ የዐቢይ ጾም /የጌታ ጾም/ ከመጀመሩ አስቀድሞ “ጾመ ሕርቃል” ብለው አንድ ሳምንትይጾማሉ፡፡
የጌታ መስቀል ለብዙ ግዜያት ኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ ልውሰድ እኔልውሰድ በማለት ጠብ ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌምየሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ከ4ት ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎችታሪካዊ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት የቀኝ ክንፉ የደረሰውለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅዱሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡
ግማደ መስቀሉ ወደ ቅድስት ሀገር ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገባብ
ግማደ መስቀሉ ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖሩ በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸውእየጠነከረ ሲሔድ በእስክንድርያ የሚኖሩ ክርስትያኖች ላይ ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊው ዓጼ ዳዊት እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ”ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህአስታግስልን ብለው ጠየቁት ዳግማዊ ዓጼ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅርአስገድዷቸው 20,000 ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብጽ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብጽ ያሉ ኃያላን ፈሩተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞቹ ላከ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁከሆኑት ክርስቲያኖች ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋለሁ” የሚል ማስጠንቀቂያ ላከ፡፡የንጉሡ መልዕክትም ለእስላሞቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደ ጥንቱ በየሃይማታቸው ጸንተውበሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡ መታረቃቸውን ዓጼ ዳዊት ሰሙበዚህም ጉዳይ ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡
እግዚአብሔርንም አመሰገኑ በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችምከ12,000 ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤአድርገው ላኩላቸው፡፡ ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልክተው ደስ አላቸው ወርቁን ግንመልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፡፡ በግብጽ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝ 12,000 ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፡፡ የእኔ ዓላማ ወርቅፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንምየምለምናችሁ በሀገሬ ኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስየተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳን አጽም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነውየሚል ነበር፡፡
በእስክንድርያም ያሉ ምዕመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳቱጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለውየፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅዱሳት ጋር አሁን በመለሰው ወቄትወርቅ የብርና የነሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብርበሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቧቸው ጊዜ በእጃቸውእያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሏቸው፡፡
በዘመኑ ባንኖርም በመልካም ምኞታችን እንደ ኖርን ይቆጠርልን ዘንድ፣ ተጉዘን ቀራንዮ ባንገኝ፣ ርቀት ቢወስነንም ስለመሻታችን እንደተጓዝን ይደረግልን ዘንድ፣ አንድም ባለንበት አምነን ስላከበርነው በረከቱን ያድለን ዘንድ፡፡ ኑ ቀራንዮ እንሂድ በእግራችን አይደለም በመንፈስ እንጂ፣ ኑ በበዓላችን ቀን መስቀሉን እንዳሰው በእደ ሥጋ አይደለም በዕደ ኅሊና እንጂ፣ የመስቀሉ ፍቅር ምሥጢር ቀራንዮ እንዲገኝ ዛሬም ያዘጋጀነው ይህ የመስቀል በዓል የቀራንዮ አካል ነው፡፡ አንድም ግሸን ደብረ ከርቤ እንሂድ የእውነተኛው መስቀል አካል ከእኛው ዘንድ አለና፡፡ ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነበት፣ ደሙ የነጠበበት እውነተኛው መስቀል ለዓለም ብርሃኑን ያበራበትን የምናከብርበት ይህ ቀን ነውና፡፡ ምክንያቱም፡-
• መስቀል የፍቅር ዙፋን ነውና፤ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ በመስቀል ላይ ሳለ እስከመጨረሻው ሳይለይ የፍቅሩን መጠን ተረድተዋል፡፡ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ የጌታን ሕማሙን በዚያች ሌሊት የአዳሩንና የውሎውን ለሰው ልጆች  ፍቅር ሲል በሰው ልጆች እጅ የተቀበለውን ጽኑ መከራውን አይተዋልና፤ በመልእክቱም ”ፍቅርም እንደዚህ ነው፣ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደወደደን ስለ ኀጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደላከ እንጂ እኛ እግዝአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም” (1ዮሐ. 4: 10) ያለው፡፡ የሰቀሉትን እንኳ ወደዳቸው፣ ይቅርም አላቸው፡፡ በመስቀሉ ዙፋን  በፍቅሩም ድነዋልና ”አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ” እንዲል፡፡
• መስቀል የጥበብ ቤት ነውና፤ ጠቢቡ ሰሎሞን ” ጥበብ ቤትዋን ሠራች … ፍሪዳዋን አረደች … ማድጋዋን አዘጋጀች … ሁሉን ጠራች … ኑ እንጀራዬን ብሉ … አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፣ በማስተዋል መንገድ ሂዱ … ”(ምሳሌ 9፥ 1-10) ሲል፤ በቅዳሴ መጽሐፍ ላይ ጥበብ መድኀኒታችን ነው በማለት የሚሥጢሩን ባለቤትን ያመሠጥራል፤ በመስቀል ላይ ጥበብ የተባለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ ሆኖ ዓለም ሁሉ ተመግቦት ድኖአልና፡፡ ለእኛ በመስቀል ጥበብ ቤት ላይ የተሰቀለው ጥበብ መድኀኔዓለም በዛሬው በምናከብረው የጥበብ ምሥጢር መገኛ በሆነው የመስቀል በዓል ራስ እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህም እርሱን የዓለምን መድኅን እንሰብክበታለንና፡፡ ”አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፣ የግሪክ ሰዎች ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ቆሮ. 1፥22-23) እንዲል፡፡
• መስቀል የክርስቲያኖች ሁሉ አርማ ነውና፤ በምድራውያን ልማድ የሀገር ነጻነት በሰንደቅ ዓላማ አርማነት መውለብለብ እንዲታወቅ ሁሉ፣ ዛሬ የሰማያውያን ተስፋና የሕይወት አርማ በዓለም ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ መውጣት በክርስቶስ የታወጀበት ሰንደቅ ዓላማ መስቀል ነው፡፡ በሀገራችን ከአደይ አበባ ውበት ጋር አንድ ሆኖ የሚውለበለብበት መስከረም 16ና 17 ልዩ ክብረ በዓሉ ነው፡፡ ልዩ የሚያደርገው ከአርማ ጋር የእግዚአብሔር ኀይል መሆኑ ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል ምንኛ ድንቅ ነው? ዕፅነት/መስቀሉ የተቀረጸበት እንጨት/ ከመለኮት ኀይል ጋር አንድነት፣ ድንቅ ተዋሕዶ፣ አጋንንት የሚርዱለት የክርስቲያኖች ቤዛ ልዩ ምልክት፣ ለመረጣቸው ብቻ ኀይልን ያደርጉበት ዘንድ የታደሉት ግርማ ሞገስ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ”የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፣ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው (1ቆሮ 1፥18) እንዲል፡፡
የመስቀል ፍቅር ሰው፣ ልዩ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ”ወሶበ ርእዮሙ እግዚእ ኢየሱስ ለእሙ ወለረድኡ ዘያፈቅር ይቀውሙ፤  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደውን ደቀ መዝሙርና እመቤታችንን ከእግረ መስቀል ቁመው ባያቸው ጊዜ ሲል፣ ድንግል ልብዋ በሀዘን ጦር ተወግቶ የልጅዋን መከራ መቻል ጭንቅ በሆነባት ጊዜ ልጅዋ መሪር ሃዘንዋን ተመለከተ፤ እንዲሁም ከአጠገቧ ካሉት በእንባ ከሚራጩት የኢየሩሳሌም ሴቶች ጋር ከወንድ ወገን የሚያጽናናት አንድ ሰው ቅዱስ ዮሐንስን አየው፡፡ ወይቤላ ለእሙ ኦ ብእሲቶ ነዋ ወልድኪ፤ አንች ሆይ ልጅሽ ይርዳሽ ያጽናናሽ አላት፡፡ ውሉድኪ ሲል ነው በዮሐንስ እኛን ለእርስዋ መስጠቱ ነውና፡፡ ወይቤሎ ለውእቱኒ ረድ ነያ እምከ፣ ደቀ መዝሙሩንም እነኋት እናትህ ታጽናህ አለው እምክሙ ሲል ነው፡፡ በዮሐንስ እርስዋን ለእኛ መስጠቱ ነውና”፡፡ (ዮሐ.19፥26-27)ብሎዋል፡፡ እነሆ ተመልከቱ፣ ለቅዱስ ዮሐንስ የባሕሪያችን መመኪያ የሆነችውን የተወደደች ድንግል እመቤት እናት ትሆነው ዘንድ ከአምላኩ ፈጽሞ ተሰጠችው፡፡ ድንግልን ከመስቀሉ ፍቅር ለይቶ ማየት ከቶ አይቻልም፡፡
መስቀል ፍጹም ፍቅር፣ ርኅራሄ፣ የዋህነት እንደሆነ ሁሉ፣ ድንግልም እንዲሁ ፍጹም ፍቅርን የተሞላች የፍጡር ሁሉ ፍቅር ቢደመር የእርስዋን ፍቅር ይደርስ ዘንድ ሊታሰብ አይችልም፤ ርኅራሄዋ እንኳን ለሰው ልጅ ለፍጡር ሁሉ የምታዝን አዛኝት ናት እንጂ፤ በየዋህነትዋ የዋሂት ርግብ የተባለች ፍጹም ናት እንጂ፡፡ድንግል በዚህ ዓለም ሳለች ልጅዋ እንደተሰቀለ ሆኖ በኅሊናዋ ተስሎ፣ ልብዋ በሕማሙ ጦር ተወግቶ፣ ሃዘንዋ ጸንቶ፣  በሰቆቃ ተውጣ፣ እጅዋን ወደ ላይ ዘርግታ አንድም ስለልጅዋ ኀዘን እንባዋን ስታዘራ በሌላም ልጅዋ ይምረን ዘንድ ስለእኛ ስለ ሰው ልጆች ምልጃ ታደርግ ዘንድ ከቀራንዮ ከስቅለቱ ቦታ እንዲሁም ከመቃብሩ ጎልጎታ አንድም ቀን ተለይታ አታውቅም ነበር፡፡ ሕማሙን እንደ እርስዋ ማን ተረዳ? ድንግልን የመስቀሉ ፍቅር እንዲገባን አማልጂን ብለን እንማጸናት፣ በአምስቱ ኀዘናትሽ ቃል ኪዳን አስቢን እንላት ዘንድ የዚህ ዓለም ፈተና ግድ ይለናልና፡፡ ልጅዋን ወዳጅዋን፣ እስዋንም ደስ እናሰኝ ዘንድ ፍቅርዋን፣ ርኅራሄዋን፣ የዋህነትዋን እንምሰል፡፡ ወገኖቼ ቂም በቀል፣ ክፋት፣ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ ዘረኝነት፣ወዘተ እንተው፣ ለዚህ ዓለምም ለወዲያኛውም አይጠቅሙምና፡፡
እኛም ዛሬ ቅዱስ ዮሐንስን የመስቀሉ ፍቅር አብነት እናድርገው፣ ይኸውም ልዩ የሚያደርገው  መለኮታዊ ፍቅሩን መረዳቱ፣ የመስቀሉ ሥር የፍቅረ ሰው መሆኑ፣ የጌታን የሕማሙን ጥልቀት መጠን ማስተዋሉ፣ ሁል ጊዜ ነገረ መስቀሉን በማሰብ ቁጽረ ገጽ መሆኑ፡፡ ከዚህ ዓለም ልዩ በሆነ ፍቅር ጌታውን የመውደዱ፣  ”እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት አምላክ የሰው ልጅን ከመውደዱ ጋር ሰው ወንድሙን ቢጠላ እግዚአብሔርን እንዳያውቅ በሚለው ኀይለ ቃልና ረቂቅ ምሥጢር ከተግባራዊ ሕይወት ጋር አቅርቦቱን ልብ ልንለው ግድ ይለናል፡፡
በነገረ መስቀሉ አንጻር፣ የድንግል እመቤታችንና የቅዱስ ዮሐንስ ፍቅረ መለኮት ሕይወታቸው ቅድስናን አጎናጽፏቸው ተገኝቷል፡፡ እኛም ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ለሁላችንም ”ዓለምንና በዓለም ያሉትን አትውደዱ … የአባት ፍቅር በውሰጡ የለም፣ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል” (1ዮሐ. 2፥15.17) በማለት የሕይወቱን ተግባራዊ ትምህርት እንዳስተላለፈልን ሁሉ፤  በዚህ ዓለም ስንኖር ነፍስና ሥጋችንን በፍቅረ መለኮት ተጸምዶ፣ በሕማማተ መስቀል ውስጥ ተገብቶ በፍቅር ውስጥ መኖርን፣ መንፈሳዊ አገልግሎታችን በፍቅረ መስቀል አንጻር ብቻ ሆኖ መሰለፍን፣ መሰባሰባችን በፍቅረ እግዚአብሔር ግብዣ ማድረግን፣ ሥራችንን በፍቅር ውስጥ ማከናወንን ያመለክተናል፡፡ ትዳራችን የመስቀል ፍጹም ፍቅር፣ ርኅራሄ፣ የዋህነት የተሞላ ሁል ጊዜ ለይቅርታ ዝግጁ የሆነ በዘለዓለም ሕይወት ተስፋ የተሞላ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ባጠቃላይም ሕይወታችን  በመንፈሳዊ ኅሊና የተዋበና የመስቀሉን ፍቅር የሚያዘክር ይሆን ዘንድ፣እግዚአብሔር እርሱን በመውደድና በመንፈሳዊ የፍቅር ወላፈን  ይጸምደን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን፡፡ አሜን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን!!!
Filed in: Amharic